የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአሜሪካ እና ብሪታኒያ ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ዩክሬን ከኔቶ አባል ሀገራት እና አሜሪካ በታጠቀቻቸው የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች ሩሲያ ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ነው፡፡
ጥቃቱን አስመልክቶ ፑቲን በሰጡት መግለጫ ፣አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ አርሚ ታክቲካል በተባለው ዘመናዊ ሚሳኤል ሩሲያ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ሩሲያ አዲስ የስትራቴጂክ ሚሳኤሎችን በመጠቀም የአፀፋ ምላሽ መስጠቷን እና በአፀፋ ጥቃቱ የሩሲያ ባላስቲክ ሚሳኤል የዩክሬን የጦር መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ለዩክሬን መሳሪያ በመላክ ጥቃት እንዲፈፀም ለሚያደርጉ ሀገራት ሞስኮ ምላሽ የመስጠት መብት አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሩሲያ ጦር ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ባደረጉት አሜሪካ እና ብሪታኒያ ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ሞስኮ እንደአስፈላጊነቱ አዳዲስ የሚሳኤል ስርዓቶችን ተግባራዊ ልታደርግ እንደምትችልም አመላክተው፤ ጦርነቱን በንግግር ለመፍታት ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ሲኤንቢሲ ዘግቧል።
ኔቶ
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመቸው የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ሀገሪቱን ከመደገፍ እንደማያስቆመው አስታወቀ፡፡
ሩሲያ በትናንትናው እለት ከድምጽ ፍጥነት በአስር እጥፍ የሚልቅ አህጉር አቋራጭ የሃይፐርሶኒክ ባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ዩክሬን ላይ መፈጸሟን ተከትሎ ኔቶ ቃል አቀባይ ፋራህ ዳክላላህ እንደገለጹት፤ የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት ኔቶ ለዩክሬን የሚያደርገውን ድጋፍ እንደማያስቆመው አረጋግጠዋል።
ሩሲያ ከአስትራካን ግዛት ያስወነጨፈችው ሚሳኤል በ15 ደቂቃ ውስጥ የዩክሬኗን ድኒፕሮ ከተማን መምታቱን የዩክሬን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለኔስኪ የሩሲያ አዲሱ የሚሳኤል ጥቃት የጦርነቱን መስፋት እንደሚያመላክት ገልጸው፤ አጋሮቻቸው ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ በአስፋላጊ ጉዳዮች ሁሉ ከዩክሬን ጎን መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ቻይና ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርባለች፡፡
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አዲሱ የሀይፐርሶኒክ ባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃት አሜሪካ በግዴለሽነት ለፈጸመችው ስህተት ምላሽ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ – ሹመት
የአሜሪካ 47ኛው ፕሬዚዳንት ተደርገው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ አንጋፋዋን አቃቢተ ህግ ፓም ቦንዲን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማድረግ ሹመት ሰጡ፡፡
ትራምፕ ሹመቱን የሰጡት ቀደም ሲል ዕጩ አድርገው የመረጧቸው ማት ጋኤዝ በተነሳባቸው ተቃውሞ ሃላፊነቱን እንደማይቀበሉ ካሳወቁ በኋላ ነው።
ፓም ቦንዲ ረጅም ዓመታትን በህግ አገልግሎት ላይ የሰሩ ሲሆን የፍሎሪዳ ግዛት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመሆንም አገልግለዋል፡፡
ትራምፕን በአደባባይ በመደገፍ የሚታወቁት ፓም ቦንዲ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት እንደሚወጡም ተነግሯል።
ዶናልድ ትራምፕ ሹመቱን ከሰጡ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፓም ቦንዲ 20 ዓመታትን የሚጠጋ ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ፓም ወንጀልን በመከላከል እና የፍሎሪዳ ጎዳናዎችን ሰላማዊ በማድረግ ለሰሩት ስራ አድናቆት ይገባቸዋል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