ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ከሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ የተሾሙት “ሽንፍላ” በሚል ስያሜ የሚጠራውን ቤት እንዲያጸዱ ነበር። የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዴኤታ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩትና ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ሀላፊ የነበሩት ወይዘሮ ሰላማዊት ወደ ኃላፊነቱ ከመጡ በሁዋላ መሻሻል ቢታይበትም የተረከቡት ተቋም አሁንም አስገራሚ ግድፈት የሚፈጸመብት ሆኗል። ቅጣት እየሰበሰብ በግለሰብና በድር አካውንት የሚያከማችና እንዳሻው ሃብት የሚያመንዥግ ተቋም ሆኗል።
ተራ የማንነት ማስረጃ ደብተር ማግኘት ቅንጦት ሆኖ፣ በገንዘብ ሲቸበቸብ፣ ማንነታቸው ለማይታወቅ ዜግነት በጠራራ ጸሃይ እየታደለ የደላሎችና የተመሳተሩ ኃላፊዎች ሃብት የሚያጋብሱበት ይህ ጉድፉ ብዙ ተቋም አሁን ድረስ ከችግር አዙሪት እንዳልወጣ በርካታ መረጃዎች አሉ።
ሊጠራ ያልቻለው የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት መስሪያ ዋና ዳይሬክተር በግልጽ ባልተገለጸ ምክንያት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቅርበው ለቀረበባቸው የኦዲት ሪፖርት ምላሽ አለመስጠታቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ተቋሙ ገንዘብ ሚኒስቴር ሳይፈቅድ በራሱ አካውንት ከፍቶ 18 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ካከማቸው በሁዋላ ግማሹን በአበልና በትርፍ ሰዓት ክፍያ እምሽክ አድርጓል።
እንዲህ ያለውን ተቋም እንዲመሩ የተመደቡት ዋና ዳይሬክተሯ በሪፖርቱ ማድመጫ ቀን አለመገኘታቸው የፓርላማውን ቋሚ ኮምቴ እንዳስቆጣ በተገለጸበት ወቅት ሌሎች ኃላፊዎች ይቅርታ ከመጠየቃቸውና ዳግም እንዲህ ያለው ተግባር እንደማይፈጸም ቃል ከመግባታቸው ውጪ ዋና ዳይሬክተሯ በምን ምክንያት እንዳልተገኙ አላስታወቁም። ከአገር ውጭ መሆናቸው በደፈናው ተመልክቷል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው ይፋዊ የኦዲት ሪፖርት ውይይት ላይ የመገኘት ግዴታ አለባቸው። ፊት ለፊት ተገኝተው የሚመሩት ተቋም የፈጸመውን ጉድለት ማብራራትና ማስረዳት ከሃላፊነታቸው አንዱና ግንባር ቀደም በመሆኑ ሽሽታቸው ለበርካታ አስተያየት በር ከፍቷል። የሾማቸው አካልም ይህን ጉዳይ እንደሚያጤነው ይጠበቃል። ከአገር የወጡበት አሳማኝ ጉዳይ ካለም ዝርዝር እንኳን ባይቀርብ በደፈናው ሊገለጽ ይገባ እንደነበር የሚጠቁሙ፣ ይፋ በሆነው መረጃ መሰረት የዋና ዳይሬክተሯን ተግባር ” ተቀባይነት የሌለው፣ ሚዛን የማይደፋ” ሲሉ ተችተዋል።
ሌብነትን የአሰራር ግድፈት ሲንጠው፣ ደላላ በኔትወርክ ተደራጅቶ ሲያስተዳድረው የነበረና በዙሪያው ባሉ መንደሮች ቢሮ ተከፍቶለት የማንም መፈንጫ ሆኖ ህዝብን ሲዘርፍና ሲያዘርፍ የነበረን ሽንፍላ ተቋም እንዲያስተካክሉ የተመደቡት ናዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የ2015 እና 2016 በጀት ዓመት የፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና ውጤታማነትን በተመለከተ የክዋኔ የኦዲት ሪፖርት እና የ2015 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ለመወያየት በጠራው ስብሰባ ላይ የመገኘት ግዴታቸውን ባያከብሩም ውይይቱ ተካሂዷል።
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ ‘’ምክር ቤቱ ተመርምረው የቀረቡለትን የዋና ኦዲት ሪፖርት በይፋ ውይይት በሚያደርግበት ወቅት የመስሪያ ቤቱ የበላይ ሀላፊ የመኖር ግዴታ አለበት’’ ሲሉ ማሳሰባቸውን ስፍራው ላይ የነበሩ ሚዲያዎች ዘግበዋል።‘’የመጣችሁትን የስራ ሀላፊዎች ሀላፊነታችሁን አክብራቹሀል’’ በማለት ሰብሳቢዋ ዋና ዳይሬክተሯ አለመገኘታቸውን ወርፈዋል።
