ባህር ዳር ከተማ ዙሪያ የሚገኘው ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ባለሞያዎችና ሠራተኞች በአካባቢው ይገኛሉ ባሏቸው ታጣቂ ዘራፊዎች ይደርስብናል ባሉት ዘረፋና ምክኒያት ሥራ ማቆማቸውን ገለጹ።
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸውና ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሁለት የሕክምና ባለሞያዎች፣ በተለያዩ ጊዜያት የታጠቁ ዘራፊዎች ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ዘልቀው በመግባት ሠራተኞቹን በሽጉጥ በማስፈራራት ዘረፋ ማካሄዳቸውን ገልጸው ከሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ሥራቸውን እንዳቆሙ ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስና ድምጻቸውን እንድንቀይር የጠየቁን አንድ የሆስፒታሉ የጤና ባለሞያ፣ ከአምስት ወራት ወዲህ በተደጋጋሚ የታጠቁ ድንገተኛ ዘራፊዎች ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ በመግባት ዝርፊያ እንደሚፈፅሙ ገልጸዋል።
ማክሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የሆስፒታሉን ዳይሬክተር ጨምሮ ሌሎች አምስት ሐኪሞች ግቢው ውስጥ እንደተዘረፉም ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለሚመለከተው አካል ጠንካራ የጸጥታ ኃይል እንዲመደብላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መልስ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ለተሻለ ሕክምና ከምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቸና ወረዳ ታካሚ በበኩላቸው የሕክምና ባለሞያዎቹ አድማ ላይ በመኾናቸው ምክኒያት ፣ ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዛሬ አገልግሎት ባለማግኘት እየተጉላሉ መኾኑን በተመሳሳይ የደኅንነት ስጋት ምክኒያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ታካሚ ተናግረዋል።
የጥበበ ጊዮን አጠቃላይ ሆስፒታል በቀን ወደ 3 ሺሕ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድ የሆስፒታሉ አመራሮች ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ በዩንቨርስቲው በሕክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የሚማሩ ተማሪዎችም የተግባር ትምሕርት ይወስዱበታል።
በዩንቨርስቲው በሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ መኾኑን የገለጸልንና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስሙ እንዳይጠቀስ ድምጹም እንዲቀየር የጠየቅ አንድ ተማሪ ከሰኞ ጀምሮ የሕክምና ተማሪዎች የተግባር ትምህርት እየወሰዱ እንዳልሆነ ተናግሯል።
“ሆስፒታሉ አጥር የለውም። ጠባቂዎቹም ዱላ ይዘው ነው የሚጠብቁት ሲል ቅሬታውን ያቀረበ አንድ በተመሳሳይ ምክንያት ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የሕክምና ባለሞያ መደበኛ የፀጥታ ኃይል ካልተመደበ በቀር ሥራ መሥራት አስቸጋሪ እንደኾነ ጠቁሟል።
በባህር ዳር ዩንቨርስቲ በጥበቃ ሥራ የተሰማራና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስሙ እንዳይጠቀስ ድምጹም አየር ላይ እንዳይውል የገለጸልን ግለሰብ፣ የጠበቃ ሥራ የሚሠሩት ያለጦር መሳሪያ በመኾኑ ችግሮች ሲፈጠሩ ምላሽ መስጠት አለመቻላቸውን ገልጿል።
በባህር ዳር ዩንቨርስቲ የጸጥታና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ፣ ኢንስፔክተር ሀብታሙ መለሰ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በምሽት በታጠቁ ኃይሎች ዘረፋ እንደሚፈፀምባቸው አረጋግጠዋል። አክለውም፣ በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ከታወጀው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጋራ በተያያዘ ከጸጥታ ኃይሉ ውጭ የጦር መሳሪያ መያዝ የሚከለክል ዐዋጅ በመታወጁ የዩንቨርስቲው ጠባቂዎች የጦር መሳሪያ እንደማይዙ ገልጸዋል። በዚኽም ምክኒያት ወደ ግቢው ታጥቆ የሚመጣውን ማንኛውንም ዘራፊ ለመከላከል አዳጋች እንደሚኾንባቸው ተናግረዋል። ችግሩ ለመፍታትም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋራ እየተነጋገሩ መኾኑን አስረድተዋል።
ሆስፒታሉን በበላይነት የሚያስተዳድረው ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሆስፒታሉ ውስጥ ዝርፊያ መከሰቱን አምነው ፣ዛሬ ጸጥታና ደህንነቱን ከሚመራው ተቋምና ከኮሌጅ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋራ ተወያይተው ችግሮችን ለመፍታት ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል።
የጥበበ ጊዮን አጠቃላይ ሆስፒታል በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ : በቀድሞው የሱማሊያው ፕሬዝዳንት መሀመድ አብድላሂ መሀመድ ” ፋርማጆ “በ2010 ዓ.ም የተመረቀ ትልቅ ሆስፒታል ነው
በጀት ጭመራ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በመንግሥት የቀረበውን ተጨማሪ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ፣ ከዓለም የገንዘብ ተቋማትና ከሌሎችም ምንጮች ከሚገኘው ገንዘብ ውስጥ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ እንደሚቀርብ የገንዘብ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል፡፡
መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተከትሎ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ተጨማሪ በጀት በመመደብ የሚወስዳቸው ርምጃዎች የሚኖራቸውን ተፅዕኖ በአሉታዊና አዎንታዊነት የሚመለከቱ ባለሞያዎች አሉ።
የአሁኑ ተጨማሪ በጀት ስለሚኖረው ተፅዕኖ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሞያው ዶ/ር ቴዎድሮስ መኮንን፣ አዲሱ የበጀት ጭማሪ የውጭ ገቢዎች ላይ የተመሰረተ በመኾኑ በዋጋ ንረት ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንደማይኖረው ያብራራሉ፡፡
ሀገር አቀፍ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት”የጥራት መንደር” ዛሬ ይመረቃል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የተጀመረው ሀገር አቀፍ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት፣ “የጥራት መንደር” ዛሬ እንደሚመረቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጥራት መንደር ቁልፍ ተቋማትን ያቀፈ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣የኢትዮጵያ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት ፣የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ከተቋሟቱ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክቷል።
ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት (NQI) የሀገሪቱን ደረጃዎች ልማት፣ የሥነ ልክ፣ የዕውቅና አሰጣጥ፣ የተስማሚነት ግምገማ፣ የገበያ ክትትል እና የጥራት ማስተዋወቅን በማጠናከር፣ ለንግድ ድርጅቶች የሚሰጠውን የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ለማሳደግ ያለመ ነው።
በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደገፈው እና የተሻሻለ አቅም ያለው ‘የጥራት መንደር’፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር በተሻለ ሁኔታ እንድትሳለጥ፣ የቴክኒክ መሰናክሎችን እንድትቀንስ እና በዓለም አቀፍ ንግድ ያላትን ተሳትፎ እንድታሻሽል አጋዥ እንደሚሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።
አደዋ
በዓድዋ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የእምነበረድ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ሊጀምር ነው
በዓድዋ ከተማ በ480 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የእምነበረድ ፋብሪካ በታህሳስ ወር የሙከራ ምርት እንደሚጀምር ተጠቆመ።
በዓድዋ ኢንዱስትሪ ዞን የሚገኘው ፋብሪካ በ2 ሺህ 421 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው።
የእምነበረድ ፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋይ ገብረ ህይወት፥ የፋብሪካው ግንባታ ሂደት 75 በመቶ መድረሱንና በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ላይ የሙከራ ምርት ማምረት ይጀምራል ብለዋል።
ግንባታው በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተከናወነ ሲሆን ለ120 ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ፋብሪካው ከክልሉ ጭላ ወረዳ ለምርት ግብዓት የሚያውለውን ጥሬ ዕቃ እንደሚያገኝ ገልጸው፥ በቅርብ ቀን የግራናይት እምነበረድ ማምረት ይጀምራል ነው ያሉት።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በየቀኑ በአንድ ሺፍት 1 ሺህ 200 ሜትር ኩብ እምነበረድ ያመርታል ነው ያሉት።
ጥብቅ ማሳሰቢያ – አደገኛ መድሃኒት “RELIEF”
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሕብረተሰቡ “RELIEF” የተሰኘ ሕገወጥ መድኃኒትን ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳሰበ።
ባለሥልጣኑ ሕገወጥ መድኃኒቱ(በውስጡ ዲክሎፌናክ፣ ፓራሲታሞል፣ ክሎረፊኒራሚን እና ማግኒዥየም ትራይሲሊኬት እንዳለው ይገመታል) በኢትዮጵያ ገበያ እየተዘዋወረ መሆኑን ባደረገው ክትትል እንደደረሰበት ገልጿል።
መድኃኒቱ በሕጋዊ መንገድ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያልተመዘገበ በመሆኑ ጥራቱ፣ ደህንነቱና ውጤታማነቱ እንደማይታወቅ አመልክቷል።
በተጨማሪም፣ የዚህ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድካም፤ የእይታ መዛባት፤ መፍዘዝ፣ ራስ ምታት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የጉበት ኢንዛይሞች መጨመርና ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል የኩላሊት ጉዳትን እንደሚያስከትል አስታውቋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህንን መድኃኒት ለረጅም ጊዜ መጠቀም ከባድ የጉበት፣ የኩላሊት ጉዳት፣ የልብ ድካም እና ስትሮክ የመያዝ እድልን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ባለስልጣኑ አስጠንቅቋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን መድኃኒት ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳስቧል።
ሕብረተሰቡ መድኃኒቱን በሚኖርበት አካባቢ ካገኘ በነጻ ስልክ ቁጥር 8482 ለኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ባለስልጣን ወይም ለክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካላት እንዲጠቁም ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።
መርካቶ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ሱቅ የተቃጠለባቸው ነጋዴዎችን በጊዜያዊነት መልሶ ለማቋቋም የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ድጋፉን ሲያስረክቡ ባደረጉት ንግግር ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መልሶ እስኪገነባ ሱቅ ለተቃጠለባቸው ነጋዴዎች የመስሪያ ቦታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ከተደረገው የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ በተጨማሪ የአይነትና የቴክኒክ ድጋፎችን እናደርጋለን ብለዋል::
በአካባቢው ያለውን ጥግግትና መጨናነቅ በዘላቂነት በመቅረፍ፣ የተሽከርካሪ መንገድን በማካተት፣ ለአደጋ ተጋላጭ በማያደርጋቸው መልኩ በዘላቂነት በአክሲዮን ተደራጅተው ደረጃውን የጠበቀ የገበያ ማዕከል መገንባት እንዲችሉ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ድጋፉን የተቀበሉት የአካባቢው ነጋዴ ተወካዮች በበኩላቸው አስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ እና ክትትል አመስግነው ድጋፉ በፍጥነት ወደ ስራ እንድንገባ ያስችለናል ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ህዳር 12 ቀን 2017 ዓም ኢፕድ