የትግራይ ሲቪል ማህበራት ህብረት በቀጣይ ሳምንት በትግራይ ክልል በውዝግብ ውስጥ የሚገኙት የህወሓት እና የጊዚያዊ አስተዳደር ቡድኖችን ሊያወያይ መሆኑን ገልጿል፡፡ህብረቱ በፖለቲከኞቹ መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት በምሁራን ጥናቶች እያቀረበ ዉይይት ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት የህብረቱ ፕሮግራም ማናጀር አቶ በሪሁ ገብረመድህን፤ “ይሁን እንጂ ይህ መፍትሄ ይዞልን ሊመጣ አልቻለም” ብለዋል፡፡
“በዚህም ምክንያት አጀንዳዎችን በጋራ በመቅረፅ፣ በሁለቱም ወገን ያሉ አካላት በማገናኘትና ችግሩን እንዲያቀርቡ በማድረግ ህዝቡ ሳይጎዳ ችግሩን ለመፍታትና ምን መደረግ አለበት የሚለው ጉዳይ ላይ እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡በዚህም በቀጣይ ሳምንታት ሁለቱንም ወገኖች በማሰባሰብ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ኃላፊዉ ተናግረዋል፡፡
“በፖለቲከኞቹ መካካል በአቋም ደረጃ ተመሳሳይ ነገር አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የስልጣን ፍላጎት ይስተዋላል” ያሉት አቶ በሪሁ፤ ይሁን እንጂ ሁለቱም ለሰላም ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡”ነገር ግን በተግባር እታየ ያለው ሁኔታና በየስብሰባው ያለው ሁኔታ በክልሉ ውጥረት እንዲፈጠር እያደረገ ነው” ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡በሌላ በኩል በቅርቡ ቅንርጫፉን በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የከፈተው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) በትግራይ ያለውን ፖለቲካዊ ውዝግብ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡
የፓርቲው የአዲስ አበባ ኮሚቴ አባልና በመቀሌ የተከፈተውን ቅርጫፍ በማደራጀት የታሳተፉት አቶ ይሳቅ ወልዳይ፤ በህወሓት መካከል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ውጥረት የፓርቲው ችግር መሆኑን ያነሳሉ፡፡ይሁን እንጂ በፓርቲው ብቻ የሚቆም ጉዳይ ባለመሆኑ፤ በክልሉ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ኢህአፓ እንደ ፓርቲ ሁለቱም መካረር ዉስጥ መግባታቸዉ ተገቢ ነው ብሎ እንደማያምን የገለጹ ሲሆን፤ ህዝቡ ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ ከዚህ ወዲህ ወደ ጦርነት የሚወስድ ማንኛውንም ሁኔታ እንደማይፈቅድ የገለጹት አቶ ወልዳይ፤ “ሁለቱም አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር እንዲያደርጉ” ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡በተያያዘ ዜና የህወሓትን ህጋዊነትን ለማስመለስ ከፌደራል መንግሥት እና ከአፍሪካ ህብረት ፓነል ጋር የሚወያይ ልዑክ እንደ አዲስ እንደሚደራጅ በህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ህወሓት በዛሬው ዕለት ገልጿል፡፡ህወሓት ይሄን ያለው ከመስከረም 20 እስከ 22 /2017 ዓ.ም ለሦስት ቀናት ያካሄደውን የማእከላዊ ኮሚቴ እና የከፍተኛ ካድሬዎች ስብሰባ ማጠቃለሉ በማስመልከት ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ ነው፡፡
በመግለጫውም ውይይቱን የሚያስቀጥል የትግራይ የሰላም ልዑክ አንደ አዲስ እንዲደራጅና በሰው ሃይል እንዲጠናከር እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡በትግራይ ክልል ያለው ፖለቲካ መካረር እየታየበት በመሆኑ ብዙዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ሲሆን፤ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ጥሪ እያደረጉ ይገኛል፡፡
@ethioreview.org