ከተለያዩ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ የቻይናዎችን ስም መስማት የተለመደ ነው። ትልልቅ ገቢ ተከራይተው በድብቅ እያመረቱ ከሚያከፋፈሉት ጀምሮ በፕሮጀክት ዕቃ ስም ከቀረጥ ነጻ በኮንቴነር ሸቀጥ እያስገቡ የሚዘርፉ እንዳሉ በመረጃ ሳይቀር የተያዙ፣ የተከሰሱ፣ የተፈረደባቸው አሉ። ማዕድን ዘርፍ ላይም እንዲሁ።
ሰሞኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር በመርካቶ ደረሰኝ በማይቆርጡ ነጋዴዎች ላይ የጀመረውን ክትትል ተከትሎ በተነሳው አለመግባባት ዙሪያ ከተለያዩ ነጋዴዎች ጋር ውይይት መደረጉ አይዘነጋም።ትንንሾቹ ነጋዴዎች አከፋፋዮችና አስመጪዎች ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል። እነሱ ደረሰኝ ስለማይቆርጡ የችግሩ ምንጭ ናቸውና ከላይ ያለውን አጽዱ ሲሉ ሞግተውም ነበር።
ለዚህ ይመውስላል በስተመጨረሻም የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት ከአስመጪዎች እና አከፋፋዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ በርካታ ጉዳዮች ከተለያዩ አካላት የተነሱ ሲሆን ቲክቫህ ለማህበራዊ ሚዲያ እንዲሆን አድርጎ ያስቀመጠእው ዘገባና የመንግስት መገናኛዎች እንዳሉት ተሳታፊዎቹ ግዴታቸው ባለመወጥታቸው ሳቢያ አስተዳደሩ ክንዱን በማንሳቱ ወደ ሌላ አካል እያመሩት ነው። |ቻይናዎቹን ፈርታችሁ ነው ወይ?” ያሉም አሉ።
በዱከም የሚገኘውን ቻይናዎች ያለሙትን ኢስት የኢንዱስትሪ መንደር ” ከዛ ቤት የሚወጣ እቃ ደረሰኝ አያውቅም ይሄንን ሳታውቁ ቀርታችሁ አይደለም” በማለይ የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል። አያይዘውም ” ቻይኖቹን ፈርታችሁ ይሁን ምን ይሁን እኛ አይገባንም ” – የሚል ሮሮ አሰምተዋል።
የቻይናዎች ህገወጥ ተግባር ላይ መሳተፍ የሚታወቅና፣ ባለስልጣናትን በጉቦ ማበስበስ የተካኑ መሆናቸው በግልጽ የሚነገርና ሃይ ባይ ያጣ ጉዳይ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ” ከቻይኖች (ከፋብሪካዎች) ጋር የተነሳው ጉዳይ ከፌዴራልም ጋር በነበረን መድረክ ተነስቷል ፤ ግብረኃይልም ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል ” የሚል ምላሽ በአ/አ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ በኩል ቀርቦበታል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ ተወያይ ” የ1 ሚሊዮን ብር እቃ ገዝታችሁ የ300 ሺህ ብር ደረሰኝ ነው የሚፅፉት (ይህ ምሳሌ ነው) ” -ሲሉ አከፋፋዮች ወይም አስመጪዎች ላይ አነጣጥረው አስተያየት ሰጥተዋል።
የገቢዎች ተወካይ በበኩላቸው ” ያለ ደረሰኝ ግብይት ፈጽማችሁ የምትገኙ ከሆነ በ100 ሺህ ብር ቅጣት ብቻ አናልፍም” የሚል ምላሽና ቁጥጥሩ መጠቋቆም ቢኖርም እንደማይቀር እንቅጩን ተናግረዋል። ይህን የጠነከረ የተባለ የመንግስት አቋም ተከትሎ ከነጋዴዎች በኩል አንዳንድ ቅሬታዎች ተንስቷል። “የአዲስ አበባ ነጋዴዎች አምጽ ጀምረዋል። ህዝብ ሊቀላቀልና መንግስትን ሊጥል ይችላል። ህዝብ ኃይል አለው። የሚበረታታ ጅምር ነው። መንግስት ተነቃንቋል” የሚል የዓመጽ ጥሪም በተለይ በዲያስፖራ ሚዲያዎች ሲስተጋባ ነበር።
ግብር ማስከፈልና በህጋዊ መንገድ ለሸጡት ዕቃ ደረሰኝ ማስጠት በየትኛውም ዓለም የተለመደና ማንም ጥያቄ የማያነሳበት አሰራር መሆኑ ይታወቃል። አተርገባበሩን እንጂ ግብር የመሰብሰብን ስራ መቃወም ትክክል እንዳልሆነ የሚስማሙ ያሉትን ያህል፣ ልክ እንደ ጥቁር ገበያው “እንዳሻን ገበያውን እንምራው” የሚሉ ክፍሎች ጉዳዩን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመሳብ መሞከራቸው፣ ከመንግስትም ወገን ሌቦች ማኖራቸው አግባብነት ያለውን ጉዳይ ውስብስብ አድርጎታል።
ለዚህም ይመስላል ትልልቆቹ ወደ ቻይናዎቹ፣ ትህህንሾቹ ወደ ትልልቆቹ ጣት መቀሰር የገቡት። ለምሳሌ በውይይቱ በተለይ ዝቅተኛ የሚባለው ነጋዴ ” ጉዳዩ ስር የሰደደ ነው ከላይ ጀምሮ መጥራት አለበት። መቼ ፋብሪካዎች፣ አስመጪዎች ፣ አምራቾች አከፋፋዮች ደረሰኝ ይሰጡናል ፤ ዝም ብለው አይደል የሚያወጡት? መጀመሪያ እነሱን መቆጣጠር አለባችሁ ” ሲሉ ተደምጠዋል። በሌላ አነጋገር “ከነሱ ጋር ግንኙነት አላችሁ” እያሏቸው ነው። ብንኙነቱ ደግሞ ባለስልጣኑ ይዘርፋሉ ማለት ነው። ጉቦ ይወስዳሉ። ወይም ኮሚሽን ይቀበላሉ ማለት ነው።
የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በተገኙበት ከአስመጪዎች እና አከፋፋዮች ጋር በተካሄደ ውይይት
ከተሳታፊዎች አንዱ ” እኛ ፎሬይን ዳይሬክት ኢንቨስትመንት አይተግበር እያልን አይደለም። ነገር ግን ዱከም ኢንዱስትሪ ዞንን ዞር ብላችሁ ያያችሁትም አይመስለኝም ፤ እኔ አሁን አሁንማ የሌላ ሀገር እየመሰለኝ መጥቷል። ከዛ ቤት የሚወጣ እቃ ደረሰኝ አያውቅም። ይሄንን ሳታውቁ ቀርታችሁ አይደለም። ቻይኖቹን ፈርታችሁ ይሁን ምን ይሁን እኛ አይገባንም ” ሲሉ የባለስልጣናትን ሌብነት የወለደው ዳተኛነት አፍርጠውታል።
” ግራ እየገባን ነው እኛ ሀገራችን ነው ብንሰርቅም። እዚሁ ነው የምንጥለው የሆነ ሰዓት መገኘታችን አይቀርም እነሱ ግን ሀገራቸው አይደለም ሰርቀው ይዘውት ነው የሚሄዱት ” ሲሉ ተናጋሪው ሌብነቱን በአገር ልጅና በውጪ ዜጋ ለይተው በየፈርጁ አስቀምጠዋል። ” ከተሰረቀ አይቀር እኛ ብንሰርቀው” ለማለት ነው። ይህ ንግግር ትዝብት የሚጥል ቢሆንም ሌብነቱን አጉልቶ ያሳያል።
ሌላ ተሳታፊው ” በኢስት ኢንዱስትሪ ዞን ያለው ነገር ግልጽ ነው ። ይሄ ለእናተ ተደጋግሞ መነሳትም ያለበት ነገር አይደለም። የ1 ሚሊዮን ብር እቃ ገዝተናቸው የ300 ሺህ ብር ደረሰኝ ነው የሚፅፉት (ይህ ምሳሌ ነው)” ሲሉ የቻይናዎቹን ድርጅቶች አጭበርባሪነት አመልክተዋል። አክለውም ” በአንድ ደረሰኝ ከ20 እና 30 በላይ መኪና ይመላለሳል ” ሲሉ የቅጥፈቱን መጠን አሳይተዋል። ጥያቄው ይህ ሁሉ ሲሆን ተቆጣታሪው አካል የት ነው? የሚለው ነው።
የውጭ ኢንቨስትመንትን እንደማይቃወሙ ጠቅሰው፣ ባለስልጣናቱ የማስተዳደር አቅም ደረጃ ቸውን በመጠራጠር ” የማትችሉትን ነገር ነው መሰለኝ” ሲሉ አስተያየት የሰጡም አሉ። እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የውጭ ኢንቨስመንት አካሄድን በአግባቡ መቆጣጠርና ማሳለጥ ካልተቻለ እንደ አገር ጉዳት ስለሚያስከትል የሚመለከተው አካል ሊሰራበት እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ የከተማው ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ቢንያም ምክሩ ሃሳባቸውን ሲሰጡ፣ ” የተነሳው ትክክል ነው እኛም እናውቀዋለን” ብለዋል። አክለውም “ከቻይኖች ጋር የተነሳው ጉዳይ ከፌዴራልም ጋር በነበረን መድረክ ተነስቷል። ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮችን የሚፈታ በክብርት ሚኒስትሯ የሚመራ የፌዴራል ገቢዎች ፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ኦሮሚያ ክልል መንግሥትን ያቀፈ አንድ የጋራ ቅንጅት የሚመራበት ማንዋል ፀድቆ ወደ ስራ ተገብቷል ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ይህ የኢስት ኢንዲስትሪ ዞንና ሌሎች ጋር የተገናኙ ወደ ከተማው የሚገባ ምርት በሸገር ከተማ ዙሪያ የሚመረቱ ነገር ግን ያለደረሰኝ ከፋብሪካ የሚወጡትን እዛ ያለው አዲስ የተቋቋመው ግብረኃይል ይከታተለዋል ” ብለዋል።
በሌላ በኩል ፤ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊው በመርካቶም ሆነ በሌላ የከተማው አካባቢ የሚካሄደው የደረሰኝ ቁጥጥሩ ወቅታዊ ሳይሆን በዘላቂነት የሚሰራበት እንደሆነ አመልክተዋል። ከአሰራር ጋር በተያያዘ ያሉት ችግሮች እንደሚፈቱ ቃል ገብተው ለአስመጪና አስከፋፋዮች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ኃላፊው ፤ ” ከዚህ በኃላ በግልጽ ልንነግራችሁ የምንፈልገው አስመጪ እና አከፋፋይ የሆናችሁ ያለ ደረሰኝ ግብይት ፈጽማችሁ የምትገኙ ከሆነ በ100 ሺህ ብር ቅጣት ብቻ አይደለም የምናልፈው ” ሲሉ ቅጣቱ ከዚያም እንደሚልቅ አስታውቀዋል።
” በቀጥታ የኦዲት ምርመራ (Investigation Audit) ውስጥ ነው የምንገባው ይህ ደግሞ በጣን ክፉኛ ይጎዳችኋል ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። መክረዋል።
” መርካቶ ውስጥ ያለ ድረሰኝ ግብይት ሙሉ ለሙሉ መቆም አለበት ” ያሉት ኃላፊው፣ ከጊዜ ጋር በተያያዘ ለሚነሳው ጥያቄ ” ለዝግጅት የሚሰጥ ጊዜ የለም ቁጥጥራችን ይጠናከራል ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ደህነነት በዘመናዊ የክትትልና የመረጃ አሰባሰብ በግብርና ደረሰኝ ረገድ ችግር ያለባቸውን መረጃቸውን ሰብስቦ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ስለ ጉድዩ የሚያውቁ ገልጸውልናል። በዚህም መሰረት ሃብትን እስከ መክሰር የሚያደርስ ክስ ሊመሰረትባቸው የሚችሉ እንዳሉ ተሰምቷል። አሁን ላይ የዲጂታል መረጃ አሰባሰቡና መረጃውን በአንድ ቋት ከቶ ማስተዳደር መጀመሩ ምርመራውን እንዳቀለለውም ነግረውናል።
አንድ አስመጪ ወይም አምራች ካለው መረጃ የበለተ ዳታና በመንግስት እጅ እንዳለ ያመለከቱ ወገኖች፣ ዳታውን መርምሮ ወንጀለኛውን መያዝና ህግ ፊት ማቅረብ ቀላል እንደሆነም ጠቁመዋል። ሲስተሙ ግብር ሰብሳቢዎችንም ወይም አጋብብ ያላቸውን ኃላፊዎች ወደ ሁውላ ሄዶ “ይህ ሁሉ ሲሆን ለምን ዝም አልክ?” የሚል ጥያቄ ሊያስነሳባቸው የሚችል ነው።