ክብርት ፕሬዚዳንት ተናገሩት እኮ!
የምን “ዝምታ ነው መልሴ” ነው?
“ዝምታ ነው መልሴ” ብሎ እንደመናገር ቅኔ ሰምተንም አናውቅ። ርዕሰ ብሔሯ ሀሳባቸውን የገለፁባት ጥቂት ቃላት ብዙ ማነጋገሯን ቀጥላለች።
ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ድንገት ወደ ኢዩቤልዩ ቅጥር ግቢ የገቡ መንገደኛ አይደሉም። ሀገራቸውን ያገለገሉ ስመ ጥር የዲፕሎማሲ ሰው በሳል ምሁር እና ባለውለታ ናቸው።
ያም ሆኖ ወደ ርዕሰ ብሔርነት ከመጡ በኋላ አልፎ አልፎ እንደ እናት አንተም ተው አንተም ተው ሲሉ ተደምጠዋል። የአሁኑ የስልጣን ዘመናቸው ማክተሚያ ዋዜማ የሙዚቃ ምርጫቸው አነጋጋሪ ኾኗል።
በኢትዮጵያ ፓለቲካ የስልጣን ዘመኑ ያበቃ ሰው እንዴት ሲበደል እንደኖረ እየነገረን ከንፈር መጥጦ መሸኘቱ ባህል ሆኗል። በስልጣን ላይ ሳለ በዚህ ምክንያት በቃኝ የሚል ሰው አይታይም በተቃራኒው ግን የስልጣን ዘመኑ ሲጠናቀቅ አልያም የግምገማ ጫናው ሲበረታ ወይም ደግሞ ፓርቲው በቃህኝ ሲለው ታፍኖ መኖሩን ይሰብከናል።
ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በቤተ መንግስት ቆይታቸው በርካታ መልካም ስራዎች ሰርተዋል። ሀገራቸውን ጠቅመዋል። ያም ሆኖ ላለፍት ዓመታት ችግሮች ደግሞ ከደሙ ንፁህ ነኝ ለማለት ዜማ ጋብዞ ማለፍ እንደ ዜማው ግጥም ቀላል አይመስለኝም።
ቤተ መንግስት ሆኖ ዓመታትን የሀገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን ላይ የተቀመጠ ሰው በመጨረሻ በዜማ ብሶቱን ዝም ብል ይሻላል ብሎ ሲነግረን እኛም በተራችን ዝምታ ነው መልሳችን።
ብዙ ሰዎች ከዚህ የፕሬዝዳንቷ ሀሳብ በመነሳት ብዙ በደል ደርሶባቸው መናገር ያቃታቸው አድርገው ሲገልፁ እያየሁ ነው።
ከሦስት ዓመት በፊት ያላቸውን ተስፋ ሲገልፁ “ከማንኛውም ፈተና በኋላ ብርሃን አለ፤ እጆቻችን በእሾህ ተወግተው እየደማ ከሆነ ጽጌረዳዋ ሩቅ አይደለችም። የእኛም ጽጌሬዳ ሩቅ አይደለችም እላለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አሁን ዝምታ ይሻላል ብለው ተስፋ የቆረጡበትን ስሜት አጋርተውናል።
የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማትነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት፤ በኢጋድ (IGAD)ና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው የሰሩት እኚህ ጉምቱ ዲፕሎማት፡፡በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ በመሆን ሰርተዋል።
የፕሬዝዳንት ዘመናቸው የተለያየ መልክ አለው። ለውጡን ሰብከውንም ነበር። ከሁሉም በላይ የቤተ መንግሥቱ ሰው ናቸው። በቤተ መንግስቱ ቆይታቸው ዓለሙን ብቻ ሳይሆን ወቀሳውንም ሊጋሩ ይገባል። ለእኛ እንዲናገሩልን ርዕሰ ብሔር ያልናቸው ሰው አንድ ዓመት ዝምታን ሞከርኩት ብሎ ዜማ መጋበዝ መፍትሔ አይመስለኝም።
“የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው
ጊዜም እንደ ሰው ሲገፋው
መሄጃ መውጫ ሲጠፋው
ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው፤” ብለውናል። እኛ ሆዳችን ሲከፋን እሳቸው ድምፅ እንዲሆኑን፣ ደግሞ ጊዜ የገፋን ቀን ለምን እንዲሉልን? ዝምታ ሳይሆን እውነቱን መናገር ነበር ተስፋ። ግን ድፍን ያለ ሀሳብ አካፈሉን። ከቀናት በኋላ ለሚሆነው ምልክት ነው።
(ስናፍቅሽ አዲስ – ለድሬ ቲዩብ)