በደቡባዊ ሳዑዲ አረቢያ ናጅራን እስር ቤት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ሕይወታቸውን እንዲያተርፍ ተማጸኑ።
በእስር ቤቱ እስካሁን ሁለት ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ኃይሎች እንደተገደሉ እና ሌሎቹም ሞታቸውን እየተጠባበቁ መሆኑን የሞት የተፈረደባቸው ሁለት ስደተኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህ በእስር ላይ ያሉ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ 47 እንደሚሆኑ እነኚሁ ስደተኞች ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ አስረድተዋል።
“መቼ እንደምንሞት ባናውቅም ሞት ተፈርዶብናል። ዛሬ ልንገደል እንችላለን ወይም ነገ፤ አናውቅም። በጣም ፈርተናል። ለምን ሞት እንደተፈረደብኝ አላውቅም። ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ አልፈሃል ነው የተባልኩት። ከታሰርኩ አምስት ዓመት ከአምስት ወር ሆነኝ” ሲሉ እኚህ ስደተኛ ለቢቢሲ ያደረባቸውን ከፍተኛ ፍርሃት በስልክ ገልጸዋል።
የሞት ፍርድ ሲፈረድባቸው እውነት ይሆናል ብለው እንዳላሰቡ ለቢቢሲ የተናገሩት ኢትዮጵያዊው ስደተኛ እስረኛ ባለፈው ሳምንት ሁለት ኢትዮጵያውያን እስረኞች መገደላቸውን ተከትሎ “የእኛም ዕእጣ ፈንታ ሞት እንደሆነ አወቅን” ይላሉ።
“በሞት እና በሕይወት መካከል ነው ያለነው። ሌሎቹ ከተገደሉ በኋላ መተኛት አልቻልንም” ሲሉ ተናግረው “መንግሥታችን ጉዳዩን እንዲሰማልን እንፈልጋለን” ሲሉ ተማጽነዋል።
አክለውም በእስር ላይ ስላሉት ኢትዮጵያውያን ባሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው “ኤምባሲ መጥቶ ጠይቆን አያውቅም” ሲሉ ተናግረዋል።
በእስር ቤቱ እያሉ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በበኩላቸው “እዚህ እስር ቤት ያለው ስሜት አስጨናቂ ነው። ፈርተናል። ፖሊስ ወደ እስር ቤት ወረቀት ይዞ በመጣ ቁጥር የሚገደል ሰው ሊወስድ ነው ብለን እንፈራለን። ጠዋትም ማታም ሲመጡ እንደነግጣለን። አሁን ሞትን እየጠበቅን ነው። ምንም ማድረግ አንችልም። ሞታችን የማይቀር ነው” ሲሉ በከፍተኛ ሐዘን ተናግረዋል።
በርካታዎቹ ሞት የተፈረደባቸው ግለሰቦች ያለ ጥፋታቸው እንደሆነ የሚናገሩት ስደተኛ እስረኛው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ሕይወታቸውን እንዲታደጋት ተማጽነዋል።
ስደተኛው ኢትዮጵያ ወዳሉ ቤተሰቦቻቸው ደውለው የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከሳዑዲ መንግሥት ጋር እንዲነጋገሩ ጥያቄ እንዲያቀርቡ መናገራቸውን ገልጸዋል።
“ወደ አገር ቤት ደውለን ቤተሰቦቻችን መንግሥት ጋር ሄደው ከሳዑዲ መንግሥት ጋር እንዲያወሩ ጠይቀውልን ነበር። እንደሚነጋገሩ ቃል ሲገቡላቸው ቤተሰቦቻችን ተመለሱ። መፍትሄ እንደምናገኝ ለቤተሰቦቻን ቃል ቢገባላቸውም እኛ ግን መፍትሄ አላገኘንም” ብለዋል።
አክለውም “ብዙ ሰዎች ሞት ተፈርዶባቸዋል። እስካሁን ሁለቱ ተገድለዋል።. . . አደንዛዥ ዕጽ አስገብታችኋል ተብለው ነው የተከሰሱት። የኢትዮጵያ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ያድነን። የተከሰሱት በሐሰት ነው። ያለ ጥፋት ነው እየተገደሉ ያሉት” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የሞት ቅጣት መፈጸም እንደ አዲስ የተጀመረ እንደሆኑ የገለጹት ስደተኞቹ ከዚህ ቀደም የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የሚሆነው በሰው ግድያ ወንጀል የተከሰሱ ናቸው ይላሉ።
ቢቢሲ ኢትዮጵያውያኑ በምን ዓይነት ወንጀል ተከሰው ሞት እንደተፈረደባቸው ከእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ማረጋገጥ አልቻለም።
በሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ በእስር ቤቶች የሚፈጸሙ ግድያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ ስጋት እንደፈጠረባቸው የሰብዓዊ መብት ተቋማት በያዝነው ዓመት መስከረም ወር ላይ የካይሮ ኢንስቲትዩት ፎር ሂውማን ራይት ስተዲስ ድረ ገጽ ላይ በወጣ ጥሪ አስታውቆ ነበር።
ተቋማቱ በሳዑዲ በሚገኘው ታቡክ እስር ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ገልጸው ካለፈው ዓመት ጥር ጀምሮ ስምንት እስረኞች በሞት መቀጣታቸውን ገልጸዋል።
በመላው አገሪቱ ደግሞ 42 ሰዎች ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል ብሏል።
የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርገው ባሰፈሩት ጽሁፍ በዚሁ ወቅት ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሆነባቸው ግለሰቦች ዜግነታቸው ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅ፣ ከሶሪያ፣ ከሱዳን፣ ከየመን፣ ከናይጄሪያ ይገኙበታል ብለዋል።
ሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ የፈረደችባቸውን ግለሰቦች በይፋ ባታሳውቅም ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ዜግነት ያላቸው እስረኞች አሏት።
