በኦሮሚያ ሁለት አብይት ዜናዎች ውስጥ ውስጡን እየጦዙ ነው። አንደኛው በኦሮሚያ ክልል የሰላም ስምምነት ውይይት መጀመሩ ሲሆን ሁለተኛው የተከፈለው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር አንዱ ሌላውን ለጠቀላይ የመግጠሙ ጉዳይ ነው። በዚህ መካከል አቶ ሽመልስ የሰላም ንግግር ስለመኖሩ ፍንጭ መስጠታቸው የጠቅላዩን ጨዋታ መቃረብ የሚያሳይ እንደሆነ ተደርጎ እየተወሰደ ነው።
የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥና የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጃል ሰኚ ነጋሳን በግልጽ ጃል መሮን ጠቅሰው ድርጅቱ ህግ፣ ድንብና ተጠያቂነት የሌለው መሆኑን አስታውቀው መለያታቸውን በገሃድ ሲያስታውቁ ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው ጥሪ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት በሚል ስያሜ የሚጠራውና ጠብ መንጃ አንስቶ ጫካ የገባው ይህ አማጺ ኃይል በይፋ ባይወጣም በውስጡ የመከፍል ችግር እንዳለበት በተደጋጋሚ መረጃ ሲወጣ ነበር። መረጃውን ራሳቸው ነበር የሚያሰራጩት።
የሁለቱም ወገኖች አመራሮች በስልክ ያካሄዷቸውን መልዕክቶች ጨምሮ በጠብመንጃ ገጥመው መገዳደላቸው ሲዘገብ ነበር። በርካታ በውጭና በውስጥ ያሉ ደጋፊዊቻቸው ሳይቀር በሰሙት ዜና ተሰላችተው እየተለዩዋቸው፣ ጀርባቸውን እየሰጧቸው መሆኑ ለኦሮሚያ ብልጽግና መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ተደርጎም አስተያየት ሲሰጥ ከርሟል።
የቀድሞ ኦነግ መስራችና አንጋፋ አመራሮች “አሁን ላይ ኦሮሞ ጠብመንጃ ለኩሶ የሚጠይቀው ጥያቄና የሚያገኘው ልዩ ነገር የለም። ቀሪው ጨዋ የፖለቲካ ትግል ነው” በማለት በግልጽ ጠብ መንጃ አንስተው የሚተኩሱትን ወገኖች ባጋኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ሲተቹ ቆይተዋል። በተለይም በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደረግ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ እገታና ዝርፊያ መበራከቱ ህዝብ ሳይቀር ምሬት ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። ምሬቱም ህዝብ ባካሄዳቸው ስብሰባዎች በግልጽ የቀረበ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች አዛውንትና ህጻናት ሞፈርና ቀንበር ተሸክመው “የሰላም ያለህ” በሚል ተማጽኖ እንዲያሰሙ አድርጓቸዋል። እገታ፣ ግድያና ማፈናቀልን ዋና ህዝብን የማነሳሻ መንገድ አድርገው የሚጠቀሙበት እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።
ይህ በሆነበትና ህዝብ ቆዳ ለብሶ፣ ልጆቹን ሞፈርና ቀበር አሸክሞ አደባባይ በወጣ ማግስት ነው ጃል ሰኚ አደባባይ ወጥተው ድርጅቱ የድርጅት ቁመና የሌለው፣ በህግና ድንብ የማይመራ፣ አላማ ቢስና ተጠያቂነት የሚባል ወግ የማያውቀው መሆኑን የተናገሩት። ለመለየት ምክንያት የሆናቸውም ይህ የመርህ ጉዳይ እንደሆነ ያስታወቁት።
ጃል መሮ ልዩነት መኖሩ በስፋት ይሰማ በነበረበት ወቅት፣ ጦራቸው ወደ መካከል ኦሮሚያ መነቃነቁን፣ የወለጋንና አካባቢውን መልቀቃቸውን ያስታወቁት በጃል ሰኚ በኩል ያለው ቡድን በተለያዩ የግጭት አውዶች ያሳደረባቸውብ ተጽዕኖና የበላይነት መቋቋም ስላቃታቸው እንደሆነ ስለ ግጭቱ የሚያውቁ ይናገራሉ።
አሁን ላይ እንደሚሰማውና ዝግጅት ክፍላችን ባሰባሰበው መረጃ ኦሮሚያ ውስጥ የሚነቀሳቀሰው የጃል መሮ ኃይል በጃል ሰኚ ኃይል አማካይነት የሚጸዳበት አግባብ ሰፊ ነው። ጃል መሮ ጋር የቀሩት ኃይሎችም ቢሆኑ በየዕለቱ አንድም ለመግስት፣ አንድም ወደ ለጃል ሰኚ ወገኖች በመቀላቀል ላይ ናቸው። የተቀሩትም እየተበታተኑ ነው። ለዚህ ይመስላል የኦሮሚያ የጸጥታ ኃልፊ በኦሮሚያ የሚነቀሳቀሱ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች ቢበዛ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጸዱ አፋቸውን ሞልተው የተናገሩት።
የጃል ሰኚ ኃይል ምን ያህል ከመንግስት ኃይላትና መዋቅር ጋር እንደሚናበብ ባይታወቅም፣ ጃል ሰኚ ለጊዜው በምግስ በኩል በበጎ የሚታዩ ለመሆናቸው አቶ ሽመልስ በቂ ምስክር ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺመልስ አብዲሳ ኦክቶበር 9 በኦሮሚኛ ባሰራጩት ጽሁፍ በጃል ሸኚ የሚመራው ቡድን ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁን ” መልካምና የሚበረታታ እርምጃ ” ሲሉ ስም ጠርተው ነው ያደነቁት።
“ቃል በገባነው መሰረት” አሉ አቶ ሽመስል ” ቡድኑ በሚታመን ደረጃ፣ በቀናነት በተግባር ለዕርቅ ከተዘጋጀ መንግስታችን ለሰላም እጁን ዘርግቶ ለውይይት ይቀመጣል” ሲሉ አስታውቀዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን በበርካታ መረጃዎች የጃል መሮ ኃይል እንዳክተመለት የሚናገሩ በዝተዋል። ከውጭም ቢሆን ድጋፉ ቀንሷል። በዛንዚባር በተደረገው የሰላም ውይይት ላይ ተስማምቶ ሲያበቃ ባለቀ ሰዓት አሳቡን የቀየረው ጃል መሮ፣ ከዚያን ቀን ጀምሮ በርካታ እድሎች ከእጁ እንደወጡ እየተሰማ ነው። ጃል ስኚ ቀደም ሲል የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠብቀ እንደነበር መግለጹ በራሱ አንዱ የልዩነቱ መካረሪያ ነጥብ ስለመሆኑ ማሳይ ነው።
ጃል መሮ የሰላም ስምምነቱን ከጠንቀቀ በሁዋላ ባለቀ ሰዓት የገለበጠው ከአገር ቤትና ዋና ድጋፍ ከሚያደርጉ ክፍሎች ሆነ ተብሎ በስልክ የሰላም ሂደቱን የሽግግር መንግስት እስካልተቋቋመ ድረስ እንዳይቀበል በሚል ግፊት ተደርጎበት ስለመሆኑ በወቅቱ ተሰምቷል።
