ሰብለ ወርቅ (ስሟ የተቀየረ) አገሯን ለቃ አውሮፓ መኖር ከጀመረች አስራ ሶስት ዓመት ሆኗታል። ብቻዋን ያሳደገቻቸው ሁለት ልጆች አሏት። አንዱና ትልቁ አስራ ስድስት ዓመት ሆኖታል። አማርኛ አቀላጥፎ ይናገራል። ሁለተኛዋ ሴት ልጇ ገና ስምንት ዓመቷ ነው።
የጉዳዩን መነሻ በስልክ ስታስረዳ የንዴት ሲቃ እያነቃት ነው። ደጋግማ “ምን በድለናቸው ነው?” እያለች ሁሉንም ባይሁን አብዛኞቹን ኤርትራዊያኖች ትጠይቃለች። ንዴቷን ያጋመው ጉዳይ መነሻው ትልኩ ልጇ አራት እየበሉ ድንገት ያነሳባት ጉዳይ ነው።
” ማማ ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ተገዝታለች” አላት በድንገት። ” ማን ነገርህ? ከየት ሰማህ? ትምህርት ቤት ነው?” በማለት ሰብለ ወርቅ ጠየቀች። ኤርትራዊ ጓደኞቹ ቤተሰቦቻቸው እንዳስተማሯቸውና ኢትዮጵያዊያን “ቅኝ አልተገዛንም የሚሉት እውሸት ነው” ብለው እንደነገሩዋቸው ጠቅሰው እንዳስረዱት ገለጸላት። ሰብለወርቅ የሆዷን በሆዷ ይዛ ቤተሰቦቻቸውን ጠየቀችው።
“ስሜቴን ደብቄ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ አስመስዬ ገበታ ካነሳሁ በሁዋላ መኝታ ቤቴ ግብቼ አነባሁ” ትላለች ሰብለወርቅ። ይህ ለሌሎችም ትምህርት ይሆን ዘንድ ቢጻፍ ብላ ለዝግጅት ክፍላችን ነገረች።
“ኢትዮጵያ ቅኝ ግዢ ተይዛለች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን ውሸታም እንደሆን ለልጆቻችን መናገር መነሻው ምንድን ነው?” ልጇ የተነገረው ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ ቤት እንደሌላቸው፣ በረሃብ እንደሚያልቁ፣ ከዓለም የመጨረሻ ደሃ አገር መሆኗን ወዘተ ለመስማትም የሚያስጠላ ብዙ ነገር የሰብለወርቅ ልጅ ሲጋት ኖሯል።
ይህን የተረዳችው ምራቋን ዋጥ፣ ስሜቷን ቆንጠጥ አድርጋ ልጇን በጥበብ መርምራ ነው። በስልክ ምልልሱ ወቅት ” ለምን በዚህ ደረጃ ተቆጣሽ” በሚል ለቀረበላት ጥያቄ ” አለማበዴ ነው የሚገርመው” ስትል ስሜቷ የተጎዳበትን ምክንያት አስረዳች።
ከኤርትራዊያኑ ቤተሰቦች ጋር የነበራት ትውውቅ
ዛሬ ኢትዮጵያን በልመና፣ በድህነት፣ በባርነት የተያዘች አገር እንደሆነችና የተለያዩ ስሜት የሚጎዱ ጉዳዮችን አንስተው ልጆቻቸውን የሚያሰለጥኑት ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደ አውሮፓ ያመጡት ከአዲስ አበባ ነው። አዲስ አበባ ጳውሎስ ሆስፒታል ጀርባ በአንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ አርፈው ወደ አውሮፓ እስኪመጡ የተስተናገዱት በሰብለ ወርቅ እናትና አባት ቤት ውስጥ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም አሁን ላይ የእናትየው ሁለት ቤተሰቦችና እናት የሚኖሩት በመጠነኛ ኪራይ ሰብለወቅር እናትና አባት ቤት ውስጥ ነው። ሽሮ፣ በርበሬ፣ የገንፎ ዱቄትና ቅመማ ቅመም እያዘጋጁ አብረው የሚልኩት ቤተሰቦቿ ናቸው። ሰብለወርቅ ደሟ የተንተከተከው በዚህ ደረጃ የምታውቃቸው ስዎች ልጇን አገሩን በተሳሳተ ስዕል እንዲያይ ማሰባቸው ነው። ከዚያም በላይ ልጄ ቤተሰቡን ውሸታም አድርጎ እንዲስል የተኬደበት ርቀት ፍጹም ሰዋዊ መስሎ ሊታያት አልቻለም።
” በዚህ ደረጃ ኢትዮጵያዊያንን የሚፈትኑን ለምንድን ነው?” የምትለው ሰብለወርቅ፣ ወዲያውኑ ደውላ ለአባትና እናቷ ቤታቸውን እንዲያስለቅቁ መናገሯን ገልጻለች። ከዛም ልጇን የዓለምን የመረጃ ሳጥን ያጨናነቀውን የኢትዮጵያን ያለመገዛት ታሪክና የአደዋ ድል አስረግጣ ማስተማር ተያያዘች። እሚማርበት ትምህርት ቤት በመሄድ አስተማሪዎን አነጋግራ እውነቱን እንዲረዳ አስቻለች።
አውሮፓ የሚያድጉ ልጆች ቤተሰብ ካልበከላቸው በቀር ውሸትና ተራ ጥላቻ የመቀበል ዕድላቸው አነስተኛ በመሆኑ ለምን ውሸት ሊነግሩት እንደፈለጉ ጠየቀ። በዚያው ሰሞን የጓደኛውን አባት አግኝቶ “ልጅህን ለምን ውሸት ታስተምራለህ” ብሎ ወቀሰው።
በዚህ ደረጃ የምታውቃቸውን፣ ምንም እንኳን በነጮች የቀን መቁጠሪያ ቢጠቀሙም የዘመን መለወጫን፣ ፋሲካን፣ ገናን፣ የየዕለት ክብረ ባዓላትን አብረው ሲያከብሩ ለዓመታት የቆዩትን ወዳጆቿን መለየቷን ሰብለወርቅ ገልጻለች።
ሰብለ ስም እየተጠራች ቤተሰቦቻቸውን አዲስ አበባ አስቀምጠው የሚጦሩ፣ የሚረዱ፣ የሚያስተምሩ፣ የሚነግዱ፣ የሚያስነግዱ … ብዙ መሆናቸውን ትናገራለች። ኢትዮጵያ በአስር ሺህ የሚቆተሩ የኤርትራ ስደተኞችን መሸከሟን ታስረዳለች። በተመሳሳይ በስደትም ይሁን በማናቸውም ምክንያት ኤርትራ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንደሌሉ በመግለጽ “ኢትዮጵያ ምን አደረገቻቸው?” ስትል ትጠይቃለች።
“በባርነት፣ በቅኝ ግዢ ተይዘናል፣ ነሳነትን እንፈልጋለን” አሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን የተነፈሱት ነገር የለም። በወረቀት ላይ ” ነሳነት አሉ እንጂ በግብር ኢትዮጵያን ተታብተው ነው የኖሩት” የምትለዋ ሰብለወርቅ፣ ትህነግ የሚባል የትግራይን ህዝብና ኢትዮጵያን ያዋረደ ድርጅት ምስጋና ይግባው መቀለጃ አደረገን ብላለች።
ትህነግ በከፋፈተው በር ውስጥ ተሰግስገው ኢትዮጵያን የዘረፉት እነሱ መሆናቸውን የምታነሳው ሰብለወርቅ፣ ዛሬ ድረስ በቀበሌና በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ቤት ያለ አንዳች ልዩነት እየኖሩ፣ በመንግስት ተቋማት እየሰሩ፣ ያለአንዳች ልዩነት ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንትሮባንድ እየነገዱና ዶላር እያጠቡ ኢትዮጵያን በዚህ ደረጃ የሚተሉበት መንፈስ ምን እንደሆነ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊመረመረው እንደሚገባ ሰበለወርቅ ታሳስባለች።
