በተጠቀሰውና አሳዛኝ ግፍ በተፈጸመበት አካባቢ አብሮ መኖር፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መነገድ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች መጣመር፣ በትዳር መተሳሰር፣ በደስታና በሃዘን አብሮ መሆን፣ አንዱ የሌላውን በዓል አብሮ ማክበር … ወዘተ ችግር ሆኖ አያውቅም። በሰላም በሚኖር ሕዝብ መካከል የገቡ የሁለት ወገን አንጋቾች የህን ህዝብ መለየት ብቻ ሳይሆን፣ እያሰቃዩት፣ እያረዱት፣ ንብረቱን እያወደሙ፣ እየደፈሩ፣ እያስገበሩ፣ እርሻና ቤቱን እያቃጠሉ ይኖራሉ። ይህ ሁሉ ዝርዝር የተሰማው አሁን በመጨረሻ ለሰሚውም ሆነ ለተመልካች ግራ የሚያጋባ የግፋ ፋይል ይፋ ሲሆን ነው።
ደራ ሰሜን ሸዋ እየሆነ ያለው ሁሉ ዓላማው ምንድን ይሆን? ፋኖ ይገድላል፣ ሸኔ ይገድላል። የመንግስት ኃይሎች ሲደርሱ የሚሸሹት ሽፍቶች የሚፈጽሙት ወንጀልና ግፍ ምን ዓይነት ዓላማ ለማሳካት እንደሆነ እነሱም፣ መሪዎቻቸውም፣ በውጭ ያሉት የሚዲያ ነጋዴዎችና ” የውጭ አገር አስተባባሪና ተወካይ ነን” የሚሉት በይፋ ሲናገሩ አይሰማም።
የመንግስት ኃይል ሲደርስ ህዝቡን “ሽፍታ ትቀልባላችሁ” በሚል ያጉላል። የእነሱን እገር ተከተው የሚመጡት ሽፍቶች ከላይ የተጠቀሰውን ይፈጽማሉ። የዚህ ህዝብ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው? ህዝብ ተንገፍግፏል። ንጹሃን እየተገደሉ በወንዙና ስርቻው ሬሳቸው ይጣላል። ቢቢሲ የነጋገራቸው እንደመሰከሩት የሚፈጸመው ሁሉ ለመስማትም የሚቀፍ ነው።
የመብት ተቆርቋሪዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ለወትሮው ኮሽ ሲል ድምጻቸውን የሚያሰሙ ተቋማት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሽማግሌዎች፣ የዕምነት ተቋማት ወዘተ ትንፍሽ ያላሉበት የደራ ህዝብ እልቂት ህዝብ አስቆጥቷል። ዓላማው ህዝብን ብስጭት ውስጥ በመክተት የኃይማኖትና የዘር ፍጅት ለማስነሳት እንደሆነ እየታወቀ፣ ጉዳዩን ተረባርቦ በማውገዝና በመተባበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማምከን ከመረባረብ ይልቅ ዝምታው በራሱ ሌላ ቁጣ የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።
ከስር ያለው የቢቢሲ ዘገባ ነው።
በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ አንድ ወጣት በታጣቂዎች ተይዞ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከታየ በኋላ በርካቶችን አስቆጥቷል።
በአካባቢው በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የሚጋጩት የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ይንቀሳቀሳሉ።
ጉዳዩን በሚመለከት ቢቢሲ ኦሮምኛ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ግድያው የተፈጸመው በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ “የፋኖ ታጣቂዎች” መሆኑን ይናገራሉ።
ድርጊቱ የተፈጸመው ከሁለት ወራት በፊት ነው የሚለው ዳንኤል ገመዳ ወደ ሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ አምርቶ የሟችን ቤተሰቦች ማነጋገሩን ለቢቢሲ ገልጿል።
ግድያው የተፈጸመበት ወጣት ደረጀ አማረ ተስፋ እንደሚባል እና የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ቤተሰቦቹ የሄደ እንደነበር ዳንኤል ጨምሮ አስረድቷል።
በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም የፋኖ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ይጋጫሉ።
