አዲስ አበባንና አካባቢዎቿን፣ የተለያስዩ የአገርሪቱ ከተሞችንና መንደሮች ላይ ተከሰተ የተባለው የመሬት ንዝረት መነሻ በሆነው ፈንታሌ የተነሳው የመሬት መንቀጥቀጥ የተወሰኑ ቤቶችን ማፍረሱን ሰመራ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ንዝረት ይከሰት እንደነበር ተጠቁሟል።
በአዋሽ ፈንታሌ እና አካባቢው ትናንት ምሽት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶችን ማፍረሱንና መሬት መሰንጠቁን ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው መረጃው ነው ያስታወቀው።

በፈንታሌ ተራራ ላይ ተከስቶ ንዝረቱ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ የተሰማው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከሁለት ሳምንታት በላይ በተለያየ አጋጣሚ መከሰቱን ባለሞያዎቹ ገልፀዋል።
ከሰሞኑ የሚስተዋለው የመሬት መንቀጥቀጥ በአዋሽ ፈንታሌ እና አካባቢው ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል ያለው ዩኒቨርሲቲው፣ አደጋው በተከሰተበት ሳቡሬ ቀበሌ ተገኝቶ መረጃ የመሰብሰብና ለማህበረሰቡ ጥንቃቄ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራቱንም ገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ጂኦሎጂስቶች ነዋሪዎች ከፈንታሌ ኮረብታማ ቦታ እና ከከሰም ግድብ ርቀው እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። እሑድ ምሽት የተከሰተውና በአዲስ አበባ በነዋሪዎች ላይ መደናገጥ የፈጠረው የመሬት መንቀጥጠጥ ለ18 ሴኮንድ የቆየ እንደነበረ ባለሞያዎች ተናግረዋል።
በአዲስ አበባና አካባቢው የመሬት ንዝረት የተከሰተባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ነዋሪዎች በምስል አስደግፈው የገለጿቸው አካባቢዎች፣ ጎጃም በረንዳ ፣ ሸጎሌ ፣ ሰሜን ማዘጋጃ ፣ አምባሳደር ፣ አዲሱ ገበያ ፣ ወለቴ፣ ጀሞ ፣ አያት፣ ገላን ፣ አራብሳ፣ ልደታ፣ ሰሚትኮዬ ፈጬ ፣አለም ባንክን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ይህ እስከታተመ ድረስ ደረሰ የተባለ አደጋ ወይም ጉዳት የለም።
ከአዲስ አበባ ውጭ በከሚሴ፣ አዋሽ 40ሐረር ፣ አሰበ ተፈሪ ፣ አዳማ ፣ ደብረ ብርሃን የመሬት ንዝረት መሰማቱ ታውቋል።
በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች ወጥተዋል። ይህ ከተገለጸ በሁዋላ ዛሬ ማምሻውን ከምሽቱ 2ሰዓት ግድም በተከሰተው ንዝረት ነዋሪዎችም ተረብሸው ከቤታቸው መውጣታቸው ተመልክቷል። ንዝረቱ ለአጭር ቅጽበት የደረሰ በመሆኑ ነዋሪዎች ወዲያው መረጋጋታቸውን ገልጸዋል።
የቤታቸው አምፑል፣ መጋረጃ፣ ቁሳቁሶች መርገፍገፋቸውን ወይም ሲወዛወዙ ማየታቸውን በረካቶች መስክረዋል። ባለሙያዎችን ጠቅሰው የመንግስት መገናኛዎች እንደዘገቡት ከሆነ የተሰማው የመሬት መንቀጥቀጥ በንዝረት ደረጃ የሚገለስ ነው። የንዝረቱ ፈንታሌ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የፈጠረው ንዝረት ድንጋጤ ቢፈጥርም በሚታወቅና አግባብ በሆነ ተቋም ይፋ የሆነ ጉዳት አልተመዘገበም።
ትናንት በአዋሽ መተሀራ ፈንታሌ ተራራ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ መድረሱን ያመልከቱት ባለሙያዎች፣ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 9 ሆኖ መመዝገቡን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ የተሰማው ይህ የመሬት ንዝረት ለከተማዋ ነዋሪዎች አስጊ አለመሆኑ ባለሙያው ለኢቢሲ ገልጸዋል። ባለፉት ቀናትም አነስተኛ መጠን ያላቸው የመሬት ንዝረቶች ሲያጋጥሙ መቆየታቸውን ባለሙያዎቹ አመልክተዋል፣
ዜጎች የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያጋጥምበት ወቅት ባለመደናገጥ ራሳቸውን ከአደጋ ሊጠብቁ ስለሚችሉባቸው መንገዶች መረጃ ሊይዙ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አገልግሎት ምክር ሰጥቷል።
ይህ ከሆነ በሁዋላ ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያጋጥም ጊዜ መደረግ የሚገባቸዉ የጥንቃቄ ርምጃዎች በዝርዝር እንዲያውቁ መረጃ ተላልፏል።
- ከቤት ውጭ ከሆኑ – ከዛፎች፣ ከሕንፃዎች፣ ከኤሌትሪክ ምሶሶዎችና ሌሎች ወድቀው ጉዳት ከሚያደርሱ መራቅ፣
- በቤት ውስጥ ከሆኑ – በበር መቃኖች፣ በኮርነሮችና ኮሪደሮች ተጠግቶ ማሳለፍ፣
- ከእሳት ምድጃዎች፣ ከተሰቀሉ ፍሬሞችና የግድግዳ ጌጦችና ከመስኮት አካባቢ መራቅ፣
- ከሕንጻዎች ለመውጣት አለመሞከር፣ ሊፍት በፍፁም አለመጠቀም፤ ከደረጃዎች አካባቢ መራቅ፣
- መኪና እያሽከረከሩ ከሆኑ- የኤሌትሪክ መተላለፊያ ምሶሶዎችን፣ ዛፎችና ሽቦዎች አካባቢ አለመቆም፣
- የኤሌትሪክ መስመር ምሶሶዎችና ሽቦዎች ተሽርካሪው ላይ ከወደቁ ከመኪናው ለመውጣት አለመሞከር፣
- ገላጣ ወደሆነ አካባቢ መኪናን መቆም እንደሚገባ ከአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ጠቅሶ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
ለእሳትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች 939 የስል መስመርን በመጠቀም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝም ተገልጿል።
የማህበራዊ ሚዲያዎች ይህንኑ የጥንቃቄ መልዕክት እንዲያሰራጩ ተመክሯል። ከመጯጯህ ይልቅ የባለሙያን ምክር ማጋራት ጠቃሚ መሆኑንን የተረዱ ይህንኑ እያደረጉ ነው። አሁን ላይ ከተማዋ ተረጋግታ ህዝቡም ወደ ቤቱ ገብቶ ህይወት እንደቀድሞው እየቀጠለ መሆኑ ታውቋል።