እሳቱን ለማጥፋት ከባድ ያደርገው የመንገዱ ስርቻ መሆንና በየዳርቻው የተቀመጡ ዕቃዎች ናቸው። እሳቱ ከቆርቆሮ ቤቶች ተነስቶ ወደ ህንጻ ማምራቱም ተመልክቷል። ባለሙያዎች እንዳሉት የእሳቱን መነሻ እምብርት ለይቶ ለማጥፋት ሰፈሩ እንቅፋት በመሆኑ አደጋውን አግዝፎታል። አየር መነገድ፣ ፌደራል ፖሊስና ውሃ አቅራቢ ተቋማት የተሳተፉበት ዘመቻ የተሳካ ቢሆንም ሌሊትን ሙሉ የቀረውን እሳት የመቃረምና የመቆጣጠር ስራው እንደማይቆም ተመልክቷል
በመርካቶ ሸማ ተራ አከባቢ በተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስራ መዋሉን ያስታወቁት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ። አደጋውን ቶሎ ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለዉን ጥረት አዳጋች ያደረገዉ የአካባቢው መንገድ የእሳት አደጋ መኪና በተሟላ ሁኔ ታ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነም አመልክተዋል።
“በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት እጅግ አዝነናል” ያሉት ከንቲባዋ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ከእሳት አደጋ እና ስጋት መከላከል እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ርብርብ መደረጉን አመልክተዋል። አያይዘውም በመንገድ ችግር ምክንያት ሄሊኮፕተር ለመጠቀም ጥረት መደረጉን አመልክተዋል። እሳቱን ለማጥፋት በተደረገውን ርብርብ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አስተላልፈዋል። ጥንቃቄ እንዲደረገም አሳስበዋል።
እሳቱ መጥፋቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍቅሬ ግዛው አሁናዊ ሁኔታውን በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጡ ” አሁን ላይ እሳቱን በቁጥጥራችን ስር አድርገናል ፤ የማጥፋትና የመልቀም ስራ ነው የሚቀረን ” ብለዋል።
” እጅግ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ እዚህ ላይ ባይገታ በጣም ብዙ ቦታ ፣ ሰፊ አካባቢዎች ላይ እሳቱ ደርሶ ህይወት ያጠፋ ነበር ፤ ከዚህ የበለጠ ሃብትም ይወድም ነበር ” ሲሉ የአደጋውን ትልቅነት ገልጸዋል።
” የአካባቢው አስቸጋሪትነት እሳቱን ለመቆጣጠር ረጅም ሰዓታት ወስዷል ” ያሉት ኮሚሽነሩ ” ከዚህ በኃላ ብዙ ጉዳት ያደርሳል ብለን አናስብም፤ ተቆጣጥረነዋል ማለት ይቻላል ” ብለዋል።
” እሳቱ ዳግም እንዳይቀጥል ቦታውን አዳሩን በሙሉ ተቆጣጥሮ ቅሪት ነገሮች ካሉ እነሱን እያጠፋን እንቀጥላለን ፤ ህብረተሰቡ እሳት ሊያቀጣጥሉ የሚችሉ ነገሮችን ያስወግድ ” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በስፍራው የሚገኙ እንዳሉት ከሆነ እሳቱ ከፈተኛ ውድመት አድርሷል። ከመንደር የወጣው እሳት ወደ ህንጻዎች መዛመቱንም አመልክተዋል።
እሳቱ ሲነሳ ምን ተደረገ
እሳቱ የተነሳው ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በመርካቶ ሸማ ተራ ነው። የአዲስ አበባ እሣትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍቅሬ ግዛው የእሳት አደጋው መነሳቱን በሰሙ ጊዜ አብዛኛዎቹ የእሳት ማጥፊያ መኪናዎች ርብርብ እንዲያደርጉ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
እሳቱን በርበር ለመቆጣጠር በስፍራ የደረሱት መኪናዎች ብቻቸውን እንደማያጠፉት የእሳቱ ባህሪ ከታየ በሁዋላ ታውቆ ደረሱ በኃላ ለሌሎች አጋዥ አካላት ማለትም አየር መንገድ፣ ፌዴራል ፖሊስና ሌሎች ከተማ ውስጥ ያሉ ውሃ አቅራቢ ተቋማት በሙሉ እንዲረባረቡ ተደርጎ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት መደረጉን በየሰዓቱ በሚሰጡት መረጃ አመልክተዋል።
ከንቲባዋ እንዳሉት ሁሉ ቦታው በሚፈለገው ደረጃ እሳቱን ለማጥፋት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል። “በሁሉም አቅጣጫ በኩል መኪና ገብቶ እሳቱን ለማጥፋት በጣም ፈትኖናል። በተለይ በመንገዱ በዙሪያ የሚቀመጡ እቃዎች ቶሎ ተገብቶ የእሳቱን መሰረት መምታት እንዳይቻል እንቅፋት ሆኗል።
“አካባቢው በቆርቆሮ የተያያዘ ነው። መንገዱ በጣም ጠባብ ነው። ገብተን ለማጥፋት ተቸግረናል። በአጋጣሚ ባለሱቆች፣ ነጋዴዎች ዘግተው ወጥተው ነበር። የቆሙ መኪኖችንም ለማስነሳት ችግር ሆኖብን ነበር” ሲሉ እሳቱን ለማጥፋት አስቸጋሪ ያደረገውን ምክንያት ተናግረዋል።