ከየትኛውም የሀገራችን አቅጣጫ ሊከፈቱ የሚችሉ ጥቃቶች ለመከላከል የሚችልና የሚመጡ አደጋዎችን ለመቀልበስ የሚያስችል የአየር ሀይል ተገንብቷል ሲሉ
የኢፌዴሪ አየር ሀይል አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ተናግረዋል።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ አየር ሀይል ከነበረበት ውድቀት ለማንሳት በፀጥታ ዘርፉ የተሰሩት ሪፎርሞች ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረው፣ በፕሮፌሽናል የሰው ሀይል ግንባታ ፣ በትጥቅና በውጊያ መሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልፀዋል።
ለታላቅ ሀገር የሚመጥን ታላቅ የአየር ሀይል የመገንባት ጥረታችን ዕውን ለማድረግና የነገውን ጠንካራ የአየር ሀይል ለመገንባት ከምልመላ ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝና ፕሮፌሽናል ፣ ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ ፤ ከፖለቲካና ሌሎች ተፅዕኖዎች ነፃ የሆነ ፤ ኢትዮጵያን የሚመስል ስብጥር ያለው አመራርና ባለሙያ እየተገነባ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ያሉትን የአየር ሀይል ትጥቆች ከማሻሻል ባለፈ ዓለም የደረሰባቸው ዘመናዊ ትጥቆችን እየታጠቅን እንገኛለን ያሉት አዛዡ በቅርቡ ከአፍሪካ ጠንካራ አየር ሀይሎች ጎን ለመሠለፍ የሚያስችል ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሀገራችን ላይ የከፈቷቸው የስነልቦና ውጊያዎች መኖራቸውና ለማስፈራራት ከመሞከር ባለፈ የሚያመጡት ውጤት አለመኖሩን ገልፀው ፤ ተላላኪዎችን እየደገፉ ያሉ ጠላቶች ጥቃት ለመክፈት ከሞከሩ እንደአመጣጣቸው ለመመለስ በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንገኛለንም ብለዋል።
ሀገራችንንና የአየር ሀይሉን ስም ለማጠልሸት በፅንፈኞች የማህበራዊ ሚዲያዎች የተከፈቱት ዘመቻዎች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን የገለፁት አዛዡ በግምት የሚደረግ ምንም ነገር አለመኖሩንና ዘመኑ በፈጠረው ቴክኖሎጂ ተፈላጊ ዒላማን በተፈለገው ቦታና ጊዜ ለይቶ እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል ነው የገለፁት።
ሆን ተብሎ ሲቪሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ለማስመሰል የሚደረጉ የውሸት የሚዲያ ዘመቻዎች በዘርፉ ዕውቀቱ የሌላቸውን ለማሳሳትና ሽንፈታቸውን ለመደበቅ መሆኑን ገልፀው ሲቪሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከመደረጉም ባለፈ ዒላማዎችን በቁጥር ጭምር መለየት ይቻላልም ነው ያሉት።
በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከሁሉም ሀገራዊ የፀጥታ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝና ለጋራ ተልዕኮ በጋራ የመስራት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልፀዋል።
ለመከላከያ ሠራዊቱ ለአየር ሀይሉና ለሌሎች የፀጥታ ዘርፎች ውጤታማነት የክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑና የተሻሻለው ፖሊሲ ፣ ስትራቴጂና የሠራዊቱ የግንባታ መመሪያ ተቋማትና አባሉ ከፖለቲካ ወገንተኛነት በመውጣት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉና ሙያዊ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
ለሀገር መስዋዕትነት ከፍለው ሀገርን ያቆዩና ታሪክ የሰሩ ጀግኖች ክብር ይገባቸዋል ያሉት አዛዡ በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙና ተቋሙን ካገለገሉ ጀግኖች ጋር አብሮ በመስራት ሙያተኞች ተቀጥረው እንዲያገለግሉ ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች አቅም ያነሳቸውን በተቻለ መጠን እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ዘጋቢ ብዙአየሁ ተሾመ የኢፌዴሪ መከላከያ