ይባስ ብሎ የታጠቁት ኃይሎች ከሀገሪቷ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ሳያፍሩ እና ሳይሸማቀቁ አስታውቀዋል፤ ጥምረታቸውም በመታዘዝ፣ በሎጀስቲክስ እና በወታደር ድጋፍ እንደተጀመረ መንግሥት ደርሶበታል
በአማራ ክልል የማጽዳት ስራው በይፋ መጀመሩን የአገር መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ ጋር በመሆን አስታወቀ። “የተጀመረው ኦፕሬሽን የተጠና፣ አውድን የለየ፣ ጀሌን ከመሪ የነጠለ እና የቡድኑን ሴል በሚበጣጥስ መልክ የሚመራ ነው” ተብሏል። በከተሞች አካባቢ የተፈጸሙት እርምጃዎች ውጤት ያሳዩ እንደነበሩ ተመልክቷል። እርምጃውን የፋኖ ደጋፊዎች በአማራ ክልል “ሁለት ቦታ ይጫወታሉ ” በሚል የታሰሩትን አስመልክቶ ተቃውሞ እያሰሙ ነው።
“መንገድ ዝጉ እና ተማሪዎች አይማሩም ከሚል ቡድን ጋር ከዚህ ያለፈ ትዕግስት አይኖርም” በማለት ሕግ የማስከበር ሂደቱ የሚቆመው የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ያስታወቁት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ናቸው።
መግለጫውን የተከታተለው አሚኮ እንዳለው በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለማስተካከል ሕግ የማስከበር እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል። የሕግ ማስከበር እርምጃውን በሚመለከት የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ መንግሥት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በክልሉ ያለው የታጠቀ ቡድን የመከላከያን የቆየ ቁስል እየነካ እና ትዕግስቱን እየተፈታተነ የመጣ እንደ ነበር ይታወቃል ያሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለሕዝብ ሰላም ሲባል ብዙውን ነገር በዝምታ አልፏል ብለዋል።
ለመከላከያ ሠራዊት የሚሰጠው ዝቅ ያለ ግምት፣ ስም ማጥፋት እና ማጠልሸት ከአማራ ሕዝብ ሥነ ልቦና የመነጨ እንዳልኾነ ሠራዊቱ ያውቃል ያሉት ኮሎኔል ጌትነት ሠራዊቱ ለሕዝብ ሰላም ሲባል ዛሬም ከኢትዮጵያዊነቱ ሳይወርድ ሕግ ያስከብራል ብለዋል።
የኦፕሬሽኑ ዓላማ ሁከትን እና ብጥብጥን አስወግዶ ለክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ሰላምን ማስፈን ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “ሕግ የማስከበር ሂደቱ የሚቆመው የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ ሲረጋገጥ ነው” ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት በቡድኑ ላይ የሚወስደው ኦፕሬሽን የተጠና፣ አውድን የለየ፣ ጀሌን ከመሪ የነጠለ እና የቡድኑን ሴል በሚበጣጥስ መልክ የሚመራ ነው ብለዋል። ከሰሞኑ በከተሞች አካባቢ የተፈጸሙት እርምጃዎች ውጤት ያሳዩ ነበሩ ብለዋል።
መከላከያ የአማራን ሕዝብ ስለሚያከብር የክልሉ መንግሥት የጀመረው የሰላም ጥረት ዳር እንዲደርስ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል ያሉት ኮሎኔል ጌትነት ከመንግሥት ጋር በሰላማዊ መንገድ የሚነጋገሩ ካሉ በሮቹ ያልተዘጉ ቢኾኑም መከላከያ ግን ሕግ ማስከበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ በሚገባ የተጠና ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ንጹሐንን ለመጠበቅ ሲባል በጥንቃቄ ይመራል ብለዋል። የማኅበራዊ ሚዲያው ጩኽት ግን የሚጠበቅ እንደኾነ ጠቁመዋል። በምንም መንገድ ቢኾንም ግን መንገድ ዝጉ እና ተማሪዎች አይማሩም ከሚል ቡድን ጋር ከዚህ ያለፈ ትዕግስት አይኖርም ብለዋል።
ይባስ ብሎ የታጠቁት ኃይሎች ከሀገሪቷ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ሳያፍሩ እና ሳይሸማቀቁ አስታውቀዋል፤ ጥምረታቸውም በመታዘዝ፣ በሎጀስቲክስ እና በወታደር ድጋፍ እንደተጀመረ መንግሥት ደርሶበታል ነው ያሉት ኃላፊው።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሕግ የማስከበር ርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው÷ ልሂቃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ አሳስበዋል።
ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቀርብዋል፡፡
ይህንኑ ዘመቻ ተከትሎ የፋኖ ደጋፊዎች “የጅምላ እስር ተጀምሯል” በሚል ብልጽግና ያሰራቸውን የራሱ አባላት እንዲፈታ እየጠየቁ ነው። በፓርቲው በኩል “ሁለት ቦታ እየተጫወቱ ነው” በሚል ማጽዳት መጀመሩን በመቃወም ተቃውሞ ከመሰማቱ ጎን ለጎን “ጅምሩ ጥሩ ነው ተነካክቶ እንዳይቆም” ያሉም አሉ።
መሳይ መኮንን ከተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች እንዳገኘው ገልጾ በንባብ ይፋ ባደረገው ጥሪ መላው የአማራ ህዝብ ይህን ዘመቻ ለማክሸፍ እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል።
ከፍኖ አደረጃጀቶች ውስጥ ለጊዜው ስማቸው ይፋ ያልሆነ ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን በክልሉ የቋቋመው የሰላም ኮሚሽን ሰሞኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk