ያለንበት ዓለም አቀፋዊ አውድ የፓን-አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ትብብርን እውን የሚያደርግ ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ተግባር መግባትን የግድ እንደሚል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገልፀዋል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ከጥቅምት 5 ቀን 2017 ጀምሮ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን “በአፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች መካከል ያለውን ትብብር” የተመለከተ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።
ባቀረቡት ገለፃ “ዓለም በአሁኑ ወቅት አንዱ ሌላውን ጥሎ የሚያልፍበት የበይና ተበይ አውድ ውስጥ ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ዓለም አቀፋዊ አውድ ውስጥ አፍሪካ አንድነቷን ካላጠናከረች ልክ እንደ በፊቱ የሌሎች የመጫወቻ ሜዳ የመሆን ዕጣ እንደሚገጥማትም ነው ያነሱት።
ቀደምት አባቶቻችን በየጊዜው በሁሉም መስክ የሚያጋጥሙ የደኅንነት ስጋቶችን የሚመክት አንድ ወጥ የአፍሪካ የመከላከያ ኃይል እንደሚያስፈልግ ቀድመው መናገራቸውንም አምባሳደር ሬድዋን አውስተዋል።
ከብዙ አስርት ዓመታት በኋላ አፍሪካ ቀደምት አባቶች ያስቀመጡትን ራዕይ አሳክታለች ወይ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንደሚያስፈልገው በመጠቆም።
አህጉሪቱ በአሁኑ ወቅት በርካታ ማኅበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እየተጋፈጠች ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ አሸባሪዎች፣ ጽንፈኛ ቡድኖች፣ የባህር ላይ ወንበዴዎችና የድንበር ግጭቶች እያመሷት መሆኑን ገልፀዋል።
የውጭ ኃይሎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አህጉራዊ የደኅንነት ስጋት መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉትን ችግሮች የውጭ ኃይሎች እንዲፈቱልን ማማተር አይገባም ያሉ ሲሆን፤ ከውጭ የሚመጣ መፍትሔ ቢኖር እርስ በርስ እየተጋጨን ልዩነቶቻችንን አስፍተን በችግር እንድንማቅቅ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የችግሩ መፍቻ ቁልፍ በእጃችን በመሆኑ ራሳችንን ችለን መቆምና አንዳችን ሌላውን በማገዝ ወደተሻለ አህጉራዊ ግብ መጓዝ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ሀገር የራሱን ችግር ለመቅረፍ የሚያደርገው ጥረት፣ ማኅበራዊ ፍትሕንና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት የውስጥ ግጭቶችን በመፍታት ሁኔታዎችን እንደሚያረግብ ጠቁመዋል።
መተማመን ላይ የተመሠረተ የሀገራት ግንኙነት፣ ችግሮችን በሰላማዊ ድርድር የመፍታት ባህል፣ የተፈጥሮ ኃብቶችን በፍትሃዊነት መጠቀም ግጭቶችን አስወግዶ አፍሪካዊ የጋራ የብልፅግና እና የሰላም ራዕይን እንደሚያሳካም ተናግረዋል።
በአፍሪካ የሚከሰቱ አካባቢያዊና ውጫዊ የፀጥታና ደኅንነት ችግሮችን የትኛውም ሀገር ብቻውን እንደማይወጣቸው ጠቅሰው፤ ጠንካራ ፓን-አፍሪካዊ ወታደራዊና የደኅንነት ትብብር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ፓን-አፍሪካዊ የቴክኖሎጂና ወታደራዊ መሳሪያዎች ምርት፣ የወታደራዊ ሥልጠና አቅም ግንባታ፣ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ፣ ወቅቱን የጠበቀ የደኅንነት መረጃ ልውውጥና የባህር ኃይል ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ወታደራዊ ትብብር እንዲጎለብት አበክራ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በወታደራዊ ልዩ ልዩ መስኮች የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ መኮንኖችንና ሙያተኞችን ከማሰልጠን ባለፈ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገች እንደምትገኝ ነው ያብራሩት።
አፍሪካውያን ከውጭ በሚገቡ ወታደራዊ መሳሪያዎች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንዲያላቅቁም የራስን አህጉራዊ አቅም መገንባት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ በጋፋትና ሆሚቾ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች የጀመረቻቸውን ተምሳሌታዊ ተግባር በተሞክሮነት አንስተው፤ አህጉራዊ የወታደራዊ ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ትብብር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የፓን-አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ስትራቴጂን መቅረፅ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው፤ ተቋማዊ ማዕቀፍ መፍጠር፣ ፓን- አፍሪካዊ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ግንኙነትን ማጠናከር፣ ሕጋዊ ሂደቶችን መጀመር፣ የሁለትዮሽና የብዝኃ-ዘርፍ ወታደራዊ ግንኙነቶችን አህጉራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የፓን-አፍሪካ የመከላከያ ኃይሎች ስትራቴጂ የአህጉሪቱን የፀጥታና ደኅንነት ሥራዎች ለመምራት እንደ አንድ ወጥ ፍኖተ-ካርታ እንደሚያገለግል ጠቅሰው፤ ሀገራት ከአህጉራዊ ግቦች የተናበበ ፖሊሲ እንዲኖራቸውም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ወታደራዊ ትብብር እውን መሆን መሠረት የሚጥሉ ግንኙነቶችን በየቀጣናው እያካሄደች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
አህጉራዊ ትብብርን እውን ለማድረግ በሁሉም ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ግንኙነትን ማዳበር እና መሪዎች የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው።
TIPS
Growing relations between Israel and Ethiopia: between military deals, intelligence influence, and an eye on Egypt
The Wars We Still Can Stop
Ethiopia: Israel Foreign Minister Says His Country Wants to Be Part of Ethiopia’s Success
A Nation Silenced: How the 1993 Referendum Stripped All Ethiopians of Their Sea
The 1976 TPLF Manifesto: TPLF’s “Republic of Greater Tigray”
Away from the global spotlight, Eritreans are trapped in a garrison state
Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s
Ethiopia-Eritrea Tension: A Volatile History that Never Truly Ended – Could Assab Become Africa’s Crimea?
“As an outlier among the five tplf leaders, I wasn’t part of the armed struggle tradition”
Former Tigray fighters say no to war
Don’t Risk Your Future: The United States Cracks Down on Illegal Immigration
Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation
Ethiopia and Eritrea Slide Closer to War amid Tigray Upheaval
Sea Outlet Serious and Unabated Agenda for Ethiopia: Retired Lieutenant General Yohannes
Israel’s Peace With Egypt Is Starting to Crack
Egyptian, Eritrean FMs reject involvement of non-bordering countries[Ethiopia] in Red Sea security