ቢቢሲ ከኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ የደራ ወረዳ አስተዳደር እና የፀጥታ ኃላፊዎች ግድያውን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
አቶ ኃይሉ አዱኛ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ከሆነ ግን “ኦሮምኛ እና አማርኛ የሚናገሩ ጽንፈኞች ናቸው ይህንን ድርጊት የፈጸሙት” ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ከፋለው በበኩላቸው ይህ ድርጊት ወደ ተፈጸመበት ስፍራ በመሄድ ሁኔታውን አጣርተው እንደሚናገሩ ለቢቢሲ ኦሮምኛ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን እንደሰማ ገልጾ ማጣራት መጀመሩን እና የደረሰበትን ውጤት ወደፊት እንደሚያሳውቅም ገልጿል።
ቢቢሲ ቪዲዮው መቼ እና የት እንደተቀረፀ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
በአሰቃቂው ቪዲዮ ላይ የሚታየው የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ እና የዓመቱን ትምህርት አጠናቅቆ ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቹ ያመራው ደረጀ እንዲሁም ጓደኛው ከማል ሁሴን በአንድ ቀን መገደላቸው ተነግሯል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ በከጀማ ተራራ ሸሽተው ነበር። ደረጀ እና ሌሎች ግን በቀያቸው የቆዩት በበረት ታስረው የሚገኙትን እንስሳትን ለመጠበቅ ነበር።
በአካባቢው የነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች ደረጀ እና ከማል ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የደረጀ አባት የሆኑትን አቶ አማረ ተስፋ ቶላን አግኝቼ አነጋግሬያለሁ የሚለው ዳንኤል፣ “ያን ቀን አሳድደው እግሩን ተኩሰው መትተው ከያዙት በኋላ ሳርኩላ ወደ ሚባል ቦታ ወሰዱት። እዚያ ቦታ ነው የፋኖ ታጣቂዎች በብዛት የሚንቀሳቀሱት” ይላል።
ደረጀ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ አስከሬኑ ለአውሬ የተጣለው እዚያ ቦታ መሆኑን የተናገሩት አባትየው፣ የልጃቸውን መገደል ቢሰሙም አስከሬኑን አግኝተው መቅበር አለመቻላቸውን ጨምሮ ገልጿል።
የደረጀ እናት እና አባት በልጃቸው ሞት ምክንያት አእምሮ ጤናቸው መቃወሱን ዳንኤል ይናገራል።
“የደረጀ እናት አእምሮአቸው ተጎድቷል እና አትናገርም። ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። ለማንም አይመልሱም።”
ደረጀ ለቤተሰቡ ታናሽ ልጅ ሲሆን ወንድሞቹ እና እህቶቹ አግብተው ከቤት በመውጣታቸው እናት አባቱን ለማገዝ በቤት ያለ ብቸኛ ትንሽ ልጅ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።
ቢቢሲ በደራ ወረዳ ቱሉ ጉዳ መንደር በሼህ ሁሴን መስጂድ አቅራቢያ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪ በርካታ የፋኖ ታጣቂዎች በሼህ ሁሴን መስጊድ አካባቢ እንደሚኖሩ ያስረዳሉ።
እኚህ ነዋሪ በተለያየ ጊዜ የፋኖ ታጣቂዎች ሰዎችን ገድለው ወደ ወንዝ እንደወረወሩ ይናገራሉ።
“ብዙ ጊዜ ለምነን ሬሳውን እንቀብራለን፤ ሳይቀበሩ የቀሩም አሉ።”
በአካባቢው ባለው ተደጋጋሚ ግጭት እና ጥቃት የተነሳ ያመረቱት ምርት መቃጠሉን የሚናጉት እኚህ ነዋሪ ከየቤታቸው ሸሽተው መሄጃ ያጡ ነዋሪዎች በመስኪዱ ዙሪያ ተሰብስበው ለመኖር መገደዳቸውን ገልጸዋል።