ሳዑዲ አረቢያ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸውን ግለሰቦች በሞት መቅጣት በአውሮፓውያኑ 2020 አግዳ ነበር። ከሁለት ዓመታት በፊትም ልዑል አልጋወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን የሞት ቅጣት ተፈጻሚነት በግድያ ወንጀል ብቻ እንዲወሰን አውጀው ነበር።
ሆኖም በዚያው ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ሳዑዲ ምንም ዓይነት ምክንያት ሳትሰጥ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ ማድረግ ጀምራለች። የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ እንዳሰፈሩት ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ የሞት ቅጣት 72 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሞት ፍርድ ተላልፎባቸው መገደላቸውን በተመለከተ መረጃ ካለ በሚል የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ቢቢሲ ቢጠይቅም መረጃ እንዳልደረሳቸው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያውያኑን ጉዳይ በተመለከተ ከማክሰኞ መስከረም 28/ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በስልክ እንዲሁም በጽሑፍ መልዕክት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
በነዳጅ ምርት የበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሠርቶ ለመቀየር መዳረሻ ከሚያደርጓቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል አንዷ ነች።
ይሁን እንጂ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በተለያየ የወቅት በአገሪቱ የሥራ እና የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም በሚል በርካታ ኢትዮጵያውያን እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ እና በማያፈናፍኑ እስር ቤቶች እንደሚቆዩ እንዲሁም ለተለያዩ የጤና እክሎች መጋለጣቸውን ቢቢሲ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
እስረኞቹ በቂ ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት በማይችሉበት እና በሕይወት ለመቆየት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እንደሚያዙ ይናገራሉ።
በማቆያ ማዕከላትም ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ከመቆያታቸው ባሻገር በጥበቃዎች ማሰቃየት እና ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው የመብት ተቆርቋሪው ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጹ የሚታወስ ነው።
በዚህም የማዕከሉ ጥበቃዎች በጎማ በተሸፈነ ብረት በፈጸሙባቸው ድብደባ ስደተኞች መሞታቸውንም ተመልክቷል።
በተጨማሪም በጦርነት እየታመሰች ካለችው የመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንን የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች መግደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂማን ራይትስ ዋች ባለፈው ዓመት ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ድረስ ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ የድንበር ጠባቂዎች ተገድለዋል ብሏል በሪፖርቱ።
ተቋሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደሆነም ባወጣው ዘርዘር ያለ ሪፖርት ጠቅሷል።
ሂውማን ራይትስ ዋች የጅምላ ግድያውን የያዘውን ሪፖርት ‘ዘይ ፋየርድ ኦን አስ ላይክ ሬይን’ [ጥይት እንደ ዝናብ በላያችን ላይ አዘነቡብን] የሚል ርዕስ ሰጥቶታል።
ሪፖርቱ የመን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የሳዑዲ ፖሊስ እና ወታደሮች ጥይት እና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጭምር በመጠቀም በጅምላ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደሏቸው የስደተኞችን ምስክርነት ይዟል።
በድንበር አካባቢ የበሰበሱ አስከሬኖች፣ በሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች የተያዙ ስደተኞች የትኛው እግራቸው በጥይት እንዲመታ እንዲመርጡ፣ እንዲሁም መትረየስ እና ሌሎች መሳሪያዎች በርካቶችን በጅምላ ለመግደል ጥቅም ላይ መዋላቸውን የሚያሳይ ዘርዘር ያለ ሪፖርት ነው ማዕከሉ ይዞት የወጣው።
የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ጠለቅ ያለ ሲሆን በርካታ የዓይን እማኞችን ጨምሮ፣ በርካታ ግድያዎች የተፈጸሙባቸውን ስፍራዎች የሚያሳዩ የሳተላይት ምሥሎች እንዲሁም ጊዜያዊ የቀብር ስፍራዎችን ይዟል።
ሪፖርቱ በተጨማሪም ስደተኞች በታጠቁ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ታጅበው ወደ ድንበር ከመወሰዳቸው በፊት ስለሚታሰሩበት የየመኑ ሞናቢህ የማቆያ ማዕከልም ይጠቅሳል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው