የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት አልምቶ ለማምጠቅ የሚያስችል የውል ስምምነት ከሻንጋይ የማይክሮ ሳተላይት ኢንጂነሪንግ ማዕከል ጋረ ተፈራረመ። ሳተላይቷ ስያሜዋ (Ethiopian Remote Sensing Satellite -2 (ETRSS-2) እንደሆእ ተመልክቷል።
የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ኢኒስቲትዩቱ የተለያዩ የሳተላይት መረጃዎችን በማደራጀትና በመተንተን ለሀገር ጥቅም እንዲውል እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እንደ ሀገር ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎችን ለማስፋት ከተለያዩ የምርምር ማዕከላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በዛሬውም እለት ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ጊዜ (Ethiopian Remote Sensing Satellite -2 (ETRSS-2) የሚል ስያሜ የተሰጣትን የመሬት ምልከታ ሳተላይት አልምቶ ለማምጠቅ የሚያስችል የውል ስምምነት ቻይና ከሚገኘው የሻንጋይ ማይክሮ ሳተላይት ኢንጂነሪንግ ማዕከል ጋር ተፈራርመናል ብለዋል። (ETRSS-2) ሳተላይት 0 ነጥብ 5 ሪዞሊሽን ያለው ሳተላይቷ ለአምስት ዓመት አገልግሎት እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
በስምምነቱ መሰረት የመሬት ምልከታ ሳተላይትን በአንድ ዓመት ከ6 ወር ጊዜ ውስጥ ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ ኤስዲጂ ሳት-1 ከተሰኘ ሳተላይት ኢትዮጵያ በነጻ መረጃ እንደምታገኝ ገልጸው፥ ይህም ሀገሪቱ የሳተላይት መረጃን የማግኘት የመተንተን አቅሟን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ተቋማት የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት።
በቀጣይ የሰብል፣ የደን፣ የውሀ፣ የከተማ እና የገጠር መሬት አጠቃቀምና ሽፋን ለውጥ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችሉ የመረጃ ማእከላት እንደሚደራጁ አብራርተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፎዚያ አሚን (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት በስፔስ ሳይንስ ሀገራዊ አቅምን ለማሳደግ ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት ጀምሮ በርካታ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ETRSS-2ን ሳተላይትን አልምቶ ለማምጠቅ የተፈጸመው ውል መሬት ላይ እንዲወርድ ሁለቱ ተቋማት በአግባቡ እንዲሰሩ አሳስበዋል። ሚኒስቴሩም ለስራው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሻንጋይ የማይክሮ ሳተላይት ኢንጂነሪንግ ማዕከል የሳይንሳዊ ምርምርና ኢንጂነሪንግ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ዣዎቸንግ ዡ በበኩላቸው፥ ማዕከሉ ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት አልምቶ ለማምጠቅ ስራውን በአግባቡ እንደሚያከናውን አረጋግጠዋል። የዛሬው ስምምነት በሁለቱ ተቋማት መካከል በዘርፉ ላይ በጋራ ለመስራትና ልምድ ለመለዋወጥ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።