መርካቶ ያገኙትን ከመሰብሰብ በቀር የግብር ጉዳይ የሚያንገሸግሻቸው ህገወጥ ነጋዴዎች ይበዙባታል። ይህን ሃቅ ራሳቸው ነጋዴዎች መድረክ ላይ የተናገሩት ሲሆን ስማቸውን ደብቀው ለኢትዮሪቪው የአዲስ አበባ ተባባሪ የገለጹም አሉ። በተመሳሳይ ህግና ስርዓት አክብረው የሚንቀሳቀሱ አነስተና ቢሆኑም አሉ። የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ከሚባትቱት ጋር ሁሉንም አንድ ላይ አካታ መርካቶ የየዕለት ተግባሯን እያከናወነች ነበር። ህግ እንደሚያስከብሩና ቁትትር እንደሚያደርጉ የሚያስታውቁ አካላት ሌብነትም የመርካቶ አንዱ ተውኔት ነው።
አሁን ላይ ባይታወቅም ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ ስታዲዮም ዙሪያ ሱቅ የተከራዩ መዋጮ እያሰባሰቡ ስፖርት ኮሚሽን ለሚታወቅ ክፍል እጅ መንሻ ያቀርቡት እንደነበረው፣ በመርካቶም ህገወጦች በተመሳሳይ መዋጮ እያሰባሰቡ የመንግስትን ከርሳሞች እንደሚቀልቡ በተደጋጋሚ ቢነገርም መንግስት መስሚያው ጥጥ እንደሆነ የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም።
አዳነች አቤቤ የሚመሩት የአዲስ አበባ አስተዳደር ሰሞኑን ታዲያ በዘመቻ መልክ በጀመረው አደን ምን ያህል ውጤታማ ስራ እንደሰራ ባይታወቅም፣ ዘመቻውን በማሳሳት መርካቶ ሰሞኑንን ከሚጎበኛት እሳት ትርምስ ሳትድን ሌላ ትርምስ ገጥሟታል። ህጋዊነትን ለማስከበር የተጀመረውን ዘመቻ አዳነጭ አቤቤ ” በጥናት የተሰራ” ቢሉትም፣ “ውርስ ሊካሄድ ነው” በተሰራጨ የማህበራዊ ሚዲያና የጎን ለጎን ሹክሹክታ በለሊት ሳይቀር ንብረት ወደ መኖሪያ ቤት ማጋዝና ማጋጋዝ ታይቷል።
የከተማዋ ምክር ቤት ይህንኑ መተራመስ አስመልክቶ ላነሳው ጥያቄ ” በመርካቶ ህጋዊ ግብይት እንዲደረግና ለግብይቱ ነጋዴው ደረሰኝ እንዲቆርጥ ቁጥጥር እና ክትትል እያደረግን ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች መመለሳቸውን ፋና ዘግቧል። ባጭሩ ነጋዴዎቹ ” ግብር ክፈሉ እንጂ ሌላ የተጠቁት ነገር የለም”
ተቆጣጣሪዎች ደረሰኝ ጠይቀው ያለ በቂ ጥናት ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጥሉባቸው የሚናገሩ ነጋዴዎች፣ በዚሁ ፍራቻ ሳቢያ ሽሽትና ንብረት ማሸሽ ውስጥ ሊገቡ እንደቻሉ ለተባባሪያችን ያስረዱ፣ “መንግስት ንብረት ይወርሳል” የሚል መረጃም በስፋት ተሰራጭቶ እንደነበር ጠቁመዋል።
“መንግስት ከንግድ ዘርፍ የድርሻውን ግብር ማግኘት ቢገባውም ህግን አክብረው ለመስራት የማይፍለጉና ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች እንዳሉ። ይህ ሃቅ ነው። እርስ በርስ እንተዋወቃለን” የሚሉት ወገኖች የፍትሃዊነት ጥያቄም ያነሳሉ። “ግብር የሚከፍሉና የማይከፍሉ እንዴት እኩል ይወዳደራሉ” በሚል የንግድ ሂደቱን መዛባት ያሳያሉ።
“በመርካቶ ህጋዊ ግብይት እንዲደረግ ቁጥጥር እያደረግን ነው” የሚሉት አዳነች አቤቤ፣ እንደ ሀገር ያለውን የግብይት ስርዓት በዘላቂነት ለማስተካከል በጥናት ላይ የተመረኮዘ ክትትል ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመርካቶ የገበያ ስፍራ ህጋዊ ግብይት እንዲደረግና ለእያንዳንዱ ግብይት ነጋዴው ደረሰኝ እንዲቆርጥ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ ላይ እንገኛለን” ሲሉ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል። በተደረገው ክትትልም በርካታ ህገ ወጥ የሆኑ አሰራሮች እንዳሉ ለመለየት እንደተቻለም አክለዋል፡፡
ግኝቱን መሰረት አድርገው “ግማሹ ግብር እየከፈለ ሌላው የማይከፍልበት አሰራር መኖሩን፣ ቀደም ሲልም ከነጋዴዎች ጋር ባደረግነው ውይይትና ክትትል ይህንኑ ተገንዘናል” በማለት ከንቲባዋ ከላይ ላነሱት ውሳኔያቸው ማስደገፊያ ያሉትን አመክንዮ አቅርበዋል።
“ግብር ለማስከፈል እና ደረሰኝ እንዲቆርጡ ለማድረግ በተደረገው ሂደት በሀሰት ውዥንብር በመንዛት መጋዘኖችን በመዝጋትና በምሽት ሳይቀር እቃዎች ሲጫኑ ነበር” በማለት አስተዳደሩ ሙሉ መረጃ እንዳለው ከከንቲባ ጽ/ቤት ያሰራጨው መረጃ ያሳያል።
የሃሰት ውዥንብሩን “ይህ ፍፁም ስህተት ነው” ያሉት ከንቲባዋ “በቀጣይ ህጋዊ ስርዓት በመዘርጋትና ለእያንዳንዱ ግብይት ደረሰኝ እንዲቆርጡ በማድረግ ግብርን በአግባቡ መሰብሰባችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል።
