በጃልመሮ የሚመራው የኦነግ ጦር ወደ ማገገሚያ ከመግባት ወይም አፈግፍጎ ድንበር ላይ በመመሸግ ተሃድሶ ካላደረገና በአዲስ መንፈስ ትግል የመጀመር ዕቅድ ካልነደፈ በስተቀር አሁን ላይ መሸነፉን በአመራር ላይ ያሉ ለኢትዮሪቪው ገልጸዋል። የትጥቅ ትግሉ ተዓምር ካልተፈጠረ በቀር ውጤት አይጠበቅበትም።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ቄለም ወለጋ እና የአርሲ ዞኖች ነዋሪዎች “ሰላምን ለማጽናት” በሚል ያደረጉትን ሰልፍ አስመልክቶ አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ የተለያዩ ተቃዋሚዎች ነቀፋ ሰንዝረዋል። ሰልፉንም መንግስት ያዘጋጀው እንደሆነ ጠቅሰው ትችተዋል። ሰልፎቹ የብልጽግናን መውደቅ መቃረብ የሚያሳዩ እንደሆነም ያለፉት መንግስታት ተግባር በማጣቀስ ” ሊያልቅ ሲል ህዝብ ማሰለፍ የተለመደ የቀደሙት መንግስታት ሁሉ ስታራቴጂ ነው” ብለውታል።
በሕዝባዊ ሰልፎ ላይ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን “ሰላምን ለማጽናት የበኩላችንን እንወጣለን፣ በሰላም እጦት ምክንያት የህዝቡ ስቃይ ሊቆም ይገባል፣ ወደ ሰላም መመለስ መሰልጠን ነው” የሚሉና የአምልኮ መልክ ያላቸው ልመናዎች በአደባባይ ሲያቀርቡ በቴሌቪዥን መታየታቸው ይታወሳል።
ይህንኑ ሰልፍ አስመልክቶ የኦነግ አመራር ለሆኑና ለጊዜው በይፋ ስማቸውን ሳይጠቅሱ ለአዲስ አበባ የኢትዮሪቪው ተባባሪ እንዳሉት የኦነግ ጦር ለሁለት ከተከፈለ በሁዋላ ነገሮች ተበላሽተዋል። መከፈላቸውን ማንም መደበቅ እንደማይቻለውና ሁለቱም ወገኖች እንደሚረዱት፣ እነሱም በግልጽ ያስታወቁት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ” አሁን ላይ ነገሩን ያበላሸው የጃል ሰኚ ኃይል ብልጫውን መያዙ ነው። የጃል መሮው ወገን ራሱን ዳግም በረሃ መልሶ ተሃድሶ ካላደረገ በስተቀር አሁን ላይ በውጊያ የሚፈይደው አንዳችም ነገር እንደማይኖር አምነናል” ብለዋል።
“ጃል ሰኚ ይዞት የተገነጠለው ኃይል በቁጥር ከጃልመሮ ባይበልጥም ዋናዎቹ ልምድ ያላቸውና በድርጅቱ አስተሳሰብ የበሰሉትን አውራ መሪዎች በመያዙ በጃል መሮ ኃይል ላይ የበላይነቱን ይዟል” ያሉት እኚሁ መረጃ ሰጪ፣ ጃል መሮ ኃይሉን ይዞ ሙሉ በሙሉ ወደ በረሃ የሚወጣበትን የትግል አግባብ እንደ መዳኛ አማራጭ መያዙን ገልጸዋል።
ጃል መሮ አዲስ ስትራቴጂ መከተሉን ገልጾ ኃይሉ ወደ መሃል አገር መጠጋቱን አመልክቶ ነበር። ጃል መሮ ወደ ሸዋ መንቀሳቀሱን ጠቅሶ ማስታወቁን ተክትሎ የኦነግ ሰራዊት በግልጽ መከፈሉ በመሪዎቹ አንደበት ይፋ ሆኗል። ይህ ልዩነት መንግስት ሙሉ ማጽዳት መጀመሩን ይፋ ባደረገበት ቅጽበት መሆኑ በርካቶችን “ምን እየተካሄደ ነው?” በሚል እንዲጠይቁ አድርጓቸው ነበር።
የእነ ጃል ሰኚ ወገን ከመንግስት ጋር መስማማቱን ገልጸው ቀደም ሲል የተለያዩ ክፍሎች መናገራቸውን አስመልክቶ፣ ራሱ ጃል ሰኚ በገሃድ ስለሰጠው መግለጫ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ” አስቀድመን እናውቅ ስለነበር ዜናው አልገረመንም። ውድቀቱ እንደሚመጣ አውቀን ለመተገን ብዙ ጥረናል። አልሆነም። የነ ጃል ሰኚ ቡድን አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ከመንግስት ኃይሎች ጋር ስምምነት ፈጥሯል። ኦነግ አያውቃቸውም። እነሱም ኦነግን አያውቁትም። ከመንግስት ጋር የገቡት ውል መጨረሻው የሚታይ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥትተዋል። አያይዘውም እንደ አንድ የድርጅቱ አባል ሃፍረት ሆኖ የሚቀርና ደጋፊን የሚያስተክዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ሰላማዊ ሰልፉ በአስገዳጅ የተደረገ ስለመሆኑ ሲናገሩ ” ይህን ማለት ዋጋ የለውም። መንግስትም ቢጠራው አይገርምም። ሰው ግን ሰላም እንደሚፈልግና ጦርነት እንደሰለቸው ነው የተናገረው ይህ እውነተና ስሜት ነው። አሁን ላይ በመላው አገሪቱ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው። ይህን ማስተባበል ጥቅም የለውም” ብለዋል። አክለውም፣ “ሕዝብ ሰላም እንደሚፈልግ መናገሩ ሳይሆን እንዴት ድርጅቱ ሪፎርም ሊያካሂድ እንደሚችል ነው መታሰብ ያለበት። እግረመንገዱንም የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችን የማስቀተል ዕድል ካለ ውጤት እንዲቃና ከቀደሙት ስህተቶች ተምሮ መንቀሳቀስ ነው የሚበጀው” ሲል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከትህነግ ጋር የነበረውን ወታደራዊ ትግል ህብረት አስመልክቶ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በሁዋላ ምን እየሆነ እንደሆነ ተጠይቀው ” እሱን ተወው፣ ትህነግ ለድርድር ሲቀመጥ የኦሮሞ ጦርንም ማካተት ነበረበት። የዛኔ ጥሎን ራሱን አዳነ። ከዚያ በሁዋላ ምን ዓይነት ነገር እንዳለ አላውቅም”
