ትጥቅ መፍታትና አለመፍታት በብሄር ካባ ተሸፍኖ ተግባራዊ እንዳይሆን ዘመቻው ብዙ እንደነበር የሚታወስ ነው። ” እገሌ ካልፈታ እኔ አልፈታም” በሚል፣ ይህንኑ ምክንያት ለራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸሚያ በመጠቀም ያለመታከት የተቀናጀ ቅስቀሳ የሚያካሂዱ ቡድኖች ታክለውበት አፈጻጸሙ እንከን ገጥሞት ኦይቶ ነበር። ከምንም በላይ ህዝብና አገር በዚሁ “ትጥቅ አንፈታም” ባሉ ኃይሎች አማካይነት ለከፍተኛ ችግር፣ ሞትና መፈናቀል ተዳርገዋል።
“የነጻ አውጪ” ስም ያነገቡ ኃይሎች “ነጻ እናወጣዋለን” በሚሉት ብሄር ስም በሚነቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ህዝብ ተማሯል። ተዘርፏል። ተገድሏል። ተፈናቅሏል። አርሶ መብላትና መገባያየት ሳይችል ቀርቷል። ከሁሉም በላይ ግን የማይረሳ ጉዳትና ጥቁር ጠባሳ የጣለ ጦርነት እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል። አስከፊ ውጤት ያስመሰዘገበውና ከትግራይ ተነስቶ አማራና አፋርን ያካለለው ጦርነት በሰላም ከተቋጨ በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ ይፋ ሆኗል። ኢዜአ ሁሉንም አካላት አነጋግሮ የዘገበውን ከስር ይመልከቱ።
በሰባት ክልሎች ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን ከ760 ሚሊየን በላይ ዶላር ወጪ በሁለት ዓመታት ውስጥ በተሀድሶ ስልጠና ሂደት በማሳለፍ መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ገለጹ።
በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ተሀድሶ የቦርድ ሰብሳቢ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳኤ ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን፥ ከሁለት ዓመታት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ያስከፈለው ዋጋ ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ትምህርት የሚወሰድበት ክስተት ነው ብለዋል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና የኢትዮጵያ ሕገመንግስት መሰረት አንድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንደሚኖር በመደንገጉ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ እንዲያወርዱና በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና እንዲያልፉ በማድረግ መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ከስምምነት መደረሱን አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑም በተቋቋመ ማግስት ተቋምን የመምራት፣ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን መፍጠር ላይ በትኩረት በመስራት የተሻለ ተክለ ቁመና ያለው ተቋም መገንባት ተችሏል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፖሊሲና ስትራቴጂው የሚመራበት ግልጽ ርዕይና ስትራቴጂ በመቅረጽ ለቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና እና የመልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የማስፈጸሚያ ፕሮጀክቶች መቀረፃቸውን አብራርተዋል።
በዚህም ከፌደራል እና ክልል መንግስታት እንዲሁም ተባባሪ ለጋሽ አካላት ጋር በትብብር መስራት የሚያስችል መተማመን መፍጠር እንደተቻለ አንስተዋል።
በተሀድሶና መልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሩ መነሻነትም በሰባት ክልሎች ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከ760 ሚሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር ወጪ በሁለት ዓመታት ውስጥ በተሀድሶ ስልጠና ሂደት በማሳለፍ መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በ1ኛ ዙር 75ሺህ፣ በ2ኛ ዙር 100ሺህ፣ በ3ኛው ዙር 150ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን እንዲሁም በ4ኛው የማጠናቀቂያ ምዕራፍ 46ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መነደፉን አስታውቀዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎች በስድስት ቀናት በሚኖራቸው የተሀድሶ ስልጠና ቆይታም ልዩ ልዩ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት የማቋቋሚያ ክፍያ በመፈጸም ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም ከመንግስት፣ ከተባባሪና ለጋሽ አሕጉራዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ተቋማት 60 ሚሊየን ዶላር በመሰብሰብ ወደ ስራ እየተገባ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ሰላምን በማጽናት በተደላደለ መሰረት ለማስቀመጥ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።
በቀጣይም የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም ተባባሪ አካል የራሱን አዎንታዊ ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተሀድሶ ስልጠና የሚያልፉ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደየመጡበት ማህበረሰብ ሲመለሱ የልማትና የሰላም አካል በመሆን ህዝባቸውንና ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ምን አሉ?
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት፥ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽንና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እየሰሩት የሚገኘው የመልሶ ማቋቋም ስራ ከጦር መሳሪያ ማስፈታት ባለፈ የትግራይ ክልልን ሰላምና ደኅንነት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ የሚከናወን ነው ብለዋል።
የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ የሚገኘው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅንጅት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አዎንታዊ ውጤቶች እያመጡ መሆኑን ጠቅሰው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ጉዳይ ቀሪ ስራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችም ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ የሚገኘው ጥረት ትልቅ እመርታዊ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የተሀድሶ ስልጠና እና መልሶ ማቋቋም ተግባሩም በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ የሚያጋጥሙ የሀብት ውስንነቶችን ታሳቢ በማድረግ በኃላፊነት ስሜት መምራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም የሁሉም አይነት የልማትና የሰላም አማራጭ አቅም ተደርጎ የሚሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽንም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት አጋሮችና ተባባሪ አካላት ጋር በመተባበር ሂደቱን በውጤት ለመምራት የሄደበት ርቀት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።