ሳዑዲ አረቢያ በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 ሰባት ኢትዮጵያውያን፣ ሦስት ሱዳናውያን እና አንድ ኤርትራዊን ጨምሮ ከ100 በላይ የውጪ ሀገራት ዜጎች በሞት መቅጣቷን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ።
በውጪ ዜጎች ላይ ተግባራዊ የሚሆነው የሞት ቅጣት በዓመቱ የጨመረው ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
የብሔራዊው ዜና ወኪል ዘገባዎች ላይ በመመሥረት በተደረገ ቆጠራ በዕለተ ቅዳሜ የተፈጸመው የሞት ቅጣት ሊገባደድ አንድ ወር ገደማ ብቻ በቀረው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 በሳዑዲ አረቢያ በሞት የተቀጡ የውጪ ሀገራት ዜጎችን ቁጥር 101 አድርሶታል።
በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት መረጃ መሠረት በ2023 በሳዑዲ አረቢያ 34 የውጪ ሀገራት ዜጎች በሞት ተቀጥተዋል። በ2022ም ቁጥሩ ተመሳሳይ ነበር። የዘንድሮው ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ ገደማ የላቀ ነው። መቀመጫውን በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ያደረገው የአውሮፓ-ሳዑዲ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት (ESOHR) እንደሚለው የዘንድሮው የሞት ፍርድ ክብረ ወሰን የሰበረ ነው ብሏል።
በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት ዘንድሮ ሳዑዲ አረቢያ ሰባት ኢትዮጵያውያንን በሞት ቀጥታለች።
ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ 21 የፓኪስታን፣ 20 የየመን፣ 14 የሶርያ፣ 10 የናይጄሪያ፣ ዘጠኝ የግብጽ፣ ስምንት የዮርዳኖስ ዜጎች በሞት ተቀጥተዋል።
ከሱዳን፣ ከሕንድ እና ከአፍጋኒስታን ከእያንዳንዳቸው ሦስት፤ ከኤርትራ እና ከፊሊፒንስ አንድ በሞት ከተቀጡት መካከል ናቸው።
በዓመቱ ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ምክንያት 92 ሰዎች በሞት የተቀጡ ሲሆን 69 የውጪ ሀገራት ዜጎች ናቸው።
ዲፕሎማቶች እና የለውጥ አራማጆች እንደሚሉት የውጪ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ዜጎች የፍርድ ቤት ሰነዶች ማግኘትን ጨምሮ ፍትኃዊ ፍርድ ለማግኘት ከፍተኛ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል ይላሉ።
ሳዑዲ አረቢያ ሞት የተፈረደባቸውን ሰዎች አንገት በመቅላት የምትታወቅ ቢሆንም የመንግሥት ኦፊሴላዊ መግለጫዎች ግን የቅጣቱን አፈጻጸም ከመግለጽ ይቆጠባሉ።
በነዳጅ ዘይት የበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በጎርጎሮሳዊው 2023 እስረኞችን በሞት በመቅጣት ከቻይና እና ከኢራን በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አምስነቲ ኢንተርናሽናል አስታውቆ ነበር።
Via : DW