በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ቀውስ እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳዔል ጥቃት የከፈተች ሲሆን፣ እስራኤልም ከኢራን የሚተኮሱ ሚሳዔሎች ወደ ግዛቷ መግባታቸውን አስታውቃለች።
የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ኢርና ማክሰኞ አመሻሽ ላይ እንደዘገበው የኢራን ጦር ሠራዊት ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ መጀመሩን አረጋግጧል።
የእስራኤል የመከላከያ ኃይልም ከኢራን በኩል ወደ እስራኤል ሚሳዔሎች መወንጨፍ መጀመራቸውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኙ የቢቢሲ ዘጋቢዎች ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በአብዛኛው የእስራኤል ግዛቶች ውስጥ የሚሳዔል ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውሎች መሰማታቸውን አረጋግጠዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱ መጀመሩን ተከትሎ ለዜጎቹ ባስተላለፈው መልዕክት “የሚወጡ መመሪያዎችን በንቃት እንዲከታተሉ” አሳስቧል።
የኢራን የሚሳዔል ጥቃት መጀመሩን ተከትሎ፣ የእስራኤል ጦር የአገር ውስጥ ዕዝ በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ወደ መከላከያ ስፍራዎች እንዲገቡ የሚያዝ “ነፍስ አድን” ያለውን መመርያዎች በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አስተላልፏል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ ደግሞ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ከጥቃት የመሸሸጊያ ስፋራዎች በመግባት ተጨማሪ መመሪያዎችን እንዲጠባበቁ መክረዋል።
ቃል አቀባዩ ጨምረውም የእስራኤል የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓት “ሙሉ ለሙሉ በሥራ ላይ ሆኖ የሚተኮሱ ሚሳዔሎችን በመለየት እያከሸፈ” መሆኑን ተናግረዋል።
እስራኤላውያን “ንቁ ሆነው እንዲጠባበቁ” እና የሚሰጣቸውን የጥንቃቄ መመሪያዎችን እንዲከተሉ በመምከር፣ “እንዲህ ያለውን ጥቃት ለመቆጣጠር ብቁ ነን፤ የእስራኤል ዜጎችን ለመጠበቅም አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ በሚገኘው አጋሯ ሄዝቦላ ላይ ጥቃት ከከፈተች እና መሪውን ሐሳን ናስራላህን ጨምሮ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ከገደለች በኋላ መሪዎቿ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ሲዝቱ ቆይተዋል።
ማክሰኞ መስከረም 21/2017 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ለጊዜው መጠናቸው ያልታወቁ ሚሳዔሎች ከኢራን ወደ ተለያዩ የእስራኤል አካባቢዎች ተወንጭፈዋል።
የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን በቀረበው እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ የተሰጠ መግለጫ ላይ “በደርዘኖች” የሚቆጠሩ ሚሳዔሎች ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፣ እስራኤል የአጸፋ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ ደግሞ ሌላ ዙር ጥቃት እንደሚፈጽም አስጠንቅቋል።
አብዮታዊ ዘቡ ለአሁኑ ጥቃት ምክንያቱ ባለፈው ሐምሌ ቴህራን ውስጥ የተገደሉትን የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ እና ባለፈው አርብ ቤይሩት ውስጥ የተገደሉትን የሔዝቦላ መሪ ሐሰን ናስራላህን እንዲሁም በእስራኤል ሊባኖስ እና ፍልስጤም ውስጥ የተገደሉ ሰዎችን ሞት ለመበቀል የተወሰደ እርምጃ ነው ብሏል።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk
ዘገባው የቢቢሲ ነው