ግብጽ ስትፈነጭበት የነበረውና ኢትዮጵያ ዘጠና ከመቶ ባለቤት በሆነችበት የአባይ ውሃ ምንም ዓይነት ልማት ማከናወን እንዳትችል ቀስፎ የያዘው ህግ ግብአተ መሬት መፈጸሙ ታወጀ። የአባይ ተፋሰስ ሃገራት አዲሱ ማዕቀፍ በ14.10.2010 አስፋው ዲንጋሞ ፊርማቸውን አኖሩበት። ይህ አዲሱ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ መፈረም ከጀመረ ከአስር ዓመት በኋላ ደቡብ ሱዳን ፊርማዋን ስታኖር ነበር የግብጽ የማዕቀፉ ንግስና በይፋ ስቅላት የተፈረደበት። “የዓባይን ውኃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መንገድ ለመጠቀም የተደረገው ረጅም ጉዞ ፍጻሜ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በኤክስ ገጻቸው የስምምነቱን ፋይዳ አስታውቀዋል። ያልፈረሙ ጥቂት አገሮች ታዛቢዋ ኤርትራ፣ ግብጽና ኮንጎን ወደ ፍትሃዊው አዲስ ዘመን እንዲቀላቀሉ ጋብዘዋል።

ለዚህ ነው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ “ታሪክ ተሰራ፣ እንኳን ደስ አለን” ሲሉ በስንበት ማለዳ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ድል ያበሰሩት። ኢትዮጵያን ተከትለው ኡጋንዳ፣ ሩዋናዳ፣ ታንዛንያ፣ ኬንያ፣ብሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን ፊርማቸውን ያኖሩበት ሰነድ የ”አዲስ ዘመን” ስምምነት በሚል ተወድሷል።
ከ1929 ጀምሮ በንብረቷ ባይተዋር የተደረገችበትና ግብጽ ምንም በማታዋጣበት የአባይ ውሃ ላይ ተክላ የኖረችውን ሌሎችን አፍኖ የያዘ hydro-hegemonic projection ስምምነት በይፋ መቀበሩ ሲበሰር ጉዳዩ ለገባቸው፣ ቁጭቱ ሲነዛራቸው ለኖረ፣ ህመሙ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተንከባለለ መኖሩ ላስጨነቃቸው ወዘተ አገር ወዳዶች ስሜቱ ልዩ ሆኗል። በአንዳንድ መድረክ ብሄራዊ በዓል ሊሆን እነደሚገባውም እየተጠቆመ ነው። በተጻራሪው ለግብጾቹ የመርዶ መርዶ ሆኖባቸዋል።
የአስመራው አምባገነን ፕሬቪዳንት ኢሳያስ እራፊ ጨርቅ አንጠልጥለው በራሳቸው መኖሪያ እንደ እንግዳ ዳር ተቀምጠው በሚታዩበት ምስል ታጅበው ኢትዮጵያ ላይ አብረው መዶለታቸውን ይፋ ባደረጉ ማግስት ኢትዮጵያ ይህን ድል ማብሰሯ ድርብ ኩራት ሆኗል። ይህን ድል “በአል ሲሲ የተደራጀው ቡትቶ ጥምረት ላይ ያረፈ የመጀመሪያው ስትራቴጂካዊ ጥፊ ነው” ሲሉ አቶ ኦሉማ ወዳጆ በፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈዋል።
“የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ አስታወቁ” የሚለው ዜና በመንግስት መገናኛዎች ይፋ ሲሆን፣ አገራቸውን ከልብ በሚወዱ የግብጽ ሚዲያዎች ግብጽ ላይ ርዕደ መሬት የደረሰ ያህል በድንጋጤ ሲያስተጋቡት፣ በኢትዮጵያዊነት ስም የሚምሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ተላቶች ተላላኪ የሆኑት ባለ ሚዲያዎች ደግሞ ዜናውን በፖለቲካ ሰፍረው ሊያሳንሱት ሲውተርተሩ ታይቷል።

እነዚህ ሃፍረት ቀለባቸው የሆነ የባንዳ ሚዲያዎችና የባንዳዎች አሽከሮች እንዳሰቡት ሳይሆን ኢትዮጵያ በተለያዩ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎችና ተቋማት በቅብብል ትግሏን በድል ደምድማለች።
ሰነዱ አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ አግባብ ላላቸው ተቋማት ቀርቧል። ደቡብ ሱዳንም የናይል ገባር በሆነው ወንዝ ላይ ታላቅ ግድብ ለመስራት የስምምነት ውላቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የለኮሰችው፣ ኃይለማሪያም ያስቀጠሉትና አብይ አሕመድ መልክና ውበት፣ እንዲሁም የተግባር እሴት አላብሰው ህያው ያደረጉት የአባይ ግድብ ለጎረቤቶች ዓይን ከፋች ሆኖ ግብጽን ጣር ውስጥ ከቷታል።
የናይል የትበብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈጻሚነት አሰመልክቶ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት ተሸጋግሯል።
የዛሬው ቀን በናይል ተፋሰስ ታሪክ ልዩ መሆኑን አንስተው “መላው የኢትዮጵያ ፣ የተፋሰሱ ሀገራት መንግሥታትና ሕዝብ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡ ለዚህ ስምምነት በተለያየ መንገድ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
የናይል የትብብር ስምምነት ተፈጻሚ መሆን የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንን መመስረት እንደሚስችል ጠቅሰው ኮሚሽኑ ለሁሉም ተጠቃሚነት የናይል ወንዝን የማስተዳደርና የመጠበቅ ኃላፊነት ይወስዳል፤የትብብሩም የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሕግ ማዕቀፍ፣ የናይልን ወንዝ ለሁላችንም ጥቅም ለማዋል የጋራ ቁርጠኝነታችን ምስክር እንዲሁም የውኃ ሀብቱን በእኩልነትና ፍትሐዊነት የመጠቀም መብት ማረጋገጫ የሚሆን ስምምነት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የናይል የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ የነበረውን ኢ-ፍትሐዊነት ያስተካክላል፤ የሁሉንም የናይል ሀገሮች የጋራ ሀብት ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
በተጨማሪም ስምምነቱ ለሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ሕጋዊ መብት ዕውቅና እንደሚሰጥ ገልጸው÷ ሁላችንንም ለውኃው ፍትሐዊ ክፍፍልና ለዘላቂ አጠቃቀም ተገዥ ያደርገናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
እያንዳንዱ ሀገር የሌላውን መብት ሳይጋፋ በጋራ የሚያድግበትና የሚበለጽግበት የሁሉንም መጻኢ ተስፋ እንደሚወክልም አመላክተዋል፡፡
ዘላቂ ልማት የትብብር ስምምነቱ ማዕከል ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ የናይልን የውኃ ሀብት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ከእኛ በኋላ ለሚመጡት ትውልዶችም እንዲሆን አድርገን መጠቀም የሚያስችል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ስምምነቱ ናይልንና ከባቢውን እንድንጠብቀው፣ ውኃውን የወደፊቱን ተጠቃሚ በማይጎዳ መልኩ እንድንጠቀም ያስገድደናል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
ሁሉም የተፋሰሱ ሀገሮች ስምምነቱን እንዲቀላቀሉትና መርሆዎቹን በታማኝነት እንዲፈጽሙ ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስትሩ÷ የናይል ወንዝ የተስፋ ምንጭ የሚሆንበትን፣ ተግዳሮቶችን በጋራ የምናቃልልበትና ለራሳችንና ለመጪው ትውልድ የተሻለ ዓለም የምንፈጥርበትን መጻኢ ጊዜ ለመገንባት በጋራ እንሥራ ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በትብብር ጉዟቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ አመሥግነው ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ በምናደርገው ጉዞም አጋርነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ትሰሰር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለታተል፡፡
“የዓባይን ውኃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መንገድ ለመጠቀም የተደረገው ረጅም ጉዞ ፍጻሜ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የድሉን ትርጉም በግል የኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ ወንዙን በፍትሃዊ ለመጠቀም የተደረገው የረጅም ጊዜ ትግል ለፍሬ የበቃበት መኾኑን አስረድተዋል። ስምምነቱ ወደ ትግበራ መሻጋገሩ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ በጋራ የውኃ ሃብቶች አስተዳደር እና አጠቃቀም ላይ ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነ አመልክተዋል። “ዕለቱ በዓባይ ተፋሰስ ላይ እውነተኛ ትብብር ለመፍጠር ያደረግነው የጋራ ጥረት ታሪካዊ ምዕራፍ ኾኖ ይታወሳልም” ነው ያሉት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት ለሰሩ የስምምነቱ አባል ሀገራት “እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡ ስምምነቱን ያልፈረሙ ሀገራትም ለፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም በመገዛት “የናይል ቤተሰብን“ እንዲቀለቀሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