የአማራ ክልል ሰላም ከድፈረሰበት ከዓመት ወዲህ በርካታ ነዋሪዎቿ ወደ አዲስ አበባ ፍለሰዋል። አቅም ያላቸው ቤተሰቦቻቸውን ይዘው አዲስ አበባ ህይወትን አንድ ብለው መጀመራቸው ብቻ ሳይሆን ይህ እግት፣ ግድያ፣ ዘረፋና እያስፈራሩ ሃብት መውሰድ ወንጀለኞቹን ለይቶ ማውገዙ ላይ እንደየ ፖለቲካ ዝንባሌና ፕሮፓጋንዳው መደበላለቅ ቢኖርም ህዝብ ተማሯል። ተሰላችቷል። ተንገፍግፏል።
ከባንኮችና ንብረት ዝርፊያ በላይ ግድያና እገታ፣ እንዲሁም ስልክ እየተደወለ “ብር አስገቡ” የሚለው ትዕዛዝ ያስመረራቸው ” አጋታሚው ንግድ የሆነላቸው ይመስላል” ሲሉ እከሌ ከከሌ ሳይሉ ምሪታቸውን ይገልጻሉ።
ከግት በሁዋላ ገንዘብ በባንክ የሚላክበት አግባብ መኖሩን፣ ከባንክም በኩል ገንዘብ ያላቸውን እየጠቆሙ ለአጋቾች እንደሚሰጡ አንዳንድ ወገኖች በምሬት ቢናገሩም ነገሩን አድምቶ የሚሰራ ሚዲያም ሆነ ገልለተኛ አካል አልተገኘም። ይልቁኑም የፖለቲካውን ልዩነትና ግጭቱን ለማስፋት ያመች ዘንድ በደቦ የሚረጨው ፕሮፓጋንዳ ለዝርፊያው ልዩ ክብር አጎናጽፎ ህዝብ በየቀኑ ለቅሶ እንዲቀመጥ፣ እንዲበረግግና ማህበራዊ እረፍት እንዲያጣ አድርጓል።
ነገሩ ሁሉ ሰርግና ምላሽ የሆነላቸው ግጭትን ለፖለቲካ ድል ሳይሆን የአጋጣሚ መጠቀሚያ በማድረግ ፈር ወደለቀቀና ” ትግል እንዲህ ነው ወይ” በሚያስብል ደረጃ ለመስማት የሚከብድ ዜናዎችን ከአማራ ክልል መስማት እጅግ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የባህር ዳር ፖሊስ ኃላፊ አንድ መቶ ሃያ አንድ ተተርታሪዎች መያዛቸውን ሲያስታውቁ የገለጹት ዋና ጉዳይ በዕገታ ወንጀል ተተርጥረው የተያዙት ገንዘብ በባንክ ሲያዘዋውሩና ገንዘብ በስልክ ሲቀባበሉ የሚያረጋግጥ መረጃ መያዙንና ክትትሉ ለአንድ ወር የተደርገ መሆኑን አመልክተዋል። ዝርዝሩን ከቢቢሲ ዘገባ ያንብቡ።
- በእገታ እና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ 121 ሰዎችን መያዙን የባሕር ዳር ፖሊስ አስታወቀ / ቢቢሲ
እገታን እና ዘረፋን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 121 ግለሰቦችን በቀጥጥር ሥር ማዋሉን የአማራ ክልል ዋና ከተማ የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሊጠናቀቅ በተቃረበው ጥቅምት ወር ብቻ መሆኑን የከተማው ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮማንደሩ አክለውም በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ከተያዙት ግለሰቦች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት በእገታ ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው ብለዋል።
በግጭት እየታመሰ ባለው አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ በተደጋጋሚ የሚከሰት አሳሳቢ ወንጀል መሆኑን የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ የተራድዖ ድርጅቶች በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።
ኮማንደር ዋለልኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች በእገታ፣ በባንክ ዘረፋ እና በተለያዩ የስርቆት ወንጀሎች ተጠርጥረው በፖሊስ ሲፈለጉ የነበሩ ናቸው።
“የተያዙት 121 ናቸው። በእገታ ብቻ ሳይሆን በባንክ ዝርፊያ እና በልዩ ልዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው። ከ20 በላይ የሚሆኑት በእገታ ተጠርጥረው የተያዙ ናቸው” ይላሉ።
የባሕር ዳር ፖሊስ ኃላፊ እንደሚሉት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ‘ኦፕሬሽን’ የተጀመረው በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ነው።
የከተማዋ ፖሊስ ካደራጀው ምርመራ እና ከሕዝብ ጥቆማ ተነስቶ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም ኃላፊው ይናገራሉ።
“ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው ማስረጃዎች ተጠቅመን ነው በቁጥጥር ሥር ያዋልናቸው።”
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የተወሰኑቱ ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ ሲያደርጉ አሊያም ገቢ እና ወጪ ለማድረግ የተጠቀሙት የስልክ ቁጥር ምርመራ ተደርጎበት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ያስረዳሉ።
ኮማንደር ዋለልኝ እንደሚሉት ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመዋቸዋል የተባሉት እገታዎች ሁለት መልክ ያላቸው ናቸው።
“አንደኛው ለኢኮኖሚ ጥቅም ሲባል የተፈፀመ ነው። ሀብት እና ንብረት ያላቸው ሰዎችን ጠብቀው ግለሰቦቹን አሊያም ልጆቻቸውን ያግታሉ። ሁለተኛ ደግሞ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ሲሆን፣ አመራር ላይ ያሉ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን እያገቱ ተፅዕኖ ለማሳደር ነው የሚጠቀሙበት።”
ኃላፊው ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ከማዋሉ በተጨማሪ እገታ ላይ የነበሩ የተወሰኑ ግለሰቦች ማስለቀቁንም ገልፀዋል።
አክለውም በፖሊስ እርምጃ ምክንያት በከተማዋ የሚከናወኑ እገታዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
“በዚህ ሳምንት ለምሳሌ ልደታ በሚባል አካባቢ አንድ ታግቶ የነበረ ሰው ተለቋል። አሁን አሁን እገታ እየቀነሰ ነው። በእገታው እና ዘረፋው ምክንያት ተማረው ወደ መሐል ሀገር የሄዱ ሰዎችም ነበሩ። ይሄን መነሻ በማድረግ ነው ወንጀሉን ለማስቆም የተነሳነው” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አንዲት የቤት ሠራተኛ የአሠሪዎቿን ጨቅላ ሰርቃ ልትጠፋ ስትሞክር በቁጥጥር ሥር እንደዋለችም ኃላፊው አስታውሰዋል።
ሠራተኛዋ ወላጆች ወደ ሥራ ሲሄዱ የ13 ወር ሕፃን ይዛ ከተሰወረች በኋላ ፖሊስ በቀረበለት አቤቱታ መሠረት ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዋ ወደ ጎንደር ልትወጣ ስትሞክር በክልሉ የአድማ ብተና ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር መዋሏን አመልክተዋል።
ኮማንደር ዋለልኝ እንደሚሉት ወንጀሉን የፈፀመችው ግለሰብ በ13 ዓመት እስራት ተቀጥታለች።
በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በሚደረግ ግጭት ምክንያት ሰላም ባጣው የአማራ ክልል እገታ እና ግድያ በተደጋጋሚ የሚሰማ ዜና ሆኖ ቆይቷል።
ባለፈው ነሐሴ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ ውስጥ ለገንዘብ የታገቱ አንድ የረድዔት ድርጅት ሠራተኛ መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ማስታወቁ አይዘነጋም።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት እና የተራድዖ ድርጅቶች የፀጥታ አካላት ሰላማዊ ዜጎችን በቁጥጥር ሥር እያዋሉ ነው የሚል ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ነገር ግን በዚህ ወር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች “ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያላቸው አይደሉም” ይላሉ የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ ኃላፊ።
“ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በፖለቲካ አቋማቸው፣ በሃይማኖታቸው ወይም በቋንቋቸው ሳይሆን ወንጀል መፈፀማቸው ስለተጣራባቸው [እና እየተጣራ ያለ] ነው። ምንም ፖለቲካዊ ይዘት የለውም። ዋናው ዓላማችን ሕግን ማስከበር ነው።”
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል አራቱ በስርቆት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እያንዳንዳቸው የ2 ዓመት እስራት እንደተፈረደባቸው የሚናገሩት ኃላፊው በሌሎቹ ላይ ደግሞ መዝገብ እየተደራጀ እንደሆነ ጠቁመዋል።