በአፍሪካ ደቡብ አቅጣጫ የምትገኘውና 56,000 በላይ ስደተኞች ከሚኖሩባት የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎትና የኢትዮጵያ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አደረጉት የተባለው የላቀ ደረጃ ስምምነት እያነጋገረ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ሃያ ዓመታትና፣ በተለይም ካለፉት ስድስት ዓመት በሁዋላ አንጎላ ሰፋፊ ስራ ላይ መሰማራታቸውና ከዛ የሚነሳው የኮንትሮባንድ ንግድ ነው ዜናውን መነጋገሪያ ያደረገው።
“የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት እና የነበሩ ትብብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ምክክር አደረጉ” በሚል ዛሬ የተሰራጨው ዜና ኢትዮጵያን መዳረሻ ካደረገው የእጽ ዝውውር ጀርባ አሉ በተባሉ ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ በተዘርፈ ሃብት አንጎላ ላይ ትልልቅ ንግድ የመሰረቱ መኖራቸው ስለሚታወቅ ነው።
የአደገኛ ዕፅ አዘዋወሪዎቹ መነሻ ብራዚል (ሳኦፖውሎ)፣ ደቡብ አፍሪካ (ጆሃንስበርግ)፣ አዲስ አበባ፣ አንጎላ ታንዛኒያ፣ ኬኒያ እና ሌሎች ሀገራት ሲሆን መዳረሻቸው ደግሞ ናይጀሪያ (ሌጎስ)፣ ደቡብ አፍሪካ (ጆሃንስበርግ)፣ ህንድ፣ ዱባይና ታይላንድ መሆናቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያሰራጨው ዜና ያመለክታል። ሁለቱ የደህንነት ተቋማት ከፈጸሙት ውል ውስጥ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በተለይም መነሻቸውን ከአንጎላ ሉዋንዳ በማድረግ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሸጋገሩ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም በአቬዬሽን ሴኩሪቲ ዙሪያ የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው።
በአንጎላ ንግድ ላይ የተሰማሩ ወገኖችን ለይተው እንደሚያውቁ የገለጹ እንዳሉት ከሆነ ይህን ስምምነት ተከትሎ የሚሰሙ ዜናዎች ይኖራሉ። በአንጎላ በርክታ ኤርትራዊያንም በስደት እየሰሩ እንደሚኖሩ እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
በአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት (SIE) ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ የተመራ የልዑካን ቡድን ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፤ ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ታዜር ገብረ እግዚአብሔር አቀባበል አድርገውለታል።
የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ እና የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት (SIE) በተቋማት ደረጃ በሚከናወኑ የሁለትዮሽና ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በስፋት መወያየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል።
በውይይታቸውም የቀይ ባሕር እና የኤደን ባህረ-ሠላጤ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በምስራቅ፣ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኛ ቡድኖች፣ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በተለይም መነሻቸውን ከአንጎላ ሉዋንዳ በማድረግ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሸጋገሩ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም በአቬዬሽን ሴኩሪቲ ዙሪያ በቀጣይ የሚደረጉ ትብብሮችና የመረጃ ልውውጥ መስኮች ተዳሰዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እያከናወነቻቸው የሚገኙ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፀጥታ ዘርፍ ሪፎርሞች እና ቱርፋቶቻቸውን በሚመለከት ለአንጎላው ልዑክ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በሠላማዊ አማራጮች የባህር በር ተደራሽነትን ለማግኘት የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑካን ቡድኑ ያስረዱ ሲሆን፤ አንዳንድ አካላት ይህንን ዕውነታ ወደ ጎን በመተው ጉዳዩን ለራሳቸው የፕሮፓጋንዳ ሥራ እየተጠቀሙበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ አካሄድ የአፍሪካ ቀንድ እና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ወደ ቀውስ ሊከት እንደሚችል አብራርተው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነት መረጋገጥ ቀጣናውን እንደሚያረጋጋው እና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማምጣት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንፃር ተቋማቸው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በደኅንነትና ጸጥታ መስኮች የሚያደርገው የልምድና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በአቅም ግንባታ መስኮች የተጀመሩ የትብብር እና አጋርነት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ያደነቁት አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ፤ ሀገሪቷ በአጭር ዓመታት ውስጥ በዓይን የሚታዩ ትላላቅ የሪፎርም እና የከተማ ልማት ሥራዎችን መስራቷ ለሌሎችም በአብነት የሚወሰድ መሆኑን ገልፀዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት (SIE) በደኅንነት እና ፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም በመረጃ ልውውጥ እና ትብብር ሥራዎች ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ የላከልን መረጃ ያመላክታል።