ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ታዋቂ የግል ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ የሚታከም የስራ ባልደረባዬን ለመጠየቅ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቸ ጋር ጎራ ብዬ ነበር፡፡በዚህ ታዋቂ የግል ሆስፒታል ዋና በር ላይ ተደርድረው ለህሙማንና ቤተሰቦቻቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከተዘጋጁት ታክሲዎች መካከል ይህች ምስሏን የምትመለከቷት ‘’የጃጀች ታክሲ ‘’ከፊት ቀድማ ተሳፋሪዎችን ትጠባበቃለች፡፡በታክሲዋ እርጅናና መልከጥፉነት ተገርሜ በሞባይሌ ምስሏን ለመውሰድ መዘገጋጀቴን ልብ ያለ አንድ ሌላ ባለታክሲ ሳቅና ቀልድ በተቀላቀለበት አነጋገር ‘’ ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው፣ካሁን በፊት በሰይፉ ፋንታሁን ፕሮግራም የቀረበችው ይበቃታል‘’አለኝ፡፡አብረውኝ የነበሩት የስራ ባልደረቦች በኔና በባለታክሲው ቀልድ የተቀላቀለበት ንግግር ተገርመው ሲስቁ ጓደኞቸም በታክሲዋ ሁኔታ እንደኔው ተገርመው እንደነበር ልብ አልኩ፡፡
እኔን የበለጠ የገረመኝና ያሳሰበኝ እንኳንስ ሊጓዙባት ቀርቶ ለእይታም የምትደብርና‘’ከአርጅናም አልፋ ያረጠች ታክሲ ‘’ለትራንስፖርት አገልግሎት ያቀረበው ‘’የታክሲ ባለንብረት ‘’ድፍረትና ማንአለብኝነት ብቻ ሳይሆን በህይወታቸው ወስነውና ምቾታቸውን አጥተው ያውም ገንዘብ ከፍለው በዚች ጥርሷን ጨርሳ በድዷ ሳንቲም በምትበላ ‘’ታክሲ ‘’
የሚሳፈሩት ሰዎች ናቸው፡፡
እርግጥ ነው የከተማችን አንዱና በኔ እምነትም እጅግ አሳሳቢውና አስመራሪው ችግር የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት መሆኑን አውቃለሁ፡፡በዚህ ምክንያትም በሌሎች አገሮች በተለይም በኢኮኖሚ ባደጉ አገሮች ‘’እስከመፈጠራቸው የተረሱ ‘’ እና ሞዴላቸው ወደ ሙዚየም ከገባ ዓመታት ያስቆጠሩ ተሸከርካሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ያለማንም ከልካይ በጎዳናዎቻችን ላይ ሲንተፋተፉና እንደ ኤሊ በደረታቸው እየተሳቡ የትራፊክ መጨናነቅ ሲፈጥሩ እንመለከታለን፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የራሱን ተሸከርከሪዎችም ሆነ ሌሎች ንብረቶች የሚያስተዳድርበትና አስፈላጊም ሲሆን የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ አሮጌና ጊዜ ያለፈባቸውን ንብረቶች/ተሸከርካሪዎች የሚያስወግድበት ወይም ቅርጽና ይዘታቸውን ቀይሮ ለሌላ አገልግሎት የሚያውልበት መመሪያ እንዳለው አውቃለሁ፡፡ጥያቄው መመሪያው በሁሉም ዘንድ በትክክል ይፈጸማል ወይ የሚለው ነው፡፡
በነገራችን ላይ በሌሎች ያደጉ አገሮች ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች የሚገለገሉባቸውን ማናቸውም ንብረቶች በእርጅና ምክንያት ከመሰቀቃዬታቸው በፊት ቀድሞ ማስወገድና በአዲስ መተካት የተለመደ ነው፡፡የታወቁ የአሮጌ ንብረቶችና ቁሳቁሶች መሸጫና ማስወገጃ ‘’መጋዝኖች ‘’እንዳሏውም እኔ ራሴ ምስክር ነኝ፡፡በአንድ ወቅት በነበርኩበት አገር አንድ ‘’ ምርጥ ጃኬት‘’ገዝቸ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለብዙ ጊዜ መዘነጤንና በኋ

ላም ለአንድ ዘመዴ በስጦታ ማበርከቴን አስታውሳለሁ፡፡
በዚህም ምክንያት ነው በሌሎች አገሮች የአገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰው የተወገዱ ተሸከርካሪዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ አልባሳት …በልዩ ልዩ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው በመግባት ችግር ሲፈጥሩና አደጋም ሲያስከትሉ የምንመለከተው፡፡
ሌለው አስገራሚ ነገር የተሸከርካሪ ቁጥጥርና የትራፊክ ፖሊስ አካላት እንዲህ ዓይነት በእርጅና ምክንያት ቆዳቸውን የቀየሩ ተሸከርካሪዎችን እየተመለከቱ ምንም ዓይነት እርምጃ ሲወስዱ አለመታየታቸው ነው፡፡ጭራሹንም በየዓመቱ የተሸከርካሪ ደህንነትና ቴክኒካዊ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ እየሰጡ በየቀኑ ግን የተሸከርካሪ አደጋና የሰው ሞት ወሬ ያቀርቡልናል፡፡
መንግስት ሆይ ! በህግ አምላክ! ለአይን የሚያስቀይሙ ብቻ ሳይሆን አደጋ የሚያስከትሉና መህበራዊ ችግር በመፍጠር ከተመሳ ጭምር የሚያቆሽሹ ያረጡ ተሸከርካሪዎችን እንዲሁም ሌሎች ያረጁ ንብረቶች ማስወገድ የሚችል ሌላ‘’የኮሪደር ልማት ‘’እንድትጀምርልን በዚች ታክሲ ስም እንጠይቃለን፡፡
Vua Al Abebe fb