– የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ድርቅን ለመቋቋም በተሰራው ሥራ በራሳችን አቅም በምግብ እህል እራስን ለመቻል እንደሚቻል በተግባር የተረጋገጠበት ነው ሲሉ የቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱሰላም ዋሪዮ ተናገሩ።
በዞኑ ተከስቶ የነበረው ድርቅ በእንስሳት ሃብት ላይ ጉዳት ያደረሰና ህዝቡን ለተረጂነት የዳረገ እንደነበር ይታወሳል።
በዞኑ የተከናወኑ የግብርና የለውጥ ስራዎች አሁን ላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል፡፡
ከደረሰው ጉዳት ትምህርት በመውሰድ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የሚያስችል ሥራ መሰራቱን ገልጸው አሁን ላይ የቦረና ከብት ዝርያ እንዳይጠፋ በተለዩ ማቆያ ጣቢያዎች የነበሩ ዝርያዎችን መልሶ ማባዛት መቻሉን ጠቁመዋል።
መንግስት ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም በገነባቸው የፊና የውሃ ግድብ ፕሮጀክቶች አማካይነት አርብቶ አደር የነበረው ማህበረሰብ ወደ አርሶ አደርነት መቀየሩን ገልጸዋል።
የዞኑ ማህበረሰብ በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ ለገበያ የሚውሉ ምርቶችን ማቅረብ መቻሉንም አስታውቀዋል።
በዞኑ ከ128 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች መሸፈኑንና ከዚህም ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።
በዞኑ ስንዴ ሲረዳ የነበረው ህዝብ ስንዴ አምርቶ ምርቱን በኮምባይነር ሰብስቧል ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ መንግስት ለህዝቡ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን በማቅረብ ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
በአርብቶ አደር አካባቢ ያሉ ጸጋዎችን በመጠቀም ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ ታሪኩ አስጨናቂ በበኩላቸው በዞኑ ድርቅን ለመቋቋም በተሰራው ስራ የእንስሳት መኖን በአካባቢው በማምረት በመጋዘኖች እየተጠራቀመ መሆኑን ገልጸዋል።
ተከስቶ በነበረው ድርቅ የቦረና ከብት ዝርያ እንዳይጠፋ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን አስታውሰዋል።
በቦረና ድርቅን ታሪክ ለማድረግ የተሰራው ስራ የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ ሀገር መቀየር እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አካባቢውን በጎበኙበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።
መስክረም 22 ቀን 2017 ዓም ENA