ከዚያን ጊዜ በሁዋላ በውስጥ በህዝብ፣ በድርጅት እንዲሁም በደጋፊዎች በካከል ድጋፍ እያጣ የሂደው የጃል መሮ ቡድን አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ግድ ሆኗል። አስተየት የሚሰጡ እንደሚሉት ጃል መሮ ከወደ ሰሜን ድጋፍ የሚያደርጉላቸውን አካላት በሙሉ ትተው ለኦሮሞ ህዝብ ሲሉ በይቅርታ ለመንግስትይ እጃቸውን መስጠት ይበጃቸዋል። ምክንያቱም ወደ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን መሄድ አይችሉም። ወደ ኬንያም ካመሩ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተላልፈው የሚሰጡበት ዕድል ሰፊ ነው። ይህን ካላደረጉ ከጃል ሰኚ እጅ አያመልጡም። ካመለጡም ከመንግስት ዓይን ሊሸሸጉ አይችሉም።
“መዋቅር ሲፈርስ መዋቅር ፈረሰ ነው” የሚሉ ብዙ ዝርዝር መናገር ባይፈልጉም ጃል ሰኚ ሁሉም መዋቅር እጁ ላይ ስላለ ከመንግስት ጋር ከመሰጠረ ምን ሊመጣ እንደሚችል ጃል መሮ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ስለሚረዳ፣ ህዝብም ነፍጥ ስለሰለቸው በዚህ እንዲያበቃ ባይ ናቸው።
በሌላ በኩል ኦሮሚያ ህዝቡ ለተቃዋሚ ድርጅቶች ቀደ ሲል የነበረው ስሜት አሁን ላይ የለም። በውጭ አገር በሚጠሩ ውይይቶች ላይ እንደቀድሞ መቀነት የሚፈቱ፣ ኪሳቸውን እየነሸጣቸው የሚገለብጡና በሰዓታት ሚሊዮን የሚሰበስቡ አይታዩም። በአሜሪካና በካናዳ የተለያዩ ስቴቶች ከደጋፊዎችቻቸው ጋር ለመነጋገር ወደ አሜሪካ ያመሩት ፕሮፌሰር መረራ ከኤድመንቶን በስተቀር ይህ ነው የሚባል ህዝብ ለስብሰባ እንዳልወጣ ካናዳ ሆነው የሰጡት ቃለ ምልልስ ያስረዳል።
ከኤርትራ በረሃና የአስመራ የግዞት ህይወት ወደ በአዲስ አበባ በክብር የገባው ኦነግ ” ትግል ማለት በሄዱበትና በገቡበት ሁሉ መነጣጠቅ ነው” ብሎ ያመነ ይመስል ሁለት ቦታ ተከፍሎ በመኖርና አለመኖር መካከል ከህዝብ ተነጥሎ ብቻውን እየተንፏቀቀ መሆኑን የሚናገሩ ” ማፈሪያዎች” ይሉዋቸዋል። “ሙክት ካኮላሸው” እንዲሉ ከሻዕቢያና ወያኔ ቁርበት ላይ መነሳት አቅቶት እዛው የሚንከባለለው ኦነግ፣ ዘመናዊ አሳብ ያላቸው፣ ወቅቱን የሚመጥኑ፣ በሰለጠነ ፖለቲካ የወደፊቱን ዓይተው የሚራመዱ አዳዲስ መሪዎች ማፍራት አቅቶት ” ለኦነግ ማኒፌስቶና መተዳደሪያ ደንብ ምን ያደርገለታል” በሚሉ ያረጡ ፖለቲከኞች መመራቱን አብዝተው ይኮንናል።
የኦሮሞን ምርጦች እነ ነዲ ገመዳን ከበሉ አካላት ጋር እየመሰጠሩ በሴራ ፖለቲካ የወለጋን ህዝብ ያስራቡ፣ በታሪኩ አይቶት የማያውቀውን የስንዴ እርዳታ ተቀባይ ያደረጉ፣ ፖለቲከኞች እውን ኦሮሞን ይመጥናሉ? በሚል የሚጠይቁ፣ ኦሮሚያ የነቁ ልጆች እንጂ ያረጀ እሳቤ ያላቸውን እንደማትፈልግ ይገልጻሉ። ገዢውን አካል የአሳብ የሚበልጡ ትንታግ ፖለቲከኞችን የሚመኙት እነዚህ ክፍሎች፣ በኦሮሚያ በተቃዋሚ ወገን ያሉ አዛውንት አመራሮች “በቃን” በማለት ለመንግስትም፣ ለትውልድም ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሙሉውን አስተያየት በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን።