ዛሬ ደግሞ በኢትኖግራፊ ሽርሽራችን ወደ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ አቅንተን ወሎን ልንዘይረው ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ግጥም የዚያራችን መክፈቻ ብናደርገውስ?…
ሀገራችን ደሴ ስማችን ወሎዬ ፣ በነካኩንና ጉዳችን በለዬ

እውነት ነው፡፡ የወሎ ሰው ፍቅር ነው የሚያውቀው፡፡ ፍቅር ነው የሚገዛው፡፡ ፍቅር ነው የሚያስተምረው፡፡ ለጸብ የሚያነሳሳውን በጄ አይልም፡፡ ነካክቶት ሊያሳስተው የሚዳዳውን ጉድ ነው የሚያወርድበት፡፡ ለጊዜው ተሸንፎ ጸጥ ሊል ይችላል፡፡ የኋላ ኋላ ግን ጊዜውን ጠብቆ ያስተነፍሰዋል፡፡ በተረፈ ግን ወሎ ፍቅር ነው፡፡ መውደድ ነው፡፡
ወሎ ውበትም ነው፡፡ ውበት ይፈስበታል፡፡ ኮረዳዎቹና ሸበላዎቹ ልብን ይቀስፋሉ፡፡ ሆድ ያጥበረብራሉ፡፡ አዕምሮ ይበረብራሉ፡፡ ብዕር ያስመዝዛሉ፡፡ ቅኔ ያስዘርፋሉ፡፡ ወግ ያስጠርቃሉ፡፡
ከወንዝም ወሎ ቦርከና
ሞልቶ ይፈሳል ቁንጅና፡፡
አዎን! እጅግ ውብ የነበሩት ጣይቱ ብጡል፣ ምንትዋብ፤ ወርቂት፤ ስሒን ሚካኤል፣ መነን አስፋው፣ መነን ትልቋ (የራስ ዓሊ እናት)፣ የሺእመቤት ዓሊ (የተፈሪ መኮንን እናት)፣ ወይዘሮ ባፈና (የልጅ እያሱ አያት) ወዘተ… ወሎዬዎች ናቸው፡፡ ከሸበላዎቹም እያሱ ሚካኤል፣ ራስ ዓሊ፣ ደጃች ማርዬ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ እያልን በርካቶችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ወሎየዋ ወጣት በቁምህ ታፈዛሃለች አሉ ከቦታው ደርሰው ያዩዋት፡፡
ቦረና ቦረና ቦረና ገነቴ ፣ አብረከረችኝ ገባች በጉልበቴ፤
በዚህ ዘመን ጥርሰ ፍንጭት መሆን ብዙም አይመረጥም መሰለኝ፡፡ የምን መሰለኝ? በትክክል እየሆነ ነው እንጂ! ፍንጭት የሆኑ ሰዎች ጥርሳቸውን እንደሚያስሞሉት እየሰማን አይደለም እንዴ?… እነ እገሌ ብለን ለመጥራት ብንቸገርም ድሮ የምናውቃቸው ፍንጭቶች የፊት ጥርሳቸውን ገጥግጠው መሙላታቸውን አንብበናል፡፡ በወሎ ምድር ግን ፍንጭት መሆን አሁንም ድረስ ውበት ነው፡፡ ፍንጭት መሆን አሁንም የቁንጅና መለኪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ፍንጭት መሆን ያስመርጣል! ፍንጭት መሆን ያስፈነድቃል፡፡ ምን ይህ ብቻ? በመላው ኢትዮጵያ የሚታወቅ ውብ የሆነ የፍንጭትነት ማድመቂያ ህብረ-ቃልም አስገኝቷል እንጂ! የወሎ ኮረዳዎችና ሸበላዎች በ“ሚጊራ ጉራ” (አክርማና ስንደዶ መልቀም ማለት ነው) እና በእንጨት ለቀማ ወቅት ተገናኝተው የውስጣቸውን በዜማ ሲተነፍሱ ፍንጭትነትን ሳያደንቁት አያልፉም፡፡
እሷ፡ “ና ካሮዬ ካሮዬ ካሮዬ”
እርሱ፡ “ነይ ካሮዬ ካሮዬ ካሮዬ”
እንዲህ ነው የሚባባሉት፡፡ “ፍንጭቴ! የኔዋ ፍንጭት! ፍንጭቷ” እያሉ ነው የሚሞጋገሱት፡፡ ዛሬም ጥርሰ ፍንጭት መሆን በወሎ ምድር ያስከብራል፡፡ የቁንጅና ምልክት ነው፡፡
ታዲያ ወሎየዎቹ የሚሞጋገሱበት “ካሮ” ስርወ-ቃሉ ኦሮሚፋ ነው፡፡ ወሎ ግን ወደ አማርኛ አሻገረችውና ሁሉም ሙሐባውን እንዲወጣበት አደረገችው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ “አባወራ”፣ “እመወራ”፣ “ይፋ”፣ ጨፌ፣ ወንበዴ፣ ጭፍራ፣ ዳለቻ፣ ቡሬ፣ ሰንጋ፣ ኮርማ፣ ካሳ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ቃላት ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ የገቡት በወሎ ማህጸን ውስጥ ነው፡፡ የወሎ አማርኛ ዘዬ ከዐረብኛም (በእስልምና በኩል) የወረሳቸው በርካታ ቃላት አሉት፡፡ ለምሳሌ “በረካ”፣ “ጀመዓ”፣ “አጃኢበት”፣ “ሙሐባ”፣ “አውሊያ”፣ “ከራማ”፣ “ከዳሚ”፣ “ዱኒያ”፣ “መጅሊስ” ወዘተ… ወደ አማርኛ የገቡት በወሎ በኩል ትራንዚት አድርገው ነው፡፡ በመሆኑም ነው ዘዬው በውበት የደመቀው፡፡
ወሎዬዎች ደስ የሚሉት በሚናገሩበት ዘዬ ብቻ አይደለም፡፡ የንግግር ቅላጼአቸው (accent) ራሱ በጣም ውብ ነው፡፡ በተለይ “ደ”ን ወደ “ዴ” እያስጠጓት የሚናገሩበት ስልት ለየት ያለ ኪነታዊ ቃና አለው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ እዚያ ሄዶ ለአንድ የወሎ ጉብል ያደረገውን ቃለ-መጠይቅ እንዲህ ጽፎት ነበር፡፡
ጋዜጠኛ፡ ደህና ዋልሽ?
ልጅት፡ ዴህና!
ጋዜጠኛ፡ ኑሮ እንዴት ነው?
ልጅት፡ ዴግ ነው!
ጋዜጠኛ፡ ስምሽን ማን ልበል?
ልጅት፡ ዴብሪቱ
ጋዜጠኛ፡ የአባትሽ ስም?
ልጅት፡ ዴስታ
ጋዜጠኛ፡ የትውልድ መንደርሽ?
ልጅት፡ ዴላንታ
ጋዜጠኛ፡ አውራጃው?
ልጅት፡ ዴሴ
ጋዜጠኛው፡ (በመገረም) እናንተ ወሎዬዎች ለምንድን ነው “ደ”ን እንደ “ዴ” የምትናገሩት ግን?
ልጅት፡ ዴምብ ነዋ!
ወሎ የጥበብ ሀገር ነው፡፡ ወይንም ደግሞ ማሪቱ ለገሰ በአንድ ወቅት እንደተናገረችው “ወሎ የዜማ እናት የቅኔ እህት” ናት፡፡ ከታዋቂ የኢትዮጵያ ቅኝቶች መካከል ሶስቱን ያዋጣችው ወሎ ናት፡፡ አምባሰል፣ አንቺ ሆዬ እና ባቲ በወሎ ምድር ነው የተወለዱት (በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ቅኝቶች አራት ብቻ ናቸው የሚለው እሳቤ ስህተት ነው፤ በአራቱ ውስጥ የማይታቀፉ በርካታ ቅኝቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርበት የማውቀውን የሀረሪ ቅኝትን መጥቀስ እችላለሁ)፡፡ ታዲያ አምባሰል፣ አንቺ ሆዬ እና ባቲ የተሰኙት ቅኝቶች የሚያምሩት በወሎዬዎች ሲዘፈኑ ነው፡፡ አምባሰልን በማሪቱ ለገሰ እነሆ!
