በርካታ ተፈናቃዮች፣ በሃዘንና በጦርነት የስነልቦና ጉዳት ያላገገሙ ቤተሰቦች፣ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ ቁስለኞች በቅጡ ባልዳኑበትና ድፍን ትግራይ ከሁሉም ዜጎች ድጋፍ በሚያስፈልገው በዚህ ወቅት የስልጣን ጥማት እያባላቸው ያሉት የችግሩ ጠማቂዎች ዳግም የትግራይን ህዝብ በመግለጫ ጋጋታ እያሸበሩት ነው። በትግራይ አዛዥና ታዛዡ ህዝቡን ግራ አጋብቶታል። ራሱን የትግራይ የጸጥታ ሃይል ብሎ የሚጠራው አካልም የመግለጫ አካል ሆኖ እየዛተ ነው።
ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሊቀመንበርነት የሚመሩት የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ድርጅት (ትህነግ) ትናንት እንዳስታወቀው ሹም ሽረት አካሂዷል። መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም አካሄድኩት ባለው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ትህነግን ወክለው በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያሉ ባለስልጣናት ከኃላፊነታቸው እንዲወርዱ ወስኖ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎ ” ለሚፈጠረው ማንኛውም ዓይነት ጥፋት ብቸኛ ተጠያቂ ቡድኑና አመራሩ መሆናቸውን ለህዝባችን መግለፅ እንወዳለን ” ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የመግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።
ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር መግለጫ ቀጥሎ ደግሞ “በህዝቡ ውስጥ የመረበሽ ስሜት ተፈጥሯል ፤ ችግር ሲፈጠር ዝም ብለን አንመለከትም ” ሲል የትግራይ ፀጥታ ኃይሎች የሚሰኘው መዋቅር ሌላ መግለጫ አሰራጭቷል። የጸጥታ ኃይሉ ዝም ብሎ እንደማይመለከት ከማስታወቁ ውጪ የትኛው ወገን ላይ እንደተደገፈ ያለው ነገር የለም።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ስርዓት አልበኝነት ለመቆጣጠር መወሰኑን ይፋ ባደረገበት መረጃ፣ በመግለጫ የመንግስት ግልበጣ ያካሄዱትን የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን” የጥፋት ሃይል ” ሲል በስም ሳይገልጽ አውግዟቸዋል። በዚሁ “የጥፋት ኃይል”በተባለው አካል ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምርም አመልክቷል።
የጸጥታ ኃይሉ መሪ የቀድሞ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በጊዚያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ሁለተኛ ሰው እንደመሆናቸው እርምጃ የሚወስደው ክፍል ውገን ቢሆኑም፣ የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን ጋር በተለያዩ መድረኮች መታየታቸው በርካቶች ላይ የአሰላለፍ ጥያቄ አስነስቷል። በሌላ ወገን አንድንድ በስም የሚጠቀሱ የቀድሞ ጄነራሎች ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው ሌላ ስጋት የፈጠረ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማል።
አቶ ጌታቸው “ እኔ በኤርትራ በኩል የምልከው ወርቅ የለኝም“ በማለት ከኤርትራ ጋር የተለየ ግንኙነት እንደሌላቸው ማስታወቃቸው አይዘነጋም። “ከኤርትራ ጋር ሆኜ እገሌ ለመምታት፣ ከፌደራል ጋር ሆኜ እገሌ መምታት ወደ ሚል ጨዋታ አልገባም” ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው የተናገሩት ዶክተር ደብረጽዮን ከኤርትራ ጋር እንደሚገናኙ ጠቅሰው ለኮነኑት ምላሽ ሲሰጡ ነበር።
አቶ ጌታቸው ያለ ምንም ምክንያት “ወርቅ” እና “ኤርትራ” ሊሉ እንደማይችሉ የገለጹ ንግግራቸው በትግራይ በህገወጥ የወርቅ ዘረፋ ላይ የተሰማሩ የታጣቂ ኃይሎች አመራሮች ወርቅ በኤርትራ በኩል እንደሚያሸሹ በመረጃ ተደግፎ የተሰራጨውን ዜና ሲያረጋግጡና ሕዝብ ጉዳዩን እንዲያውቅ አጀንዳ ለማስቀመጥ አስበው ነው።
ከሻዕቢያ ጋር በመሆን ጦርነት ለመክፈት እያሴሩ ክፍሎች ያሉ መኖራቸውንም “ከኤርትራ ጋር ሆኜ እገሌ ለመምታት፣ ከፌደራል ጋር ሆኜ እገሌ መምታት ወደ ሚል ጨዋታ አልገባም” ሲሉ መናገራቸው፣ የአረና ትግራይ አመራሮች “ከኤርትራ ጋር ግንኙነት የጀመሩ ቡድኖች አሉ” ሲሉ ከተናገሩት ጋር መመሳሰሉ በትግራይ ህዝብ ዘንዳ “ጦርነት ሊነሳ ይችላል” የሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
አቶ ጌታቸው በምንም መልኩ ካሁን በሁዋላ ጦርነት በትግራይ ምድር እንዲደረግ እንደማይፈቅዱና እንደማይተባበሩ በግልጽ ማስቅመጣችው፣ ይህንኑ አሳባቸውን የገዙላቸው መበራከታቸውን ያልወደዱት ወገኖች ከስልጣን እንዲነሱ ሲሰሩ ቆይተው ትናንት በመግለጫ መፈንቅለ መንግስት ማካሄዳቸውን ይፋ አድርገዋል።
ይህንኑ ለጊዜው በመግለጫ ደረጃ የተካሄደ መፈንቅለው መንግስት፣ ህግና ስርዓት ለማስክበር የተጀመሩ ጥረቶች በማጠናክር የህዝቡ ስጋት ከግምት ያስገባ እንቅስቃሴ በማድረግ እርምጃ እንደሚወስድ ጊዚያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል።
በመግለጫ የተከናወነውን መፍንቅለ መንግስት በማስጠንቀቂያ ጭምር ተቃውሞ ሌላ መግለጫ መሰራጨቱን ተከትሎ “በመግለጫዎች ምክንያት በትግራይ ውስጥ ማንኛውም የፀጥታ ችግር እና ስርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር አይፈቀድም” ሲል የትግራይ የፀጥታ ሃይሎች አስታውቋል። ይሁን እንጂ ለይቶ የትኛውንም ወገን አላወገዘም ወይም አልደገፈም።
የፀጥታ ሃይሎች ባወጡት አጭር የፅሁፍ መግለጫ ” መስከረም 27 ጊዚያዊ አስተዳደሩን የሚመለከቱ ሁለት ተፃራሪ መግለጫዎች መውጣታቸው ተከትሎ በህዝቡ ውስጥ የመረበሽ ስሜት ተፈጥሯል ” ሲል ህዝቡን ለማረጋጋት ሞክሯል።
” የትግራይን ሰላም እና ደህንነት እናረጋግጣለን ” የሚለው የፀጥታ ኃይሉ አጭር መግለጫ ” በተፃራሪ መግለጫዎች ምክንያት ስርአት አልበኝነት እንዲፈጠር አንፈቅድም ፤ ችግር ሲፈጠርም በዝምታ አንመለከትም ” በሚል የሚቋጭ ነው።
ከሳምንት በፊት አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉ የጸጥታ ተቋማት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚታዘዙና የአስተዳደሩ አካላት መሆናቸውን ጠሰው መናገራቸው አይዘነጋም። በትግራይ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች መኖራቸው፣ እነዚሁ ታጣቂዎች 500 በሚሆኑ የህጻናት መማሪያ ትምህርት ቤቶችን እንደ ካምፕ በመጠቀማችው ልጆች ትምህርት መማር እንዳልቻሉ ክቀናት በፊት የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ረዳይ ገ/ እግዚአብሄር ለመናኽሪያ ሬዲዮ መግለጻቸው ይታወሳል።
አሁን ላይ በክልሉ አጠቃላይ 2ሺ 492 ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የገለጹት ኃላፊው፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈጸመ በኋላ የመማር ማስተማር አገልግሎት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች 1ሺህ 835 ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ አሁንም 552 ትምህርት ቤቶቸ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን የገለጹት አቶ ረዳኢ፤ መደበኛ የመማር ማስተማር ተግባሩን እያከናወኑ ያሉ ትምህርት ቤቶችም ስራቸውን በአግባቡ እየተወጡት እንዳልሆነ ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ዓይነት ውጥንቅጥ ውስጥ ያለችው ትግራይ የስልጣን ሽኩቻ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል። ወደ ሻዕቢያ ባጋደሉና ጦርነት በቃ ባሉ ወገኖች መካከል እየታየ ያለው ግብግብ ወደ መንግስት ግልበጣ ማደጉን ተከትሎ መንግስት ዝምታን የመረጠበት አግባብ ሌላ ግራሞት የፈጠረ አካሄድ ሆኗል።
በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት መስከረም 27/2017 ዓ.ም ያወጣውን የመንግስታዊ ስልጣን ሹም ሽር የነቀፈው የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፤ “ቡድኑ ወደ ስርዓት አልበኝነት ለመሸጋገር የሚያስችለው ግልፅ መንግስታዊ ግልበጣ ማካሄዱን አውጇል” ሲል አስተዳደሩ ለሚሆነው ሁሉ ኃላፊውና ተጠያቂው ይህ ቡድን እንደሆነ ህዝብ እንዲያው ብሏል።
” ቡድኑ የመንግስት ስልጣን እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሚያዝ ጠፍቶት ሳይሆን አካሄዱ ከዛሬ መስከረም 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ ስርዓት አልበኝነት ለማስፈን ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ለማሳካት ሆን ብሎ ያደረገው ነው ” ሲል የጊዚያዊ አስተዳደሩ ስርዓተ አልበኝነት የማንገስ እቅድ እንዳለ አመልክቷል። ጊዚያዊ አስተዳደሩ ይህንን ስርዓት አልበኝነት በትእግስት እንደማያልፈውም አስታውቋል። ” የጥፋት ሃይል ” ሲል በገለፀው አካል ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጀምራል ብሏል።
“ህግ በማስከበሩ ሂደት ለሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት ጥፋት ብቸኛ ተጠያቂ ቡድኑና አመራሩ መሆናቸውን ለህዝባችን መግለፅ እንወዳለን ” በማለት አስተዳደሩ አስጠንቅቋል።
በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራ ትህነግ ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ የሚገኙባቸው በጉባኤ ያልተሳተፉ 13 የጊዚያዊ አስተዳደሩ አመራሮች በጉባኤ በተሳተፉ 14 አመራሮች ለመተካት የወሰነበትን መግለጫ ዛሬ መስከረም 27/2917 ዓ.ም ማሰራጨቱ ይታወሳል።
በቴሌግራም ይከተሉን እባክዎ https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk
በዶ/ር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚገኙባቸው 13 የጊዚያዊ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች በማንሳት በሌሎች 14 የድርጅቱ አባላት እንዲተኩ መወሰኑን ከገለፀ በኋላ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ” የመንግስት ግልበጣ ነው ” ያለው ተግባር የሚያርም ” ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ” ሲል ገልጿል።