በጦርነት ክፉኛ የተጎዳችውን ትግራይን እንዲመሩ የተመደቡት አቶ ጌታቸው ረዳ በጦርነቱ 800 ሺህ የሚልቁ የሰው ልጆች መሞታቸውን በገሃድ ተናገሩ። በዚህ ደረጃ ትውልድን የበላውን ጦርነት ሲመራ የነበረው ትህነግ አመራሮቹ ከዚህ ይህ ሁሉ ሆኖ ዳግም ለስልጣን መሻኮታቸው አስገራሚ እንደሆነባቸው ቀደም ሲል ጀምሮ ሲገለጽ መሰነበቱ አይዘነጋም።
ኩማ በጣልያን ቱሪን እየተካሄደ ባለው የጤና ጉባኤ ላይ CUAMM: an NGO working for the promotion and protection of health in Africa እየተሳተፉ ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ Avveniee ከተባለ ድረ ገጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ነው በጦርነቱ የተጠቀሰው ቁጥር ያላቸው ወገኖች መሞታቸውን ያስታወቁት። ከወር በፊት ዶክተር ደብረጽዮን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሞተዋል መባሉ ወሬና ማስረጃ የማይቀርብበት እንደሆነ ተናግረው ነበር።
ጣሊያን የቆሰሉት የትግራይ ተዋጊዎች እንዲያገግሙ ከሚረዱት ጥቂት አገሮች አንዷ መሆኗን ያወሱት አቶ ጌታቸው፣ አሁን ላይ አስተዳደሩን ዳግም በሚገባ ለማዋቀር፣ በፍትህና በሰላም መካከል ያለውን አስቸጋሪ ሚዛን ለመጠበቅ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አመልከተዋል። አያይዘውም ስለ ፕሪቶሪያው ስምምነት ለተጠየቁት ምላሽ ሰጥተዋል።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት ከሁለት ዓመት በኋላ በጥንካሬና በደካማ ጎን የተስተዋሉትን ክንውኖች ሲገልጹ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ለአራት ዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ለ 800 ሺህ ሰዎች ሞት እና ቁሳዊ ውድመት ምክንያት መሆኑን አስቀድመው ገልጸዋል።
በጦርነቱ ወቅት የውጊያ ውሎ ቃል አቀባይና የመረጃ ኮሞሬድ የደበሩት የ 49 ዓመቱ የትግራይ ክልል መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ጣሊያን, በቱሪን ውስጥ በሊንጎቶ፣ ከአፍሪካ ጋር በ Cuamm ዶክተሮች ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ መገኘታቸውን ጠቅሶ የዘገበው ድረገጹ፣ ጦርነቱን ለማስቆም ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ለመደራደር በመረጡት አግባብ ምክንያት በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ናቸው ሲል አወድሷቸዋል። አቶ ጌታቸው ከሃያ አራት ወራት በፊት በጦርነት የወደመውን ክልል መልሶ ለመገንባት እየሞከረ ያለው የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንደሆኑም አመልክቷል።
በትግራይ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ ዛሬ ተሻሽሏል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ መሻሻል ታይቷል” በሚል የመለሱት አቶ ጌታቸው፣ ነገር ግን አሁንም በርካታ አካባቢዎች በኤርትራ ኃይሎች መያዙን፣ ቀደም ሲል ምዕራብ ትግራይ በሚባለውና የአማራ ክልል “ወሰኔ ነው” በሚል ለረሽም ዓመታት አቤቱታ ሲያቀርበበት በነበረበት አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች እንዳልተመለሱ ገልሰዋል።፡
ከመፈናቀል በተጨማሪ የጤና፣ የትምህርት እና የምግብ ዋስትና ችግሮች እንዳሉ አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል። የእርስ በርስ ጦርነቱ በግብርና እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ቀደም ሲልም በሰብአዊ ርዳታ ላይ የተመሰረተውን አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ለከፋ ችግር እንደዳረገ ገልጸዋል።
በጦርነቱ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የህዝብ መገልገያ ተቋማት ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል። መልሶ ለመገንባት እና የተለመደውን አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ብዙ ስራ እንደሚቀር በመጥቀስ ድጋፍ እንደሚሹ ጠይቀዋል።
አሁን ላይ ውጊያ እንደሌለ እና የፕሪቶሪያ ስምምነት የጠመንጃዎቹ ድምጽ ጸጥ እንዲል ማድረጉን አመልክተዋል። ጦርነቱ እንዲቀጥል ከተደረጉት በርካታ ግፊቶች አንጻር የሰላም ስምምነቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አመልክቷል።
“የኤርትራ ወታደሮች አሁንም የትግራይን ክፍል በተለይም እንደ ኢሮብና የኢሮብ አዋሳኝ አካባቢዎችን መያዙን ቀጥሏል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ኃላፊነት ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት የውጭ ሃይላት ወይም ወታደሮችን ከትግራይ ክልል መልቀቅ እንዳለባቸው ያዛል ብለዋል። አክለውም “ከኤርትራውያን ጋር ሰላም መፍጠር እንፈልጋለን፣ስለ ጦርነት ማውራት የለብንም።” ብለዋል።
በተለያዩ አካላትና ተቋማት ይፋ እንደሆነው፣ ማንም ንጹህ ልብ ያለው እንደሚፈርደው ትህነግ የትግራይ ህዝብን ከጎረቤቶቹ ሁሉ አቃቅሮ፣ በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጎ ውጊያ ውስጥ ከከተተ በሁዋላ፣ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ወደ ፊት በጥናትና ይፋ የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮችና፣ በፍትህ አግባብ የሚዳኙ ወንጀሎች በሚጠበቁበት በአሁኑ ሰዓት የትህነግ አመራሮች ለስልጣን መሻኮታቸው በርካቶችን አሳዝኗቸዋል። ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ከመረባረብ፣ በጦርነት የተጎዱ ወጣቶች ስብራትን ለመጠገን ከመስራት ይልቅ ወገን ለይተው ለወንበር የሚደረገውን ግብግብ በክልሉ ያሉ ተቃዋሚዎች በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ብለውታል።
ሙሉ ቃለ ምልልሳቸውን እዚህ ላይ ያንብቡ