አመለኛው ልቤ መጓዝ የለመደ
አመለኛው እግሬ መሄድ የለመደ
ሐይቅን ሲዞር ውሎ ውጫሌ ወረደ፡፡
እንዴትነሽ ውጫሌ እንደምን ነሽ ጢሳ
የተቋደስንብሽ ፍቅር እራት ምሳ፡፡
አምባሰል ለገደል መች ያሽሟጥጡታል
ፈረስ ባያስጋልብ ሰው ይወጣበታል፡፡
ምንኛ ደግ ነው ውሃ መሰለል
አያልሰው ወስዶ ዘንድሮ አምባሰል፡፡
የአምባሰል ማር ቆራጭ ይወርዳል በገመድ
አደራ ቢሰጡት ይበላል ወይ ዘመድ፡፡
እውነት ነው! በኢትዮጵያ ውስጥ ስም ያላቸው በርካታ ዜመኞችን በማዋጣት ረገድ ወሎ ጉልህ ስፍራ አላት። አሰፋ አባተ፣ ባህሩ ቀኜ፣ ዘሪቱ ጌታሁን (ትዝታ በፖስታ)፣ ሀብተ ሚካኤል ደምሴ፣ ማሪቱ ለገሰ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ አያሌው መስፍን፣ ሻምበል በላይነህ፣ ጋሻው አዳል፣ ጸሐይ ካሳ፣ ዚነት ሙሐባ፣ መሐመድ አወል ሳልህ፣ መሐመድ ኮይስ፣ ወዘተ….. ስንቱ ተቆጥሮ ይዘለቃል?…ወሎዬ የሆኑትን ከመጥራት ያልሆኑትን ማውሳት ይቀላል፡፡
ወሎ የምሁራን ቋት ነው፡፡ የሀገር ግንባር የሆኑ ሺ ምንተሺህ ምሁራንና ፖለቲከኞች ፈልቀውበታል፡፡ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ግንባር ቀደም የነበሩት ዋለልኝ መኮንን፣ ነገደ ጎበዜ፣ ብርሃኑ እጅጉ ወዘተ… ከወሎ ነው የተገኙት፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርጥ ምሁራን ተብለው የሚታወቁት አለማየሁ ሀይሌ አባ መርሳ፣ ሑሴን አሕመድ፣ ሞገሴ አሸናፊ፣ አድማሱ ገበየሁ፣ አረጋ ይርዳው (የሚድሮኩ)፣ ጎበዜ ጣፈጠ (የዶ/ር ነገደ አባት) ወዘተ ወሎዎች ናቸው፡፡ ኤርትራዊው አስመሮም ለገሰ እና የትግራዩ ሰለሞን እንቋይ ጭምር የተወለዱት በወሎ ምድር ነው፡፡
ወሎ የታሪክ ሀገር ነው፡፡ የላሊበላ አድባራት፣ ግሸን ማሪያም፣ የጀማው ጥንታዊ መስጊድ፣ የከሚሴ ኸልዋዎች፣ ቴዎድሮስ አለምን የተሰናበተበት የመቅደላ ምሽግ፣ ምኒልክና ጣሊያን ጣጠኛውን ውል የተፈራረሙበት የውጫሌ አምባ፣ የዮሐንስ የሀይማኖት ፖሊሲ ሺዎችን በሰይፍ የቀረደደበት የቦሩ ሜዳ፣ ንጉሥ ሚካኤል ሺ ሰዎችን ግብር ያበላበት የአይጠየፍ አዳራሽ ወዘተ… ሁሉም በወሎ ምድር ነው የሚገኙት፡፡
ወሎ የዑለማ ሀገር ናት፡፡ የኢትዮጵያ አዝሀር የተባለላት የዒልም ሀድራ! እርግጥ ሀረር በዚህ ላይ ተቃውሞ አቅርባለች፡፡ “አዝሀር ሺህ ዓመት የኖርኩት እኔ ጉብሊቷ ነኝ” ብላለች! ክርክራቸው ከኛ በላይ ስለሆነ ለምሁራን ምክር ቤት አስተላልፈነዋል (ሀረሪነቴ እዚህ አላስቻለኝም ቂቂቂቂቂቂ)፡፡ ይሁንና ወሎ “አዝሀር” የመሆኗ ክብር ቢነጠቅባት እንኳ የኢትዮጵያ “መዲና ዩኒቨርሲቲ” የመባልን ያህል ትከበራለች፡፡ እስቲ ተመልከቱ እርሷ ያፈራችውን ዑለማ!… ከኢፋት ምድር ጀምሮ እስከ ራያ ድረስ በተንጣለለው ክልል ውስጥ ያለው ጎራና መንደር ሁሉ የየራሱን አንድ ቱባ “ዓሊም” አበርክቷል፡፡ ሼኽ ጠልሃ ጃዕፈር (ኢፋት)፣ ሙፍቲ ሲራጅ (ራያ)፣ ሼኽ ዳኒይ (ዳና)፣ ሐጂ ከቢር (ከሚሴ አውራጃ)፣ ሼኽ ዑመር ቡሽራ (ቃሉ አውራጃ)፣ የጀማው ሼኽ (ደሴ ዙሪያ አውራጃ)፣ የዶርቃው ሼኽ ወዘተ……. እያልን መዘርዘር እንችላለን፡፡ ቅዱስ ቁርኣንን በአማርኛ የተረጎሙት ሁለቱም ዓሊሞች ወሎዎች ናቸው- ሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ እና ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፡፡