ይህንኑ ተከትሎ መርካቶ ከወትሮ የተለመደ ግርግር ይልቅ ተፋዛለች። መርካቶን የጎበኙ እንዳሉት የተዘጉ፣ የታሸጉ፣ በመዝጋትና መክፈት መካከል የሆኑ ሱቆችን አስተውለዋል። ሚሊተሪ ተራ ፤ ዱባይ ተራ ፤ አድማስ እና አመዴ ገበያ አካባቢ የሚገኙ ሱቆች ይገኙበታል። ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን የዘጉት ከደረሰኝ ጋር በተገናኘ ውዝግብ መሆኑን ለቲክቫህ ነግረዋል። ተስያት ላይ አንዳንድ ሱቆች እንደተከፈቱ መሆኑም ተጠቁሟል።
ገለልተኛ ነዋሪዎች ” ግብር ሳልከፍል ዝም ብዬ ትርፍ እያግበሰበስኩ ልኑር” የሚለው አካሄድ ልክ እንዳልሆነ ገልጸው መንግስት ገቢው ቀረጥ በመሰብሰብ ስለሆነ አጠናክሮ ሊገፋበት ይገባል” ብለዋል። ግን ፍትሃዊ መሆንና ባለስልጣኖቹ ራሳቸውን ከሌብነት ሊያሸሹ እንደሚገባ፣ በሌብነት በሚገኙ ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ መክረዋል። ዘመቻው ነጋዴው ላይ ብቻ ሳይሆን ግብር ሰብሳቢው ላይም ሊሆን እንደሚገባ በርካቶች በአደባባይ የሚገልጹት ጉዳይ ነው።
በሰሀን ተራ አካባቢ የሚገኙት ሱቆች በግድ እየታሸጉና ባለቤቶቹ እየተባረሩ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚሰራቸው ወሬ ” በአክሲዮን የገበያ ማዕከልን ለመገንባት በያዙት ዕቅድ መሰረት ሱቆቻቸውን በፈቃዳቸው ለቀው እየወጡ ባለንብረቶቹ ተናግረዋል። ለቲክቫህ ምስክርነታቸውን የሰጡ እንዳሉት፣ በተጠቀሰው አካባቢ የሚገኙት ነጋዴዎች ሱቃቸውን የለቀቁት በስምምንነት መሆኑንም አረጋግጠዋል። የተለቀቁትም ሱቆች ከወረዳው የመሬት የልማት አስተዳደር ጽ/ቤት ማህተም የተደረገበት ” ታሽጓል ” የሚል ማህተም ታትሞባቸዋል። ” በሃይል ተባረሩ” ሲሉ መረጃውን ሲረጩ የነበሩት በማስረጃነት የተጠቀሙባቸው የታሸጉ ምስሎችም ይህንኑ በስምምነት እንደተፈጸመ የተነገረለትን የ”ታሽጓል” ማህተም ያረፈባቸውን ሱቆች ነው።
ከደረሰኝ መቁረጥ ችግር ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች ደረሰኝ የመቁረጥ ስራ መከናወን እንዳለበት ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድም ግብረሀይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገልጸዋል።
ይሁንና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይት ደረሰኝ አንቆጥርም የሚል ሀሳብ እንደሌለ ነገር ግን ትኩረቱ ጅምላ እና አከፋፋዮች ላይ መሆን እንዳለበት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ረገድ ውይይቱ መቀጠሉን እና በጉዳዩ ላይ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
በከተማዋ የሚሰራው የልማት ስራ ገቢን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ደረሰኝ እየቆረጡ የገቢን መሰረት ማስፋት፣ህጋዊነትን ማስፈን ፣በህግ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን መብት መጠበቅ እንደሚገባ እና በዚህ ረገድ የምክር ቤት አባላትም እገዛ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡
ትልቁ የገቢ ማእከል የሆነው መርካቶን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለይም ከገቢ ደረሰኝ መቁረጥ እና ከባለሙያ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ችግሮች እየታረሙ የሚሄዱ መሆናቸውንም አቶ ጃንጥራር አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የታክስ ኢንተለጀንስ እና የምርመራ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ነጋሽ ” መርካቶ በባህሪው ብዙ የክልል ግብር ከፋዮች የሚያለቅሱበት ቦታ ነው የሌሎች ክፍለ ከተሞች ግብር ከፋዮችም ቅሬታ ያቀርባሉ ደረሰኝ አይሰጡም በሚል ትልቅ ችግር ስላለበት ትኩረት ተደርጎበት ያለ ነው እንጂ አዲስ አይደለም ” የሚል ምላሽ መስጥታቸው አይዘነጋም።
የተጭበረበር ደረሰኝ በማተምና በማሰራጨት መንግስት በመቶ ሚሊዮኖች ያሳጡ አጭበርባሪዎች በተደጋጋሚ መያዝቸውና ፍርድ ቤት መቀረባቸው አይዘነጋም።