ቅድመ ክፍያ እንዳይሰበስቡ የሚስገድድ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀረ
ግንባታ ሳያጠናቅቁ ቤቶችን የሚሸጡ ሪልስቴቶች የሚሰበስቡትን ገንዘብ በዝግ የባንክ ሂሳብ እንዲያስቀምጡ የሚስገድድ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀረበ
ግንባታ ከማከናወናቸው አስቀድመው ቤት የሚሸጡ ሪል ስቴት አልሚዎች፤ከደንበኞቻቸውን የሚሰበስቡትን ገንዘብ በዝግ የባንክ አካውንት እንዲያስቀምጡ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ ቤት ለመገንባት የመሬት የይዞታ ማረጋገጫ እና የግንባታ ፈቃድ ያላገኙ የሪል ስቴት አልሚዎች ደንበኞችን እንዳይመዘግቡ እና ቅድመ ክፍያ እንዳይሰበስቡም ይከለክላል።
“የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ” የተሰኘው ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ዛሬ ሐሙስ መስከረም 30/2017 ዓ.ም. በተደረገው የፓርላማው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው።
በዛሬው ስብሰባ ላይ ከቀረቡት አራት ረቂቅ ሕጎች መካከል የሆነው ይህ አዋጅ፤ ከዚህ ቀደም ራሱን የቻለ ሕግ ላልነበረው የሪል ስቴት ቤቶች የግንባታ እና ግብይት ሂደት አዲስ እና አሳሪ አሠራሮችን ያስተዋወቀ ነው። እንደ ሕንጻ ያሉ የማይንቀሳቀስ ንብረቶች ያላቸው ዋጋ በመንግሥት እንዲሁም በግል ባለሙያዎች የሚገመትበትን እንዲሁም ግመታው አገልግሎት ላይ የሚውልበት አሠራርም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።
ከረቂቅ አዋጁ ጋር አብሮ ለምክር ቤቱ የቀረበው ማብራሪያ የሪል ስቴት ልማት፣ ግብይት እና የዋጋ ትመና “በቂ የሕግ ሥርዓት የሌለው በሕገወጥ ደላሎዎች ተጽዕኖ ስር የወደቀ” እንደሆነ ያስረዳል። የሪል ስቴት ልማት ካለው የቤት ፍላጎት “በእጅጉ የራቀ” እንዲሁም “በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ደላላ ተብለው በሚታወቁት አካላት” ተፅዕኖ ስር የወደቀ እንደሆነ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።
ምክር ቤቱ ስድስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 1ኛ መደበኛ ስብሰባው ስድስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ የኤልክትሮኒክስ ፊርማ ማሻሻያ አዋጅ ህጋዊ ዕውቅና ለመስጠት እና በዲጂታል የፊርማ ስርዓት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ሚና መብት እና ግዴታ ለመደንጋግ የረቂቅ አዋጁ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ለምክር ቤቱ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚው ያላትን ዝግጁነት ለማረጋገጥ እና በዘርፉ መልካም እድሎችን ለመጠቀም ረቂቅ አዋጁ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ የረቂቅ አዋጁን መሻሻል ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅምና ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በጥልቀት ሊያየው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጅ ቁጥር 1/2017 ሆኖ ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነት እና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡
የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ የኢትዮጵያ የህንፃ ረቂቅ አዋጅ የአገልግሎት ለውጥ ሥራ የሕዝብን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ እና የህንጻ ተደራሽነትን ለአካል ጉዳተኞችና ለማህበረሰቡ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አመልክተዋል።
እያጋጠሙ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ የግንባታ ጥራት እና የሃብት ብክነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግልፅና ምቹ የሆነ የአሰራር ስርዓትን ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤በከተሞች የሚገነቡ ህንፃዎች የመሬት የመሸከም አቅም፤ የአካል ጉዳተኞችን ደህንነት እና የአካባቢን ተፅዕኖ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ረቂቅ አዋጁም አዋጅ ቁጥር 2/2017 ሆኖ ለዝርዝር እይታ ለከተማ፣ መሰረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡
የእንስሳት ጤና እና ደህንነት ረቂቅ አዋጅ በእንስሳት ሃብት ልማት የህዝቡን ተጠቃሚነትና በዘርፉ ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር እና ደህንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርትን ለማሳደግ እና ለማሻሻል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ አመላክተዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ዜጎች በእንስሳት ሃብት ልማት ተጠቃሚ እና ጤናማ የኑሮ ዘይቤ ለማፍጠር ያስችል ዘንድ በህግ ማዕቀፍ ማካተቱ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 3/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።
በተመሳሳይ ምክር ቤቱ፤ የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለጤና፤ ማህበራዊ ልማት፤ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 6/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለከተማ፣ መሰረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መምራቱን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
Parlamentet news