የአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ምዕራባዊ የባህር ዳርቻ አስፈሪ በተባለለት ሀሪኬን ሚልተን በተባለ ከባድ ማእበል መመታቷ ተነግሯል።
ሀሪኬን ሚልተን ማዕበል ነፋስና ነጎድጓዳማ ዝናብ ያዘለ በመሆኑ ጉዳቱን ከባድ እንዳደረገው ነው የተገለጸው።
በግዛቲቱ የሚገኙ 3 ሚሊዮን መኖርያ እና ንግድ ቤቶችም በዚሁ ምክንያት የኤሌክትሪክ ሀይል ኢንዲቋረጥባቸው ሆኗል።
በተለይም በሃርዲ ካውንቲ ውስጥ ከ97 በመቶ በላይ ቤቶች ኤሌክትሪክ እንደሌላቸው ሪፖርት ተደርጓል።
የአሜሪካ ብሔራዊ አውሎ ነፋስ ማዕከል (ኤን.ኤች.ሲ) በሰጠው መግለጫ ሀሪኬን ሚልተን በፍሎሪዳ ምስራቃዊ የባህር ጠረፍ በሰዓት በ90 ማይል (150 ኪ.ሜ.) የሚጓዝ መሆኑን አስታውቋል።
ይህም ጠንካራ ማእበል ነው ያለው ማእከሉ በከተሞች መሰረተ ልማትን እና ዛፎች እንዲወድቁ ምክንያት መሆኑን ነው የገለጸው።
የአሜሪካ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ማዕበሉ በቀጣይ ቀናትም ከባድ ዝናብ፣ ጎርፍ እና አውዳሚ ነፋስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
እንደ ታምፓ ቤይ ታይምስ ዘገባ ከሆነ አሁን ላይ በማዕበሉ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት በፍሎሪዳ ግዛት የሚገኙ ሁለገብ ስታዲየሞች ለብሔራዊ ጠባቂዎች እና ለኤሌክትሪክ ሰራተኞች እንደ ማረፊያ ቦታ እያገለገሉ ይገኛሉ።
በሀሪከን ሚልተን የተነሳ ብዙዎች ቤት ንብረታቸውን ሲያጡ ቁጥራቸው በውል ያልተለዩት ደግሞ ህይወታቸው ሳያልፍ እንዳልቀረ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ጠቅሶ ዶቼቬሌ ዘግቧል።