ብሪክስ በብራዚል፣ሩሲያ፣ሕንድ፣ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት የተጀመረው ሌላኛው የዓለም ባለብዙ የዲፕሎማሲ መድረክ ንብረት ነው። በተለይ የአሜሪካ፣የካናዳ፣ የጃፓን፣የጀርመን፣የዩናይትድ ኪንግደም፣የፈረንሳይ እና የጣሊያን ጥምረት የሆነው ቡድን ሰባት (G7) በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ተፅዕኖ በመቀነስ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለማስፈን ያለመምና ፍትሃዊ ዓለምን እንደሚናፍቅ የሚነገርለት ነው።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እንደ አይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ ባሉት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የበለጠ ድምጽ እንዲኖራቸው ግፊት እያደረገ ያለጥምረትም ነው፡፡ ብሪክስ በቡድን 7 እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ከሚደገፉ የፋይናንስ ተቋማት የማይገኙ ድጋፎችን ለማመቻቸት የራሱ የሆነ የልማት ባንክም አቋቁሟል፡፡ ባንኩ ለብሪክስ አባል ሀገራት እና ከዚያ ባሻገር ላሉት አዳጊ ሀገራት ለዘላቂ ዕድገት የሚረዱ የልማት ፕሮጀክቶችን ይደግፋል፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት የህንድ እና የቻይና የመግዛት አቅም ከአጠቃላይ የቡድን 7 ሀገራት ልቋል፡፡ የብሪክስ ሀገራት ከ32 እስከ 40 አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ይህም የቡድን 7 ሀገራት የመግዛት አቅም ድርሻ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ይገለጸል፡፡ ከ40 በመቶ በላይ የዓለም ሕዝብ ቁጥርን የያዘው ብሪክስ ለዚህ የጥምረቱ የመግዛት አቅምን የሚጨምር ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፍትሃዊ ዓለምን ከማስረስ አንሳር የብሪክስ ህብረት ጠቀሜታ ላይ ትኩረት ያደርገ ንግግር ያደረጉት።
በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ተደማጭነት የሚጨምሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ጉባዔው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ በርካታ የዲፕሎማሲ ሥራዎች የተከናወኑበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በ16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።
በጉባዔው ላይ የኢኮኖሚ ትብብርን፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያን የተመለከቱ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በውሳኔዎቹ ላይ የራሷን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የጋራ አቋም ማንጸባረቅ መቻሏንም አስታውቀዋል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶች መከናወናቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁለትዮሽ ውይይቶቹ ሀገራቱ የኢትዮጵያን አቋም እና መሰረታዊ ጥቅም በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይትም ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውን ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም እና ፀጥታ መስክ በጋራ የመስራት ፍላጎት አሳይተዋል፦ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም እና ፀጥታ መስክ በጋራ የመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ በ16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የነበራትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጉባዔው ዋንኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የሰላም እና ፀጥታ ጉዳይ እንደሚጠቀስ በማብራሪያቸው አመልክተዋል።
በዓለም የተለያዩ ቀጣናዎች ያሉ ግጭቶ እና ውጥረቶች በሰላም እና ፀጥታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ እና ዜጎችን ለጉዳት እያደረጉ ስለመሆኑ በውይይቱ መነሳቱን ጠቅሰዋል።
አሁን እየመጣ ካለው የዲጂታል ዓለም ጋር በተገናኘ ያለው የመረጃ ስርቆት እንዲሁም የሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግሮች በዓለም ሰላም ላይ ተጽእኖ እንዳለው መገለጹንም አመልክተዋል።
የዓለም ሰላም እና ጸጥታን በማስጠበቅ ሂደት ሀገራት በዘርፉ ያሉ ተቋማት ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባቸው በጉባዔው ላይ መንጸባረቁንም ተናግረዋል።
የብሪክስ አባል አገራት የጸጥታ ተቋማቶቻቸውን ሪፎርም በማድረግ በዓለም ሰላም እና ፀጥታ የጋራ አስተዋጽኦ የማበርከት ጉዳይ አጽንኦት መሰጠቱን ነው አምባሳደር ሬድዋን የገለጹት።
በዋናነት የብሪክስ አባል አገራት የጋራ ጥቅሞቻቸው ላይ በማተኮር ያላቸውን ትብብር በማጎልበት የብሪክስን ውህደት እና ጥንካሬ ማሳደግ እንደሚገባቸውም እንዲሁ።
በተለያዩ ውይይቶች ላይ ኢትዮጵያ እያደገች እና እየተለወጠች መምጣቷን መነሳቱን ገልጸው፤ ካለችበት ቀጣና አንጻር በሰላም እና ጸጥታ የጎላ ሚና መጫወት እንደሚገባት የተለያዩ ሀገራት መግለጻቸውንም ተናግረዋል።
ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት በብሪክስ ጉባዔ ላይ የተሳተፉ ሀገራት በሰላም እና ጸጥታው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ያቀረበቻቸው ጉዳዮች ተቀባይነት ማግኘታቸው እና የሁለትዮሽ ትብብሮችን ለማጠናከር የተካሄዱ ውይይቶች ውጤታማ እንደነበሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አጋርን በማብዛት መርህ ከተለያዩ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ትብብርን ለማስፋት የሚያስችሉ ፍሬያማ ውይይቶች መካሄዳቸውን አምባሳደር ሬድዋን ጠቁመዋል።
የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያሏትን አቋሞች ይበልጥ ያንጸባረቀችበት ነው፦ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ያሏትን አቋሞች ይበልጥ ያንጸባረቀችበት እንደነበር የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ የነበራትን ተሳትፎ እና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በጉባኤው የተንጸባረቁ ሀሳቦች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች የሚያሳኩ ሆነው መገኘታቸውን ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ተናግረዋል።
ጉባኤው የአባል ሀገራቱ ፍላጎቶች፣ጥቅሞች እና አቋሞች የተጸባረቁበት እና የተበታተኑ ድምፆች ወደ አንድ የመጡበት እንደነበር ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዳጊ ሀገሮች ድምጻቸው የሚሰማበት፣ ኢ-ፍትሀዊ የሆነው የፋይናስ አቅርቦት፣ በጸጥታው ምክር ቤት ያለው ኢ-ፍትሃዊ ውክልና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለውጥ ለማድረግ የጋራ ፍላጎቶች የታዩበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን የግነኙነት መድረኮች ማካሄዳቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርኋ ከታሪክ፣ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ፣ ከህዝብ ብዛቷ እንዲሁም ከኢኮኖሚ እድገቷ ጋር የሚመጥን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷንና አቋሟን ማንጸባረቃቸውን አንስተዋል።
“በምግብ ዋስትና እራስን ለመቻል በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ በተለይም በስንዴ ዘርፍ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ሰፊ የስንዴ ምርት እንዲኖር እያደረገች ያለውን ጥረት እና ያስገኘውን ውጤት ለማስረዳት እድል አግኝታለች” ብለዋል ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ 40 ቢሊዮን ችግኖችን በመትከል እያካሄደች ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ ሌሎች ሀገራትም በተሞክሮነት የሚወስዱት መሆኑን በመድረኩ መጠቀሱን አመላክተዋል፡፡
ጥቂት እውነታዎች
የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የሕንድ፣ የቻይና እና የደቡብ አፍሪካን የመጀመሪያ ፊደል በመውሰድ ብሪክስ (BRICS) የሚለውን ስያሜ የያዘው ይህ ህብረት በቅርቡ የተቀላቀሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳውዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ አባል ሀገራቱ ናቸው። ብሪክስ በአባላቱ መካከል የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የልማት፣ የፋይናንስ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ትብብርን ማጠናከርን መዳረሻው አድርጓል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ሀገራትን የሚያካትተው ይህ ስብስብ በአኀዝ ሲገለፅ ይህን ይመስላል፡-
• ቱርክ እና ኢንዶኖዢያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ሌሎች ከ40 በላይ የሚሆኑ የዓለም ሀገራትም ጥምረቱን የመቀላቀል ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
• የብሪክስ አባል ሀገራት 41 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ የያዙ ናቸው።
• 35 በመቶ የሚሆነውን የዓለማችንን የሀገር ውስጥ ምርትን ሲሸፍኑ፤ ቻይና ቀዳሚውን ቦታ ትይዛለች።
• ሀገራቱ 26 በመቶ የሚሆነውን የምድራችንን ቦታ ሲይዙ፤ ሩሲያ 17.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ቦታ ትሸፍናለች።
• የመስራቾቹ ሀገራት የውጭ ምንዛሬ ክምችት 4.8 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን ቻይና 3.2 ትሪሊዮን ዶላር በመያዝ ቀዳሚዋ ናት።
• በዓለም አቀፍ ገበያ 20 በመቶ የሚሆን አስተዋፆ ያላቸው ሀገራቱ በገቢ እና ወጪ ንግድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ናቸው፤ በዚህ ረገድ የዓለማችን ከፍተኛዋ የምርት ላኪ ሀገር የሆነችው ቻይና ስብስቡን ትመራለች።
• ሀገራቱ 40 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የኃይል ሐብቶችን በመቆጣጠር፣ በኃይል ገበያ ዘርፍ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።
• አዲስ ልማት ባንክ በሚል ስያሜ እ.ኤ.አ በ2014 በ100 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ተቋቁሟል።
ባንኩ ከ90 በላይ የመሠረተ ልማት፣ የኢነርጂ፣ የትራንስፖርት እና ማህበራዊ ፕሮጀክቶች ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፋይናንስ አጽድቋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ የኢነርጂ ሐብቶች፣ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንቶች እንዲሁም ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ ያላቸው ናቸው።
ጥምረቱ እ.ኤ.አ በ2050 ከዓለም ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት 50 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል።