የቀድሞ የትህነግ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ወደ ተሀድሶ ስልጠና ማዕከላት የማስገባት ስራ በይፋ መጀመሩ ታወቀ። መንግስት የውጭ መንግስታት ከሚሰጡት ድጋፍ በተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ዶላር መመደቡ ታውቋል።
ወደ ተሀድሶ ስልጠና ማዕከላት የሚገቡ የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል። በዚሁ መሰረትም የመጀመሪያ ዙር የመቀሌ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከል የሚገቡ የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የነፍስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በማስረከብ ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፖች ሲገቡ የሚያሳዩ የቪዲዮና የምስል ዜናዎች ታይተዋል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የቀድሞ ታጣቂዎች ከአንድ ዓመት በፊት የከባድና መካከለኛ የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ታዛቢዎች በተገኙበት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ማስረከባቸው ይታወሳል።
በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይም የብሔራዊ ተሃድሶ ምክትል ኮሚሽነርና የመከላከያ ሰራዊት ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ፣ የመከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ መኮንኖች፣ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነሮች፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ተባባሪ አካላት ተገኝተዋል።
የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች በየስልጠና ማዕከላቱ የሚኖራቸውን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ ከማሕበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን የሚመሩበት የገንዘብና የቁሳቁስ መቋቋሚያ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፤ በትግራይ ክልል መቀሌ፣ እዳጋ ሀሙስ እና ዓድዋ በተዘጋጁ ሶስት ማዕከላት በሚቀጥሉት አራት ወራት 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በዘላቂነት የማቋቋምና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ እንደሚከናወን አስቀድሞ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ታጣቂዎቹን ወደ ካምፕ የማስገባቱ ስራ ሲጀመር ” ትጥቅ መፍታት መሸነፍ ፣ መዋረድ ወይም ራስን ዝቅ ማድረግ ማለት አይደለም። ትጥቅ መፍታት ማለት የሀገር አንድነትና ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ ከማቆም አንፃር መታየት አለበት ” ሲሉ የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ተናግረዋል።
ዛሬ በተካሄደ ይፋዊ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው ፤ ” የዴሞብላይዜሽን አሰራር ሴት ተዋጊዎችን ፣ አካል ጉዳተኞችን እና በአደረጃጀት ውስጥ ያሉ አመራሮችን በማስቀደም ይፈፀማል ” ሲሉ ተደምጠዋል። ትጥቅ በማስፈታቱ ሂደት በየቀኑ 320 ታጣቂዎች ወደ ስልጠና ማዕከላት የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። በዚሁ ሂደት በመጀመሪያ ዙር 75 ሺህ ታጣቂዎች እንደሚስተናገዱ አክለዋል። የመቀበያ ካምፖቹ መቀለ፣ አደዋና ደግሃ ሃሙስ እንደሆኑም ታውቋል።
” ማንኛውም ትጥቅ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ውጭ መያዝ የሀገሪቱ ህገ-መንግስት ይከለክላል ስለሆነም በትግራይ እየተፈፀመ ያለው ትጥቅ የማስፈታቱ አፈፃፀም ህግና ስርዓት ተከትሎ የሚፈፀም ነው ” እንደሆነና ጉዳዩ ህግንም የማስከበር እንደሆነ አመልክተዋል።
በመሆኑም ” ትጥቅ ማስረከብ ማለት ያለችን እንዲት ሀገር ከሚጋረጡባት የውጭ ስጋቶች መታደግ መሆኑን መገንዘብ ያሻል ” ያሉት ጀነራሉ ” ትጥቅ የማስፈታት ተግባሩ የትግራይ እና በክልሉ ድንበር አከባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተፈፃሚ ይሆናል ” ሲሉ አሳውቀዋል።
የትግራይ የፀጥታ እና የሰላም ቢሮ ሃላፊ ጀነራል ፍስሃ በበኩላቸው ፤ ” ትጥቅ የመፍታቱ ተግባር እርምጃ ለትግራይና ለሀገር ሰላም የተከፈለ ውድ እና ሁሌ በታሪክ ድምቆ የሚታወስ ፍፃሜ ነው ” ማለታቸውን ከቲክቫህ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት እንዲቀላጠፍ አሜሪካ ሰሞኑንን ከመንግስት ጋር መምከሯን ኤምባሲው ማስታወቁ አይዘነጋም። የአውሮፓ ህብረትን ጨመሮ የተላያዩ አገራት ድጋፍ ማድረጋቸውም በተደጋጋሚ ሲዘገብ መቆየቱ አይዘነጋም።
የትህነግ ኃይል አካማችቶ መንግስትን በጡንቻ መፈተኑና ሌሎችን በማደራጀትና በማስታጠቅ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ መጣሉና በየክልሉ ላሉ ነፍጥ አንጋቢዎች የመጥፎ ተግባር ምሳሌ መሆኑንን የሚጠቅሱ ” ፍትህ ሊሰፍን ይገባል” የሚለው ድምጻቸው አሁን ድረስ እየተሰማ ነው።
በዚያ ደረጃ ውድመት እንዲደርስ፣ የሰው ልጆች እንዲያልቁ ያደረጉና ሰብአዊ ጉዳት ያደረሱ የትህነግም ሆነ የማንኛውም አካል መሪዎች እስካልተጠየቁ ድረስ ነገም ህዝብ እያስፈጁ በድርድር ሰላማዊ ህይወት መቀጠል ሊቀለበስ የማይችል ልማድ ሆኖ ሊቀር እንደሚችል እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
በሚሊዮን ዚኡእጎችን የነጠቀው ጦርነት መነሻው ጥንሡ፣ መሪዎቹ፣ አስተባበሪዎቹ፣ ነዳጅና ጋዝ በማርከፍከፍ ያጋጋሉ፣ የሰው ልጆችን መብት በከፋ ደረጃ የጨፍለቁ፣ ነጹሃንን ቤታቸው ድረስ በመሄድ የጨፈጨፉ፣ የደፈሩ፣ ወዘተ ተጣርቶ ህጋዊ ዳኝነት እንዲያገኙ መደረግ እንዳለበት የበርካቶች ዕምነት ነው።