እኚህ ግለሰብ አክለውም ታጣቂዎች ደረጀን ለመግደል ሲዝቱ እንደነበር መስማታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪ ታጣቂዎችን የመንግሥት ኃይሎች ከመጡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላትን ትመግባላችሁ በሚል ጥቃት ያደርሱብናል በማለት ፍርሃት እንዳለባቸው ይናገራሉ።
በተጨማሪም የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ከመጡ ደግሞ ቤት ያቃጥላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ይገድላሉ ሲሉ ነዋሪዎች መናገራቸውን ዳንኤል ይናገራል።
ለዚህም ማሳያ አንድ የአካባቢው ነዋሪ “ፋኖ ታጣቂዎች” ወደ ቤታቸው መጥተው አንደነበር ገልጸው “ባለቤቴ እና አማቴ ቤት ነበሩ። አማቴ ልጄን ደብቃ ከአባቷ ጋር ወጥታለች ብላ አሸሸቻት። እርሷን መትተዋት ባለቤቴን ይዘዋት ወጡ” ይላሉ።
ግለሰቡ ባለቤታቸውን ለማስለቀቅ 10 ሺህ ብር ቢከፍሉም ከቀናት በኋላ ግን ባለቤታቸው በታጣቂዎች መደፈራቸውን መስማታቸውን ለቢቢሲ ኦሮምኛ ተናግረዋል።
“መጀመሪያ አንደተደፈረች ደብቃ ነበር። ነገር ግን የአካባቢው ሰዎች ማውራት ሲጀምሩ ነው ለእኔ የነገረችኝ። እኔ እንዲለቋት ብዬ 10 ሺህ ብር ከፍዬ ነበር።”
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከሚፈጽሙት የንብረት ውድመት እና ዘረፋ በተጨማሪም በተደጋጋሚ የመድፈር ጥቃቶች ይፈጽማሉ ሲሉ ነዋሪዎች ይከሳሉ።
በችግር ላይ የሚገኙት ነዋሪዎች ተጨማሪ ስጋት
ሌላ በአካባቢው በሚገኝ መስኪድ ውስጥ ከሰኔ ወር ጀምሮ ተጠልለው የሚገኙ አንድ ነዋሪ “መውጫ መንገድ የለም። ለመንግሥት ይግባኝ ለማለት ምንም መንገድ የለም። መንገድ ዘግተው ያሉት እነርሱ [የፋኖ ታጣቂዎች] ናቸው” ይላሉ።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ዘርፈው፣ የተረፈውን በማቃጠላቸው በአሁኑ ጊዜ የሚበላ ነገር በእጃቸው አለመኖሩን ይናገራል።
“በፊት በዘር እና በሃይማኖት ሳንከፋፈል አብረን እንኖር ነበር” የሚሉት እኚሁ ግለሰብ፣ “በጾም ወቅትም አብረን ጾምን ነበር። በኢሬቻ ጊዜ እንኳን ከአማራ ተወላጆችጋር አክብረናል” ሲሉ በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ የነበረበትን ትስስር ይገልጻሉ።
“አሁን ግን እነዚህ ታጣቂዎች መጥተው አብረን የምንኖረውን ሰዎች በእኛ ላይ አነሳሱብን” በማለት የተለያዩ ሰቅጣጭ ጥቃቶች እና ግድያዎች መፈጸማቸውን ለቢቢሲ ኦሮምኛ በዝርዝር አስረድተዋል።
ሌላው የደራ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው ከፍርሀት የተነሳ ማገዶ ለመልቀም እንኳ የምንሄደው በጋራ ነው ይላሉ።
ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያስረዱ “ምናልባት አንዱ እንኳ ቢያዝ ጮኽን ለማስለቀቅ በሚል ነው በጋራ የምንሄደው።”
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በቀን አንድ ጊዜ እንኳ ለመመገብ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት መንግሥት የእርዳታ እህል ወደ ስፍራው ቢልክም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እጅ መግባቱን ይናገራሉ።
መንግሥት ጉዳዩን በሚመለከት እስካሁን ድረስ ያለው የለም።
በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች በሚደርሱ ጥቃቶች የተነሳ በርካቶች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የፌደራል መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የገባውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሁለት ዙር በታንዛኒያ ያካሄደው ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።