ሰብሳቢያዋ ሪፖርቱ ከመቀረቡ አስር ቀን በፊት አስቀድሞ የማሳወቅ አሰራር መኖሩን አመልክተዋል። አክለውም ከአስር ቀን በፊት ማሳወቅ የተመረጠበት ምክንያት ኃላፊዎች መገኘት የማይችሉ ከሆነ ተለውጭ ቀን ቀደም ብሎ ለማመቻቸት እንዲረዳ ታስቦ መሆኑን ጠቅሰው ዋና ዳይሬክተሯ ይህን አሰራር መጣሳቸውን ገልጸዋል። “ይሄ እኮ የመ/ቤቱ ቁልፍ ተግባር ነው” ሲሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ሃብት ይሰጣል። ይህ ሃብት በአግባቡ፣ በህግ እና በስርዓት አገልግሎት ላይመዋሉን ለማረጋገጥ መቆጣጠር ይፈልጋል። ቁጥጥር በሚያደርገበትና የኦዲት ሪፖርት በሚቀርበበት ወቅት ኃላፊነት የተሰሰጣቸው አካላት አለመገኘት ተገቢ እንዳልሆነ ደጋግመው ሰብሳቢዋ በመናገር ዋና ዳይሬክተሯን ወቅሰዋል።
“በርካታ ስራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ከበርካታ ስራዎች የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በኦዲት ምርመራ ሪፖርቱ ላይ መገኘት ነው” ካሉ በሁዋላ አክለው፣ ይህ የሚያመላክተው ለኦዲቱ የሰጣችሁትን ትኩረት ነው። ትኩረት ላለመስጠታችሁ አንዱ ማሳያ በአካል ተገኝቶ ይሄን ተምሬያለሁ፣ ፈጽሚያለሁ፣ ይሄን አልፈጸኩም ብሎ ፊት ለፊት መናገርና ማስረዳት ከአንድ ኃላፊ የሚጠበቅ ተግባር ሆኖ ሳለ አለማድረጋችሁ ነው” ብለዋል። ዳግም ይህ ተግባር እንዳይፈጸም አበክረው አሳበዋል።
18 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ከገንዘብ ሚኒስቴር ፈቃድ ውጭ
ከፓስፖርት ቅጣት የተሰበሰበው ወደ 18 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በግለሰብ አካዉንት ገቢ ሲደረግ እንደነበር በኦዲት ተረጋገጠ!
ኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት ቅጣት ክፍያን የመሰብሰብ ፍቃድ ሳይሰጠዉ የራሱን የመመሪያ ተመን በማዉጣት ሲሰራ እንደነበር ተገልጿል።ስልጣን ሳይሰጠዉ ከፓስፖርት የሚገኝ የቅጣት ገንዘብን እየሰበሰበ ይገኛል የተባለው አገልግሎቱ የገንዘብ ሚኒስትርን ሳያስፈቅድ የራሱን አካዉንት በመክፈት 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገደማ ገቢ አድርጓል ተብሏል።
በራሱ የተመን መመሪያ ቅጣት ሲጥል የነበረዉ ተቋሙ ከ 1 ሺህ እስከ 1500 ብር እያስከፍል እንደነበር ካፒታል ከኦዲት ሪፖርቱ መመለከቱን ገልጾ ዘግቧል። “ይህ ገንዘብ ገቢ ሲደረግ የነበረዉ በግለሰቦች አካዉንት ተከፍቶ ነበር” ያለዉ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የተከፈተው የባንክ አካዉንት ወደ ሰራተኞች መረዳጃ እድር መቀየሩን አመልክቷል።
በዚህ ባልተፈቀደ አካዉንት ገቢ ተደርጓል ከተባለው ገንዘብ ዉስጥ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆነው ለትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ለበዓል ወጪ መደረጉን እና 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ደግሞ በአካዉንቱ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።የፌዴራል ዋና ኦዲተር በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ በቅጣት የተገኘው ገቢ ወደ መንግስት መተላለፍ የነበረበት ያለ ሲሆን ይህ ባለመሆኑ ህጉ መጣሱና ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት ሊጠየቁ ይገባል ብሏል።
ይህ እስከተጻፈ ድረስ ዋና ዳይሬክተሯ ይቅርታም ሆነ ምላሽ አልሰጡም።