ወሎ የሽፍታ ሀገር ነው፡፡ በግብርና በስፍር ሲማረር ይሸፍት ነበር፡፡ በዚህ በኩል ቀዳሚው ተጠቃሽ የከላላው “ስንዴው ሼኽ” ናቸው፡፡ እንዲህ ተብሎላቸዋል ይባላል፡፡
ከላላ ነው ቤቱ ከላላ ነው ቤቱ
ከላላ ነው ቤቱ ያበራል ጥይቱ፡፡
ስንዴው ሼኽዬ ፈረሱ ነጫጭ
ይወረወራል እንደ ልምጭ።
ወሎ የትንግርት ሀገር ናት! የትንግርቶች ትንግርት የሆኑ ዓጃዒባትን ያስገኘች አስገራሚ ሀገር፡፡ ትልቁ የወሎ ትንግርተኛ ደግሞ ሼኽ ሁሴን ጂብሪል ነው፡፡ ለመቶ ዓመታት ጥቂት እስኪቀር ድረስ ኖሯል፡፡ በዓለም ላይ ወደፊት የሚሆነውን ሁሉ አላህ አሳውቆታል አሉ፡፡ እናም በግጥም ተናገረው፡፡ አላህ ከራማውን እንዴት እንደሰጠው እና ወደፊት ከዱኒያ እንዴት እንደሚሰናበት ሲናገር እንዲህ ብሏል ይባላል፡፡
ሰው ያልነካው እጣ ጀሊሉ ሰጠን
መጭውን አየነው ጉድ ዓጃኢቡን
ዓለም ስትስቅብኝ እኔም ሳቅኩባት
ካለፉት በስተቀር ያሉት በሐያት
ተከትቦ አየዋለሁ ስሙን ወደፊት
ገና ከሆድ ሳለ ሳይከተብ በፊት።
አዱኒያ ደህና ሁኚ እኔ ጋለብኩሽ
ምስክሬ አንቺው ነሽ ወደጅ እንዳትረሺ
በሐቅ መስክሪ እንደኔ አትዋሺ
የሚያውቀኝ ብዙ ነው እንዳትወቀሺ
እኔን በታች አርገሽ በላይ ካረገሽ
እኛም ልንወድቅ እሷም ላትሸሽ
ስሟን ብትጠይቀኝ አለችኝ ወራሽ
ስሜን ብትጠይቀኝ አልኳት ነኝ ብላሽ
ኋላ እንዲህ ልትሰድበኝ ልትለኝ በስባሽ
በዘጠና ስምንት ገላችን ፈራሽ።
ዘመኑን ወራቱን የሚያጫውታችሁ
ሑሴን ጅብሪል ሄደ ተመሀከላችሁ።
አቲቃ አሕመድ ዓሊ የምትባል የወሎ ጉብል በታሕሳስ ወር 2006 ዓ.ል. በመስመር ላይ እየመጣች ትጨቀጭቀኝ ነበር፡፡ “እስቲ በብዕርህ እኛን ያፈራውን የወሎ ምድር በማስመልከት አንድ ነገር ጻፍልን” ትለኛለች፡፡ በእርሷ ቀስቃሽነት ነው እንግዲህ ይህንን ጽሑፍ የከተብኩት።
አሁን የኢትኖግራፊ ሽርሽራችንን ልናሳርግ ነው። በማሳረጊያ ላይ አቲቃን እርሷ በምታውቀው ግጥም እንደዚህ ብላት ምን ትለኝ ይሆን?
ኧረ ደሴ ደሴ ገራዶ ገራዶ
አለቀልሽ ልቤ ተንዶ ተንዶ፡፡
እኚህ ወሎዬዎች አበላል ያውቃሉ
ተገብስ እንጀራ ላይ ሳማ አርጉ ይላሉ፡፡
(ቂቂቂቀቂቂቂቂ ወሎዎች ነፍስ ናቸው! እንዲህ ብለው ስለራሳቸው ይገጥማሉ፡፡ “ሳም አርጉ ይላሉ”! ፐፐፐፐፐፐ)
በመጨረሻም “አፈንዲ ሙተቂ” ለየትኛውም ህዝብ መጥፎ እይታ ኖሮት አያውቅም። ሁሉንም ህዝብ እንደ ራሳችን ህዝብ ነው የምንወደው (እኛ እንደ ጃንሆይ የሀረር ሰዎች በመሆናችን ሲያሻን “እኛ” እያልን እንጽፋለን)። ይህንን ያስተማረን ደግሞ እኛን ወልዶ በፍቅር ያሳደገን የኦሮሞ ህዝብ ነው። እኛን የሚዘልፉት እኛን በጭራሽ የማያወቁ ወጀላቴዎች ናቸው። ፈጣሪ አደብ ይስጣቸው።
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 9/2006
በሸገር ተጻፈ።
(ይህ ወግ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ድሬ ዳዋ” በተሰኘው መጽሐፌ ውስጥ ተካትቷል)።
ምስጋና ለጸሃፊው