ምርጫ ቦርድ ለቀድሞዋ ሰብሳቢ መኖሪያ ቤት አጥር ጨምሮ ለአጃቢዎችና ለሾፌሮች ያወጣው ገንዘብ የኦዲት ትችት ቀረበበት
|የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀድሞ ሰብሳቢው መኖሪያ ቤት ዕድሳትና አደገኛ የሽቦ አጥር ለማሠራት ወጪ ያደረገው 233 ሺሕ ብር፣ ለአጃቢዎችና ለሾፌሮች ለምሣና ለእራት ያላግባብ የተከፈለ 218 ሺሕ ብር በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ግኝት ትችት ቀረበበት፡፡
ትችቱ የቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የ2015 በጀት ዓመት ሒሳብ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ ኅዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ውይይት ሲደረግ ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ካየ በኋላ ባቀረበው ጥያቄ በ2013 በጀት ዓመት 218,500 ብር ለአጃቢዎችና ለሾፌሮች ያለአግባብ የምሣና የእራት አበል ክፍያ መከፈሉ በዋና ኦዲተር ተረጋግጦ ገንዘቡ ተመላሽ እንዲሆን በኦዲተር አስተያየት ቢሰጥም፣ ቦርዱ ግን ምላሽ አለመስጠቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በ2013 ዓ.ም ለቦርዱ ሰብሳቢ መኖሪያ ቤት ዕድሳትና አደገኛ የሽቦ አጥር ለማሠራት በአጠቃላይ ከ233 ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ ለቦርዱ ከተፈቀደው በጀት ላይ ያላግባብ ወጪ መደረጉን፣ገንዘቡም ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲተካ አስተያየት ቢሰጥበትም ቦርዱ መልስ እንዳልሰጠበት በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ቀርቧል፡፡
የዋና ኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ተመሥርቶ የቀረበው የኮሚቴው ጥያቄ እንደሚያሳየው 981 ሺሕ ብር መነሻ የምዝገባ ሰነድ የሌለው የተከፋይ ሒሳብ ላይ የተመዘገበ ገንዘብ፣ 6.5 ሚሊዮን ብር በተገቢው የሒሳብ መደብ ሳይመዘገብ የተገኘ ገንዘብ፣ በ2014 ዓ.ም. 19 ሚሊዮን ብር ሥራ ላይ ያልዋለ ገንዘብ፣ 138 ሺሕ ብር ለሐረር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ያለ ውድድር በቀጥታ የተፈጸመ ግዥ ይገኝበታል፡፡
በተመሳሳይ 24.5 ሚሊዮን ብር በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተከፋይ ሒሳብ፣ ሁለት የቦርዱ ሠራተኞች ንብረት ሳያስረክቡ መልቀቃቸውና ቦርዱ የራሱ የሆነ የተሽከርካሪ ጋራዥ እያለው ተሽከርካሪዎቹ በውጭ ጋራዥ እንደሚጠገኑ ጥያቄ ተነስቷል፡፡
ምርጫ ቦርድ ሠራተኞችን ማስታወቂያ በማውጣት መቅጠር ሲገባው፣ በፕሮጀክት ተቀጥረው የነበሩ 55 ሠራተኞችን ያለ ውድድርና ማስረጃዎችን ሳያሟሉ ያላግባብ መቀጠራቸውን ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አንስቶበታል፡፡
በተጨማሪም ከሐምሌ 2011 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ከቦርዱ ዋና ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢዎች በመመርያው መሠረት ከደመወዛቸው ያልተቀነሰ የሕክምና ሁለት በመቶ ወጪ፣ በድምሩ 40,000 ብር የሚጠጋ ተቀናሽ ተደርጎ ወደ መንግሥት አለመግባቱ ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡
ቦርዱ በ2013 ዓ.ም. 2.7 ሚሊዮን ብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ መክፈሉን ቢገለጽምና ፓርቲዎቹ መቀበላቸውን የሚያሳይ የገንዘብ ገቢ ደረሰኝ እንዲያቀርብ ከኦዲተር ጥያቄ ቢቀርብም፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ደረሰኝ ማቅረብ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
ዜናው የሪፖርተር ነው