ኢትዮጵያዊያን የተጋነነ የቤት ኪራይ ወጪ ላይ የተዳረጉት አንድም በእነሱ ፍልሰት ምክንያት እንደሆነ እየታወቀ ከቅናትና ከበታችነት ስሜት በሚመነጭ ቅዠትና ስካር ኢትዮጵያን ለማቆሸሽ ሌት ተቀን መዳከራቸው እጅግ ያስቆጣት ሰብለወርቅ ” ኢትዮጵያዊያን ኋላ ቀር ናችሁ” ሲሉ ለልጇ የሰቱትን ምክንያት በስላቅ አንስታ “… ስለ ንቃት፣ ስልጣኔና ዘመናዊነት ወዘተ መናገር ቢያስፈልግ የአውሮፓን ጋዜጦች ያጨናነቀው የእነማን አስገራሚ የዕለት ተዕለት ክስተት እንደሆነ በማስረጃ መዘርዘር ይቻላል” ብላለች።
ጥሩ ሰዎች እንዳሉ ባይካድም አብዛኞቹ ኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው የምትገልጸው ሰበለወርቅ ” ኢትዮጵያ ሶማሌን ልትወር ነው” ብለው ለልጇ መንገራቸውን ስታነሳ ከንዴት በላይ ነው የሚሰማት። “ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ የባህር በር ብትከራይ ኤርትራዊያን ምን አገባቸው? ቢሳካ ቢያንስ ከውጤቱ ተጠቃሚዎች የሚሆኑት አዲስ አበባ አስቀምጠው የሚቀልቧቸውና የሚጦሩዋቸው ቤተሰቦቻቸው ጭምር እንደሆነ እንዴት አይገባቸውም”
ፖለቲከኛ ባትሆንም ስለ ኢትዮጵያ በደል ለመናገር እንደማታንስ ገልጻ በቅርቡ ኢትዮጵያዊያን ለልጆቻቸው ስለ አገራቸው ታላቅነት፣ ስልጣኔ፣ እድገት ለልጆቻቸው ማስተማርና በመረጃ ማስታተቅ እንደሚገባቸው ለማስተማር ማቀዷን ገልጻለች። በተለይም ከባንዳነት፣ ከቅኝ ግዢ አስተሳሰብ፣ ከበታችነት ስሜት ከሚቀዱ እሳቤዎች አንድን የህብረተሰብ ክፍል እንዴት ከእውነትና ከአመክንዮ እንደሚያርቁ ለማሳየት መወሰኗንም አመልክታለች። ኢትዮጵያዊያን ልጆቻቸውን ሊከታተሏቸው እንደሚገባም መክራለች።
“ረጋ በሉና መርመሩ። ወያኔ አዲስ አበባ ሲገባ ክላሽ ከጓዳችሁ እየመዘዛችሁ ስታሽካኩብን ነበር አላኮረፍንም። ወያኔ ዓይናችሁ ቀለሙ ቀፈፈኝ ሲልና ሲያግዛችሁ አልቅሰን ሸኘናችሁ። ንብረታችሁን በአደራ ጠበቅን። ስትመጡ እጃችንን ዘርግተን ተቀበልን። ጓዳችንን ከፍተን አስተናገድን። እያስተናገድንም ነው። ምን አጉድለን ነው በዚህ ደረጃ የምተፈትኑን? አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ዜጋችሁን የተሸከመች፣ ከዜጎቿ ለይታ የማታያቸሁ እርጥብ አገር ምን በድላ ነው በዚህ ደረጃ የምትጠሏት? … አምላክ ፍርዱን ይስጥ”
ዝግጅት ክፍሉ- በዚህና ተመሳሳይ ጉዳዮች ማናቸውንም ጽሁፎች ጨዋነት እስከተላበሱ ድረስ ለማተም ዝግጁ መሆናችንን እናስታውቃለን።