ከዚህ ቀደም ” በኦሮሚያ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እኛ ዝግጁ ነን ” በማለት ጃል ሰኚ ነጋሳ ለቪኦኤ ኦሮምኛ አቋማቸውን አስመልክቶ የሰጡትን መግለጫ ማስነበባችን ይታወሳል። እንደዚህ ነበር ያሉት
” በጃል መሮ (ኩምሳ ድሪባ) ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ራሳችንን አግልለናል ” ሲሉ የማዕከላዊ ዞን የቀድሞ አዛዥና የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጃል ሰኚ ነጋሳ በይፋ ያስታውቁት ለቪኦኤ አማርኛ ነው። የኦሮሚያ ክልል ሸኔ የሚለው ይህ ታጣቂ ቡድን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንደ ድርጅት መንቀሳቀስ በማይችልበት ደረጃ መድረሱንና በወራት ዕድሜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚከስም ሰሞኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ከተመረጡ መገናኛ ብዙሃን ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት ጃል ሰኚ ባለፈው ረቡዕ ዕለት ወጥቶ ሲዘዋወር የነበረው የማዕከላዊ ዞን ዕዝ በጃል መሮ ከሚመመራው ቡድን መነጠሉን የሚገልጸው መግለጫ አስመልክቶ ” አዎ የኛ የቡድናችን ነው ” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ቪኦኤ የተመረጡ የተባሉት መገናናዎች ግን አልተዘረዘሩም።
ጃል ሰኚ ” የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት ህግና ደንብ መተዳደሪያ ደንብ የሌለው ድርጅት ነው ” ብለዋል። “ጥፋት ሲሰራ ተጠያቂነት የሌለበት ድርጅት ነው፣ ህግና ደንብ ሲኖር አንዱ ሲያጠፋ ለማስተካከል የሚያስችል ህግ ይኖራል ግን አሁን በአንድ ሰው የሚመራ መሆኑን አይተንና ተረድተን እንዲሁም ወደ ድርጅቱ ህግና ደንብ ተመልሰን እርስ በእርሳችን እናስተካክል ብለን ለኦሮሞ ህዝብ ባለን ክብር ባህልና ወጉን ጠብቀን ነው በህዝቡ ውስጥ የምንቀሳቀሰው ከዚህ ባለፈ በህግ ሊታይ ይገባል፤ በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ በ2017 በተደነገገው ህግና ደንብ መመራት አለብን ብለን ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር ጋር መቀጠል አንችልም ብለን ነው መግለጫ ያወጣነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
” አሁን ዋና አዛዥ የምንለውን ወደፊት ኦሮሚያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ጋር ተነጋግረን ነው የምንመርጠው ፤ ስለዚህ ከዚህ በኃላ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አይወክለንም ” ብለዋል። ጃል ሰኚ በኦሮሚያን ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ፈቃደኛ መሆናቸውን ሲገልጹ ” እኛ ዝግጁ ነን” በማለት ነው።
” በሰላማዊ መንገድ ስንል በድርጅቱ ፕሮግራም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የቀጠለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉም ይታትራል። ስለዚህ መንግሥት ከሰላማዊ መንገድ ከእኛ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ከሆነ እኛም ለመነጋገር ዝግጁ ነን ፤ እንዴት ነው የምንነጋገረው ? የት ነው ? ከማን ጋር ? የሚለውን የውይይቱ ጊዜ ሲደርስ ይገለጻል ” ብለዋል።
አሁን ላይ ከመንግሥት ጋር ድርድር እየተደረገ እንደሆነ ተጠይቀው ” አሁን ከመንግሥት ጋር የጀመርነው ግንኙነት የለም ” ሲሉ መልሰዋል።
ያነጋገርናቸውን የኦነግ አመራር ሙሉ ቃለ ምልላሳቸውን እናትማለን።