ሲያልቅ ወይም ሊያልቅ ሁልወት ቀን ሲቀር የማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ግልጽ ያልሆነ ቅኔ ያዘለ መልዕክት ያስተላለፉት የቀድሞዋ ፕረዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተሸኙ። መንግስት ለሃሜት የማያመች፣ የትችትን በር የሚያዘጋ ሹመት መስጠቱን አስተያየት የሰጡ ገለጹ። ታዬ አቅጸስላሴ ተክተዋቸዋል።
” የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው ጊዜም እንደ ሰው ሲገፋው፣ መሄጃ መውጫ ሲጠፋው ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው” ማለታቸውን ተከትሎ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ዜናውን በሰበር አሰራጭተውት ነበር። በታሰበው መሰረት ሳይሆን በርካታ ትችት ያስተናገዱት ሳህለቀርቅ ዘውዴ፣ ” የስራ ጊዜውን ሲያጠናቅቅ እንደሚሰናበቱ የሚታወቅና በህግ የተቀመጠ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ስንብታቸው ሰበር መባሉ የአገሪቱን የሚዲያ ፊት አውራሪዎች ሙያዊ ውድቀት የሚያሳይ ነው” በሚል ትችት የሰነዘሩ ነበሩ።
አንዳንድ የህትመት ውጤቶችና አሜሪካ የሚገኙ የዩቲዩብ ወሬ ነጋሪዎች ምንጮች እንደነገሯቸው ጠቅሰው ዛሬ ስንብት እንደማይደረግ፣ አዲስም ምርጫ እንደማይከናወን ጽፈው ነበር። ስም እንዳይጠቀስ የጠየቁ ስውስጥ አዋቂዎች “አዲሱ ፕሬዚዳንት አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጫፎ ናቸው” ብለውም ነበር። ዛሬ ይፋ እንደሆነው ሁሉም ሳይሆን ቀርቶ አዲስ ፕሬዚዳንት ተሰይሟል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሆኑ ማግስት “ኢትዮጵያ ከረዥም ዓመታት በሁዋላ ለቦታው የሚመጥን ሰው አገኘች” በሚል ተሞግሰዋል። ግብጽ ሶማሊያ መግባቷን አስመልክቶ ለሚዲያና ለህዝብ ማብራሪያ ሲሰጡ ባሳዩት እውቅትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ ” በከዚህ በፊቶቹ ሚኒስትሮች አፈርን” በሚል ሰፊ አድናቆትን ተላብሰው ነበር።
በረጋ፣ ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነ፣ የዓለምንና የአፍሪቃ ቀንድን ፖለቲካ ባሳለጠና የኢትዮጵያን ቁልፍ ሚና በማጉላት በተባበሩት መንግስታት ያቀረቡት ንግግር እነ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴንና አቶ ተስፋዬ ዲንቃን ህዝብ እንዲያስታውስ አድርገዋል። በወጉ የተጻፈውን እንግሊዘኛውን ማንበብ የማይችሉ የፖለቲካ ሹመኞች በዓለም አደባባይ የተጻፈላቸውን ማንበበ እያቃታቸው ሲወራጩ ለተመለከቱ ታዬ አቅጸ ስላሴ ካላቸው አቅም በተጨማሪ ኢትዮጵያን በወከሉባቸው መድረኮች ያሳዩት ሞገስና በራስ መተማመን የበርካቶችን ቀልብ እንዲስቡ አድርጓቸው ነበር።
አቶ ደመቀን በተኩ አጭር ጊዜ ውስጥ ይሁንታ ያገኙትና ዛሬ የሣኅለወርቅ ዘውዴ የሥራ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የሆኑት ታዬ አቅጸ ሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ባካሄደበት ቀን በምክር ቤቶቹ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ቀጥሎም ከቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሣለወርቅ ዘውዴ የሥራ እርክክብ አድርገዋል፡፡
ከስንብታቸው ሁለት ቀን በፊት በኤክስ ገጻቸው ብሶት ቢጤ ያሰሙት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ እንዳሰቡት ሳይሆን ከፈተኛ በሚባል ደረጃ ተቃውሞ አስተናግደው ዛሬ ሲሰናበቱ፣ የተኳቸው ታዬ አቅጸ ስላሴ መሆናቸው መንግስት ወቀሳ እንዳይነሳ የሄደበት ርቀት የተሳካ እንደሆነ አመልካች መሆኑ ተመልክቷል።
በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ የተወለዱት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእንግሊዙ ላንክስተር ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በስትራቴጂ ጥናት አግኝተዋል። እንዲሁም አጫጭር የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ፖለቲካል ሳይንስ ሥልጠናዎችን እና ኮርሶችን በተለያዩ ሀገራት ተከታትለዋል፡፡
የሥራ ሕይወታቸውን በተመለከተም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ መምሪያ የሥራ ክፍል፣ የምዕራብ አውሮፓ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢንፎርሜሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር፣ በስቶክሆልም የኢፌዲሪ ኤምባሲ አማካሪ፣ በዋሽንግተን የኢፌዲሪ ኤምባሲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
እንዲሁም በ1998ዓ.ም በሎሳንጀለስ ቆንስላ ጀነራል ባለሙሉሥልጣን አምባሳደርነት መሾማቸው እና በሎስአንጀለስ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ማዕረግ የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡
በአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል እና በ2008 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ በመሆንም አገልግለዋል፡፡
በሌላ በኩል በግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ተጠሪ በመሆን ለሀገራቸው ሠርተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። ከየካቲት 15 ቀን 2016 ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ግለ ታሪካቸው ያስረዳል። በዛሬ ውዕለት ማለትም ከመስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ታዬ እኚህ ናቸው።
ኢትዮጵያን በመወከል የ74ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የተባበሩት መንግስታት ዩኒሴፍ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡
ባለፉት 4 አስርት ዓመታት ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በታላቅ ቅንነት፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን ለዚህም የረጅም ዘመን የመንግሥት ሰራተኛ አገልግሎት የክብር የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡
በቴሌግራም ይከተሉን እባክዎ https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk