“በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ወደ መሬት ለመውጣት ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቅልጥ አለት አሁን ረገብ ብሎ ወደ ታች መውረድ ጀምሯል”
በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በመሬት ውስጥ የተፈጠረው የቅልጥ አለት እንቅስቃሴ የተለያየ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እና በሩቅ ቦታዎች ደግሞ የመሬት ንዝረት እንዲፈጠር ማድረጉ ይታወሳል።
የመሬት መንቀጥቀጡ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የመሬት ንዝረት አስከትሎም ነበር።
በኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ለ22 ቀናት ወደ መሬት ለመውጣት ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቅልጥ አለት የመወጠር ሁኔታ አሁን ረገብ ብሏል፤ አሁን ባለን መረጃ ቅልጥ አለቱ ወደታች እየወረደ ነው ብለዋል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂዮ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሌዊ (ዶ/ር) በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር።
በዚህም ምክንያት ባለፉት 2 ቀናት የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ቀደም ሲል የነበረው ስጋት ባለፉት ቀናት ቀንሷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምንገኝ እንደመሆናችን ስጋቱ ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ስለ መሬት መንቀጥቀጡ በማህበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ ነው ያሉት ዶ/ር ኤሊያስ፤ ሚዲያው ሀሰተኛ መረጃ ከማሰራጨት ይልቅ በጥናት የተረጋገጠ እና ትክክለኛ መረጃ ብቻ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ስምጥ ሸለቆ እና አካባቢው በተፈጥሮ ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ መሆኑ የማይቀየር ተፈጥሯዊ እውነታ ነው፤ እንደ ሀገር፣ እንደ ህዝብ የራሳችንን ጥንቃቄና ዝግጀት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ማንኛውም የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂዮ ፊዝክስ፣ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ እንደሚያደርግ በመጠቆም ህብረተሰቡም ይህንኑ እንዲከታተል አሳስበዋል።
Via ETV