አምስት ባንክ ያልሆኑ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ ግብይት እንዲያካሂዱ ፈቃድ ተሰጣቸው
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ ጨምሯል – የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል – አቶ አህመድ ሽዴ
-የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ ጨምሯል ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው እለት ተገምግሟል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አማካኝነት ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ስራ ላይ የቆየውን የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ መሰረታዊ በሆነ መልኩ ማሻሻል ተችሏል ብለዋል፡፡
ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀረፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡
ለአብነትም ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት በባንኮችና በትይዩ ገበያ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ልዩነት ወደ 3 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት በባንክና ትይዩ ገበያ መካካል ያለው የውጭ ምንዛሬ ልዩነት ከመቶ በታች ከሆነ አፈጻጸሙ ጤናማ መሆኑንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን ተከትሎ በወጪ ንግድ አፈጻጸም የተሻለ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በተያዘው መስከረም ወር የተመዘገበው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ53 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
ከሃዋላ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢም ካለፈው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ145 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
በከፍተኛ ሁኔታ ለኮንትሮባንድ ተጋልጦ የነበረው የወርቅ ወጪ ንግድም እጅግ መሻሻል ማሳየቱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከወርቅ ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 58 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር ጠቅሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት አስካሁን ባለው ሂደት ከወርቅ ወጪ ንግድ 488 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ መጨመሩን ጠቁመው ይህም ማሻሻያው ስኬታማ አፈጻጸምን እያስመዘገበ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ስርዓቱን ጤናማነት ለመጠበቅ የጀመራቸውን ጥብቅ ቁጥጥሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ ረገድ ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ምንዛሬና ብድር አሰጣጥ ጋር ተያያዝ ተገቢና ህጋዊ ያልሆነ አካሄድ በሚከተሉ ባንኮች ላይ ጠንካራ ቁጥጥርና የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ ዜና ብሄራዊ ባንክ ባንክ ላልሆኑ አምስት ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ ስራ እንዲሰሩ ፈቃድ መስጠቱን ይፋ አድርጓል። ባንኩ ይፋ ያደረገውን መግለጫ ከስር ይመልከቱ።

በተመሳሳይ ዜና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል -ሲሉ አቶ አህመድ ሽዴተናግረዋል።
አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ሁለት ወራት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው እለት ተገምግሟል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያለፉት ሁለት ወራት አፈጻጸም በዝርዝር መገምገሙን በተለይም ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም ማሻሻያው ኢኮኖሚው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ከማድረጉም ባሻገር በዜጎች ላይ የሚፈጠርን ማህበራዊ ጫና በቀነስ አግባብ መተግበሩን ነው ያነሱት፡፡
በቅርቡም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን በማሻሻያው አፈጻጸም ላይ ግምገማ በማካሄድ በተሳካ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ ትኩረት የመንግስትን ገቢ ማሻሻል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል።
በዚህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ ገቢ መገኘቱን ነው ያብራሩት፡፡
በቀጣይም የመንግስትን ገቢን የማሳደጉ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አቅጣጫ መቀመጡን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የገቢ ማሻሻያውን በሚመለከትም ከግብር ከፋዮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዝቅተኛ ገቢ በሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግስት አስቀድሞ የዝግጅት ስራ በማከናወን ወደ ትግበራ መግባቱንም ነው የገለጹት፡፡
በዚህም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ከመስከረም ጀምሮ የሚተገበር የደሞዝ ጭማሪ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
መንግስት ዘይት በድጎማ እንዲገባ ማድረጉንና የማዳበሪያ ድጎማውም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በከተማና ገጠር ለሚተገበር የማህበራዊ ሴፊቲኔት መርሃ ግብርም መንግስት 60 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በመያዝ ተጨማሪ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው የእዳ ሽግሽግ ላይ የተሻለ ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ንግድ ባንክ ለተለያዩ የልማት ድርጅቶች አበድሮት የቆየውና ያልተከፈለን እዳ ለማሸጋሸግና ለካፒታል እድገት ጭማሪ በገንዘብ ሚኒስትር በኩል እስከ ዘጠኝ መቶ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ቦንድ ለንግድ ባንክ ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡
በትሬዥሪ ቢል አመካኝነትም ለረዥም ጊዜ ያልተከፈሉ ብድሮች ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ እንዲቀየሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ሀገር የብድር ሽግሽግን በሚመለከትም በቡድን 20 የተቋቋመው የአበዳሪ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የብድር ማሸጋሸግ ዋስትና መስጠቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ የውጭ እዳ እፎይታ እንደምታገኝ ጠቁመዋል፡፡
ከልማት አጋሮች ጋር የሚደረገው ውይይትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ሚኒስትሩን ጠቅሶ ኢዜአ ነው የዘገበው
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk