ሰንደቅ ዓለማ የሉዓላዊ ሀገር መለያ አርማ እና የህዝቦች ማንነት መገለጫ ነው፡፡ የህዝቦች ታሪክና አንድነት መገለጫ እና የሀገር ምልክትም ነው፡፡ ሰንደቅ ዓለማ የሰላም፣ የድል አድራጊነት እና የስኬት መገለጫ ተደርጎ ከፍ ብሎ ይውለበለባል፡፡ ሀገራት ካላቸው ሀገራዊ ታሪክና ዳራ ጋር አያይዘው ለሰንደቅ ዓለማቸው ያላቸውን ፍቅር እና ክብር በማሳየት ያከብሩታል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ጥንታዊ እና ነጻ ሀገራት የድል ቀናቸውን፣ በቅኝ ግዛት የተያዙት ሀገራት ደግሞ ከቅኝ ግዛትነት ነጻ የወጡበትን ቀን፣ በተለያዩ ምክንያት ዘግይተው ሀገር የሆኑት ደግሞ ነጻና ሉዓላዊ መንግሥት የመሰረቱበት ቀን ለማስታወስ የሰንደቅ ዓለማ ቀን ያከብሩታል፡፡
በዓለማችን 52 ሀገራት የሰንደቅ ዓለማ ቀንን ያከብራሉ፡፡ ኢትዮጵያም በራሷ መንገድ የሰንደቅ ዓለማን ቀንን ሀገራዊ መልክና ይዘት ያላቸው መልእክቶችን ቀርጻ በደማቅ ሁነቶች ታከብራለች፡፡ በዓሉ ጥቅምት በገባ በመጀመሪው ሳምንት ሰኞ ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት 16 ዓመታትም የሰንደቅ ዓለማ ቀንን በተለያዩ መሪ ቃሎች ስታከብር ቆይታለች፡፡ በዓሉ በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ በፌዴራል ደረጃ፣ በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች እና በሁሉም የፌዴራልና ክልል ተቋማት ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ይከበራል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት 16 ዓመታት ቀኑን በሀገር አቀፍ ደረጃ ስታከብር ምን ዓይነት መልእክቶችን ተጠቅማ ነበር? ባለፉት 16 ዓመታት የሰንቅ ዓላማ ቀናት አከባበሮች በሰንደቅ ዓለማው መርሆች እና ለብዘኃነታቸው ባላቸው ትርጉም ዙሪያ ግልጽነት ለመፍጠር፣ ዜጎች በሰንደቅ ዓለማው ትርጎሜ እና ቅርጽ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ ለማድረግ፣ የተዛቡ እና አሉታዊ አስተሳሰቦችን ለማቃናት ለማረም የሚያስችሉ መልዕክቶች ተላልፈውባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ አረንጎዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያሉት ሲሆን መሃሉ ላይ ሰማያዊ ኮከብ መደብ ብሔራዊ አርማ ያለው ሰንደቅ ዓለማችን ልምላሜያችንን፣ ተስፋችን እና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል መስዋእትነት ያንጸባርቃል፡፡
በኢትዮጵያ እስከ አሁን የተከበሩ የሰንደቅ ዓለማ ቀኖችን አስመልክቶ የተንጸባረቁ መሪ ሀሳቦችን በከፊል እናስታውስ፡-
• 7ተኛው “በህዝቦቹዋ ተሳትፎና ትጋት ድህነትን ድል በመንሳት ብሄራዊ ክብራችንና ሰንደቅዓለማችንን ከፍ ከፍ በማድረግ ላይ ያለች ሀገር ኢትዮጵያ!”
• 10ኛው “ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል!”
• 11ኛው “ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን!”
• 12ኛው “ሰንደቅ ዓለማችን የብዙሃን ድምር ውጤት፣ የአንድነታችን ምሶሶ ነው!”
• 13ተኛ “ሰንደቅ ዓለማችን ፣ለሰላማችን፣ ለአንድነታችን፣ ለሀገራዊ ብልጽግናችን!”
• 14ኛ “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓለማ ከፍታ!”
• 15ኛ “ሰንደቅ ዓላማችን የብዘሃነታችንና የሉዓላዊነታችን ምሶሶ ነው!”
• 16ኛ “የሰንደቅ ዓለማችን ከፍታ ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችንና ሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው!”
• 17ኛ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!”
በመሃመድ ፊጣሞ
አስገራሚ እውነታዎች -ስለ ሰንደቅ ዓላማ
ለመጀመሪያ ጊዜ የሰንደቅ ዓላማ ሃሳብ እንዴት እንደመጣ እርግጠኛ የሆነ መረጃ ባይኖርም፣ በተደረጉ ጥናቶች እጅግ ጥንታዊው ሰንደቅ ዓላማ መሰል በኢራን ሻህዳ ከተማ የተገኘው የነሐስ ሰንደቅ ዓላማ ነው።
ይህም በ2400 ዓመተ ዓለም እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፤ ሌሎች የሰንደቅ ዓላማ እውነታዎች እንደሚከተሉት እነሆ፡-
• ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት በመላቀቅ ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ፣ የኢትዮጵያን የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የነጻነት ምልክት በማድረግ በሀገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ውስጥ በማካተት ያዋሉ ሲሆን፣ ይህም “የፓን አፍሪካን ቀለሞች” በመባል እንዲታወቅ አድርጎታል።
• “ቬክሲልኦሎጂ” ስለ ሰንደቅ ዓላማ የሚያጠና መስክ ሲሆን ቃሉ በላቲን ሰንደቅ ዓላማ ወይም ባነር የሚል ትርጓሜን ይዟል፡፡
• ኔፓል የዓለማችን ብቸኛዋ አራት ማዕዘን ያልሆነ ሰንደቅ ዓላማ ባለቤት ሀገር ናት፤ሰንደቅ ዓላማዋ የሦስት ማዕዘን ቅርፅ ያለው ሲሆን የሂማላያስ ተራራን እና የሀገሪቱን ሁለት ኃይማኖቶች የሚያመለክት ነው፡፡
• የዴንማርክ ሰንደቅ ዓላማ የዓለማችን እድሜ ጠገቡ ሰንደቅ ዓላማ በመሆን ሪከርድ ያስመዘገበ ሲሆን ከ1219 ጀምሮ በጥቅም ላይ እንደነበር ይገለፃል፡፡
• ቀይ ቀለም በብዙ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚገኝ ሲሆን 78 በመቶ በሚሆን መጠን በዓለም ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ላይ ይገኛል፡፡
• ቱርክ፣ አልጄሪያ፣ ፓኪስታን እና እስራኤል በሰንደቅ ዓላማ ቸው የሚከተሉትን ኃይማኖት ምልክት ያዋሉ ሀገራት ናቸው፡፡
• የሮማኒያ ሰንደቅ ዓላማ የዓለማችን ትልቁ ሰንደቅ ዓላማ ሲሆን 349.4 ሜትር ርዝመት እና 227.8 ሜትር ስፋት አለው፤ ይህም 79 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ነው፡፡
• የኦሎምፒክ ሰንደቅ ዓላማ የዓለማችንን 5 አህጉር ያላቸውን አንድነት እና መስተጋብር በአምስቱ ቀለበቶች በኩል ያመላክታል፡፡እያንዳንዱ ቀለም ቢያንስ በአንድ የዓለም ሰንደቅ ዓላማ ላይ ይታያል።
• ሰንደቅ ዓላማ ሀገራትን ከመወከል ባሻገር በባሕር እንቅስቃሴ ወቅት መርከበኞች የሚግባቡበት ነው፤ ይህም መርከቡ ያለበትን ሁኔታ ለማመላከት ይረዳል፡፡
• በጨረቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በአስትሮናትስ ኔሊ አርመስትሮንግ እ.ኤ.አ በ1969 የተቀመጠው ሰንደቅ ዓላማ “ኦልድ ግሎሪ” የተሰኘው የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡
• የሞዛምፒክ ሰንደቅ ዓላማ ባለው የተለየ ዲዛይን እና የጦር መሳሪያ ምስል ከሌሎች ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ የተለየ ነው፡፡
• ሲዊዘር ላንድ እና ቫቲካን ሲቲ የስኩዌር ቅርፅ ያለው ሰንደቅ ዓላማን የሚጠቀሙ የዓለም ብቸኛ ሀገራት ናቸው፡፡
በአፎሚያ ክበበው ETV