“በአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ኤርፖርት ዛሬ ቀትር አካባቢ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር ሃይል የሆነ አንድ ሄሊኮፕተር በቴክኒክ ችግር መጠነኛ አደጋ እንዳጋጠመው ከስፍራው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል” በማለት በትናንትናው ዕለት የተበተነው ዜና ከዕውነት የራቀ መሆኑንን የኢፌዴሪ መከላከያ ማኒስቴር አስታውቋል።
ሁነኛ ምንጭ ሳይጠቅሱ የተለያዩ ሚዲያዎች በማህበራዊ ገጾቻቸው በአደጋው ምክንያት የአየር በረራዎች መስተጓጎላቸውን ዘግበዋል። “በርካታ ሰዎች check-in ጨርሰው በረራ ዘግይቶባቸዋል” ብለዋል። “ከሰዓት በኋላ ሁሉም በረራዎች እንደተሰረዙ ታውቋል። እስካሁን ከሚመለከተው አካል የተሰጠ መረጃ የለም” የሚል መረጃ በቅብብል አሰራጭተዋል።
ይህን ተከትሎ የጉዳኡ ባለቤት የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ ማኒስቴር አስታውቋል እንዳለው ምንም የተፈጠረ አደጋ የለም። “የኢፌዴሪ አየር ኃይል ካሉት ቤዞች አንደኛው ምድብ የሆነው ባህርዳር የሚገኘው የምዕራብ አየር ምድባችን ነው። በትላንትናው ዕለት በነበረው የአየር ኃይል የምድብ ልምምድ ምክንያት መደበኛ የአየር መንገድ በረራ ለጥቂት ጊዜያት ተቋርጦ ነበር” ሲል ማብራሪያ ሰጥቷል። ልምምድ ከመካሄዱ ውጭ የፈጠረ አንዳችም ነገር እንደሌለ አስታውቋል።
“ይሁን እንጅ” ይላል የኢፌዴሪ መከላከያ ማኒስቴር ያሰራጨው መረጃ፣ የአየር መንገድ ተሳፋሪዎች የተወሰነ የጉዞ መዝገየት ተንተርሶ፣ የተሰራጨው ዜና ፈጠራና አጋጣሚውን ለፕሮፓጋንዳ የመተቀም ጉዳይ እንደሆነ አመልክቷል። “አጋጣሚ በመጥቀስ ሄሊኮፕተር ተበላሸ፣ ተከሰከሰ በሚል የማደናገሪያ ሃሳብ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ እየተራገበ ይገኛል” ሲል ያስታወቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ማኒስቴር፣ “መደበኛ በረራ ለውስን ጊዜያት ተቋርጦ የነበረው በተገቢው መንገድ ስራ የጀመረ ሲሆን የምዕራብ አየር ምድብም ልምምዱን ስኬታማ በሆነ መንገድ አጠናቋል” ብሏል።
“አሁን እያየን ያለነው ምናልባትም የጠላት ሁለንተናዊ አቅምና የፕሮፖጋንዳ መስክ መክሰርና መከስከስ ካልሆነ በስተቀር የተከሰከሰ ሄሊኮፕተር እንደሌለ ማሳወቅ እንወዳለን” እንወዳለን ሲል ሄሊኮፕተር ላይ አደጋ ደረሰ፣ ተከሰከሰ በሚል የተሰራጨውን ዜና፣ የጠላት ሃይል መመናመን፣ የፕሮፓንጋንዳ ውድቀትና ክስርተ እንደሆነ ገልጿል።