ኢራን ዛቻዋን ወደ ተግባር የለወጠችው « ኢራን ዉስጥ የእስራኤል ረጅም እጅ የማይደርስበት ሥፍራ የለም።ይሕ ለመላዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ የማይታበል ዕዉነት ነዉ።» በማለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመንግሥታቸዉን ጥንካሬና ዕቅድ ባስታወቁ በሁለተኛው ቀን ነው። የእስራኤል ጦር ጥቃቱን በአብዛኛው ዓየር ላይ ማምከኑን ቢገልጽም በተከታታይ በምስል ተደግፈው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢራን ያለማቋረጥ የላከቻቸው፣ እየላከችው ያለችው ሚሳይሎች ሲፈነዱ ታይተዋል።
የእስራኤል “Irone Dome” የሚባለው የመቃወሚያ ስርዓት የኢራን ሚሳኤሎችን መከላከል ያልቻለበት ሁኔታ መስተዋሉን ቢቢሲ ዘግቧል። ጥቃቱን እንደወትሮው ማምከን ያልቻለችው እስራኤል አቆላምጠው ሲጠሯቸው “ቡልዶዘሩ” በሚባሉት ኔታንያሁ አዛዥነት የምትወስደው እርምጃ ከወዲሁ ዓላምን እያነጋገረ ነው።
አሁን እስራኤል ላይ የደርሰውን የሚሳይል ጥቃት ለመበቀል እስራኤል “ምን ትጠቅማለች?” የሚሉት የሚጠይቁት “ኒዩክሌር ቦምብ ወይም የአሜሪካው F-35” የሚለውን እንጂ አጻፋው እንደማይቀር እርግጠኞች ናቸው። ይህንኑ ተከትሎ ዓለም አሁን ካለችበት የመጥፋት ስጋት ወደ እሳትነት እናድትቀየር የሰጉም አያሌ ናቸው።
ምንም ይባል ምን ባለፈዉ አርብ እስራኤል የገደለቻቸዉ የሒዝቡላሕ ዋና ፀሐፊ ሰይድ ሐሰን ነስረላሕን ሃዘን ተከትሎ ኢራን ዛቻዋን ወደ እውነት እንደምትቀይር እየለፍለፈች ባለበት ሰዓት እስራኤል ከግድያውም በላይ በሊባኖስ ሂዝቦላን ለማጥፋት የጀመረችውን ጥቃት ማፋፋሟ ኢራን ለዛቻዋ ተግባራዊነት እንድትፈጥን እንዳደረጋት ተመልክቷል።
ይህንኑ ተከትሎ ነው ቀጣይ ቀናት ለዓለም ሁሉ ጭንቅ የሆነ መረጃ ከፈረሱ አፍ የተሰማው። ኢራን እስራኤል ላይ ያዘነበቻቸው 180 በላይ ሚሳይሎች ተከትሎ ነው። ኔታንያሁ “ኢራን ስህተት ሰራች። ዋጋም ትከፍልበታለች” ማለታቸውን ቢቢሲ በደማቅ ቀለም ስለ ጥቃቱ በቀጥታ በሚያሰራጨው የጽሁፍ ዜናው የገለጸው።
እስራኤል “ኢራን ስህተት ሰራች ዋጋም ትከፍልበታለች” ያስባላት ጥቃት
ኢራን ወደ እስራኤል ከ180 የሚልቁ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን የስራኤል ጦር ይፋ አድርጓል። ጥቃቱ ባለፈው ሚያዚያ ኢራን በተመሳሳይ እስራኤል ላይ ካስወነጨፈችው110 የሚጠጉ የባላስቲክ ሚሳዔሎች እና 30 ክሩዝ ሚሳኤሎች ጋር ሲነጻጸር ይገዝፋል። የሚያዚያው ጥቃት እስራኤል በምትተማመንበት ማክሸፊያዋ አየር ላይ ስላመከነች ጥቃቱ ይህ ነው የሚባል ጉዳይ አለማድረሱ መዘገቡ አይዘነጋም።
አብዛኛዎቹ ሚሳዔሎች በእስራኤል የአየር መከላከያ ዘዴዎች አንዲከሽፉ መደረጉን የእስራኤል የደህንነት ባለስልጣን ቢገልጽም ወታደራዊ ካምፖች፣ ትምህርት ቤቶችና ሬስቶራንቶች ላይ ጥቃት መድረሱን በእየሩሳሌም የሚገኝ የቢቢሲ ዘጋቢ ጽፏል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ (አይአርጂሲ) ጠቅሰው መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎች በበኩላቸው ጥቃቱ ዘጠና በመቶ ዒላማውን አሳክቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች ጥቅም ላይ እንደዋለም ጠቅሰዋል። አንዳንድ ምንጮች ባሰራጩት ዜና ደግሞ ሦስት የእስራኤል ወታደራዊ ካምፖች የኢራን ጥቃት ዋንኛ ዒላማ ሆነዋል።
ቢቢሲ እንዳለው በዌስት ባንክ በምትገኘው ኢያሪኮ ከተማ በኢራን የሚሳዔል ጥቃት አንድ ሰው ሞቷል። ሰውየው የሞተው በሮኬት ስብርባሪዎች ተመትቶ ነው።ይህንኑ ያረጋገጡት የከተማውን አስተዳዳሪ ሁሴን ሃማኤልን ናቸው።
የእስራኤል ባለስልጣናት ማክሰኞ በደረሰው ጥቃት ምንም አይነት ከባድ ጉዳት እንዳልደረሰ ቢገልጹም፤ የአገሪቱ የሕክምና ባለሙያዎች ግን ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል። እንግዲህ ለጊዜው በኢራን ጥቃት የሞቱት ሰዎች ሁለት ብቻ ሲሆኑ ሌላው ዒላማውን ያሳካ የተባለው ጥቃት ያደረሰው ጉዳይ አልታወቀም።
የሚሳይል ጥቃት የደረሰበትን አንድ ትምህርት ቤት በምስል ያሳየው የቢቢሲ ዘገባ አስገራሚ ሲል ያስታወቀው አንድም ሰው አለመሞቱን ነው። እስራዔል ብሊባኖስ የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ ከሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
ታላላቅ የሚባሉት መንግስታት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ድጋፍ የሚሰጧት እስራኤል እንደወትሮው ሁሉ አገራቱ በይፋ ከእሥራኤል ጎን እንደሚቆሙ አስረግጠው እየተናገሩ ነው። በተቃራኒው ከኢራን ጎን በገሃድ እንቆማለን ያሉ አገራት የሉም። ይሁን እንጂ ከዓለም የኃይል አሰላለፍ አንጻር ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አይነት ነው።
እንግዲህ ለጊዜው ይህ የሚመስል ግርድፍ መረጃ እየወጣበት ያለውን የኢራን ጥቃት አስመልክቶ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ “ኢራን ትልቅ ስህተት በመሥራቷ ዋጋ ትከፍልበታለች” ሲሉ የተናገሩት። እሳቸው ብቻ ስይሆኑ የእስራኤል መከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ የኔትንያሁን ዛቻ አጽንተዋል። ዳንኤል ሃጋሪ “እቅዶች አሉን። በወሰንበት ቦታ እና ሰዓት እንተገብረዋለን” ሲሉ ድፍን ያለ መረጃ ሰጥተዋል። ኢራን በበኩልዋ እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ከወሰደች ቴህራን የምትሰጠው ምላሽ ይበልጥ አፍራሽ እና አጥፊ እንደሚሆን ገልጻለች። ከስር ቢቢሲ ለመረጃ ያተመውን ቅጂ እንዳለ አስፍረነዋል።
አይረን ዶም ሚሳዔሎችን አጨናግፏልን?
እስራኤል የተራቀቀ የአየር መከላከያ ዘዴዎችን ትጠቀማለች። ከእነዚህ ውስጥ በጣም የሚታወቀው አይረን ዶም ነው። በሐማስ እና በሄዝቦላ የሚተኮሱትን የአጭር ርቀት ሮኬቶችን ለማጨናገፍ በሚል የተሰራ ነው።
በሚያዝያ ወር ከኢራን የተሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል ጥቅም ላይ ውሏል። ሌሎች የአገሪቱ ያሏት “ላቅ ያሉ” የመከላከያ ሥርዓቶች የማክሰኞ ጥቃት ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ሳይውሉ አልቀሩም።
በአሜሪካ እና በእስራኤል በጋራ የሚመረተው የዳዊት ወንጭፍ (ዴቪድስ ስሊንግ) ከመካከለኛ እስከ ረዥም ርቀት የሚጓዙ ሮኬቶችን እንዲሁም የባለስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ይውላል። የረዥም ርቀት የባለስቲክ ሚሳዔሎች ለመከላከል ደግሞ እስራኤል አሮው 2 እና አሮው 3 የተባሉ ስርዓቶችን ትጠቀማለች።
የእስራኤል አጋሮች ምን አይነት ምላሽ ሰጡ?
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ ጥቃቱን “የከሸፈ እና ውጤታማ እንዳልሆነ” ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚገኙት የአሜሪካ ኃይሎች “እስራኤልን እንዲረዱ” እና የኢራንን ሚሳዔሎችን እንዲያጨናግፉ አዘዋል።
የፔንታገን ቃል አቀባይ በበኩላቸው የአሜሪካ የባሕር ኃይል ወደ እስራኤል በሚምዘገዘጉ የኢራን ሚሳዔሎች ላይ ወደ 12 የሚጠጉ ጸረ ሚሳኤሎችን መተኮሳቸውን ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ደግሞ “ይህንን የኢራን ድርጊት” በማውገዝ፤ ዩናይትድ ስቴትስ “በርካታ” ጸረ ሚሳዔሎችን መተኮሷን አረጋግጠዋል።
በዮርዳኖስ መዲና አማን ላይ የጸረ ሚሳዔል ጣልቃ ገብነት አንደነበር የሚያሳይ ምሥል እንደነበር ቢቢሲም አረጋግጧል። ኢራን በሚያዝያ ወር ባደረሰችው ጥቃት ዮርዳኖስ በርካታ ሚሳኤሎችን መትታ ጥላለች።
የዩናይትድ ኪንግደም ተዋጊ ጄቶች በሚያዝያ ወር እንዳደረጉት ሁሉ ማክሰኞ ዕለትም እስራኤልን በመደገፍ ተሳታፊ ነበሩ።
የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሌይ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ሳይሰጡ የብሪታንያ ጦር ማክሰኞ ማምሻውን “ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉንን ሚና ተጫውቷል” ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር አገራቸው ከእስራኤል ጎን መቆሟን እና “ራስን ለመከላከል መብቷ” ዕውቅና እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ፈረንሣይ እና ጃፓን ደግሞ የኢራንን ጥቃት በማውገዝ ድምጻቸውን በማሰማት ግጭቱ የበለጠ ተባብሶ እንዳይቀጥል ለሁሉም ወገኖች ጥሪ አቅርበዋል።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk