ኢትዮሪቪው :- በነዳጅ አከፋፋይነት የተሰማሩ ካምፓኒዎች ዋና ዓላማቸው ነዳጅን በኮንትሮባንድ በመሸጥ ገንዘብ ማግበስበስና ካምፓኒያቸውን ከባንክ ብድር ለማግኘት የሚጠቀሙበት መሆኑ መረጋገጡን ሲሉ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ እስመለአለም ምህረቱ አስታወቁ። ዘርፉ በብልሹ አሰራርና ሌብነት የተዋተ መሆኑን ጠቅሰው ተገልጋዮች መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ሲማጸኑ እንደነበር ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የኤክስፖርት ሃብቷን አሟጣ የምታስገባው ነዳጅ በህገወጥ ወደ ጎረቤት አገራት ሳይቀር እንደሚጓጓዝ፣ ይህም የሚሰራው በቅንጅት እንደሆነ በተለያዩ መደረኮች የሚገለጽና ልጓም ሊበጅለት ያልቻለ ችግር ነው። ዘርፉ ከፍተኛ ብር የሚዘዋወርበትና የተለያዩ አካላት ከላይ እስከታች የሚሳተፉበት በመሆኑ ለቁጥጥር አዳጋች እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
አሁን በጥናት መረጋገጡ ተገልጾ ይፋ እንደሆነው መጥኑ ባይገልጽም ነዳጅን ” ለኮንትሮባንድ ንግድና ብድር ማግኛ በሚል ወደ ዘርፉ የገቡ ኩባንያዎች ስርዓት ይይዛሉ ” ሲል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
” አዋጁ ከፍተኛ ሀብት ወጥቶበት ወደ ሀገር የሚገባውን የነዳጅ ምርት ለተገቢው አካል መድረሱን የሚያረጋግጥ እንዲሆን ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል“ ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል።
በረቂቁ አዋጁ ላይ አጋብ ካላቸው አካላት ጋር መምከሩን ተከትሎ ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው አዋጁ ሲጸድቅ፣ በህገወጥ የነዳጅ ግብይት የታየዘ ግለሰብ ነዳጁ ተወርሶ ከ3 ዓመት በማይበልጥ እስራትና እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል።
አዲስ የነዳጅ ምርት አከፋፋዮች ስራ ለመጀመር ቢያንስ 500 ሺህ ሊትር የነዳጅ ውጤቶች መያዝ የሚችል ማከማቻ ጉድጓድ ወይም ዴፖና አራት ማደያዎችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው አዋጁ ያስገድዳል።
በስራ ላይ ያሉ ማደያዎች ደግሞ አዋጁ ከሚጸድቅበት ጊዜ ጀምሮ ለአዲስ አከፋፋዮች የተጣሉትን ግዴታዎች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። አዲስ ጀማሪ ሆኑ ነባሮቹ በሶስት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ ስድስት ማደያዎችን የመገንባት ግዴታ አለባቸው።
የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጭ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው ቦታና የግብይት ስርዓት ውጭ ሲሸጥ የተገኘ ወይም አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ ከ3 ዓመት በማይበልጥ እስርና ከብር 50 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልበት ረቂቅ ህጉ ያስረዳል።
መንግሥት ከሚያወጣው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ተመን ውጪ በተደጋጋሚ የመገበያየት ወንጀል እንዲሁም የነዳጅ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል እስከ 3 ዓመት እስርና እስከ 300 ሺህ ብር ቅጣት ያስጥላል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ እስመለአለም ምህረቱ በአሁኑ ወቅት የደነዳጅ አቅራቢነት ስራ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ፍላጎቱ ሌላ ፍላጎት ያዘለ መሆኑን አስረድተዋል።
“በድርጅቱ በተደረገው ጥናት ይህ ፍላጎት ለኮንትሮባንድ ንግድ እና ከባንክ ብድር ለመወሰድ ተብሎ የሚደረግ እንደሆነ ተደርሶበታል ሲሉ” ዋና ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የካምፓኒዎቹ ቁጥር ሃምሳ ዘጠኝ መድረሱን የገለጹት አቶ አስመረ ዓለም፣ በዘርፉ የተሰማሩት ጃምፓኒዎች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ከአስር እንደማይበልጡ ጠቁመዋል። ከነዚህም ውስጥ ሶስቱ የመንግሥት ገንዘብ አባክነው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ናቸው ብለዋል።
ሃምሳ ስድስቱ ካምፓኒዎችን በገበያ ድርሻ ህግ መሰረት ተደልድለው ነዳጅ እያገኙ መሆኑን ገልጸው፣ አሰራሩ ስምምነት የሌለበት፣ ሁልጊዜ ጭቅጭቅ ሊለየው ያልቻለ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዘርፉን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ካምፓኒዎች መብዛታቸው፣ ዓላማቸው? ቁጥራቸውስ ያደገበት ምክንያት ምን ሊሆን ይቻላል? የሚለው ግምግማ በጥናት በተደገፈ ድምዳሜ እንደተደረሰበት ዋና ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል። በጥናቱ ውጤት መሰረት ዘርፉን ለመቀላቀል ቁጥራቸው የበዛ ካምፓኒዎች ዋናው ዓላማቸው በኮንትሮባንድ በመስራታቸው ገንዘብ ማግበስበሳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሌላ በኩል ከባንኮች ብድር መውሰድ ዓይነተኛ መንገድ አድርገው እንደሚጠቀሙበት መረጋገጡን ይፋ አድርገዋል።
እነዚህ የነዳጅ ካምፓኒዎች ባንኮች ጋር ሄደው ብድር በሚጠይቁበት ጊዜ ባንኮቹ ” ከእናተ ጋር ያላቸው የሥራ አፈጻጸም ይጻፍልን ” የሚል ጥያቄ እንደሚያቀርቡና ተቋማቸውም ባንኩ በሚጠየቀው መሰረት ደብዳቤ እንደሚጽፍ ገልጸዋል። ካምፓኒዎቹ ከባንክ ለመበደር ሲሉ ወደ ዘርፉ እንደሚገቡ በጥናት መረጋገጡን ቢጠቅሱም ለባንክ ደብዳቤ ከመጻፍ ወደ ሁዋላ ስለማለታቸው ያሉት ነገር የለም።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ የአዋጁ ዓላማ መንግሥት በየዓመቱ በሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጣበትን የነዳጅ ምርት በአግባቡ ለማስተዳደር ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግሥት በኩል የነዳጅ አቅርቦትን የማበራከት ዓላማ እንደሚሌለ ሚኒስትሩ ገልጸው። “አዋጁ በእያንዳዱ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ባሉት ተዋናዮች ላይ የህግ ገደብ ይጥላል። የአቅራቢ፣ የማደያ … ወዘተ ግዴታዎች ያስቀምጣል” ብለዋል።
የአገሪቱ የግብይት ስርዓት ችግር እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የአቅርቦት ችግር ሳይኖር ስርጭት ላይ ትልቅ ችግር መኖሩ የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል። የአቅርቦት ችግር ባይኖርም የታሰበለት ቦታ አግባቡን ጠብቆ እንደማይደርስ በክልሎች የሚቀርበው ቅሬታ ገሚሱ ትክክል እንደሆነ አምነዋል።
ነዳጅ እያለ !! ሳምንት ሁለት ሳምንት ገበያውን ማስራብ ፣ በነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ነዳጅ ይዞ ‘ ቤንዚን የለም ፤ ናፍጣ የለም ‘ ብሎ መለጠፍ የተለመደ መሆኑንን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ እንዲህ ያለው ተግባር ተጠያቂነት የማያስከትልበትና በዘርፉ የሚታዩ የአሰራሩን ባህሪያት ለመቀየር ታስቦበት በመንግሥት አዋጅ ማዘጋጀቱን ሚኒስትሩን ጠቅሰው ከተሰራጩ ዘገባዎች ለመረዳት ተችሏል።
“ከዚህ በኃላ ንግድን አንከለክልም እናሰፋዋለን ፤ ግብይቱ እንዲሳለጥ እንፈልጋለን ነገር ግን ለኮንትሮባንድ ንግድና ብድር ማግኛ ብሎ የገባው ኩባንያ ስርዓት ይይዛል” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የነዳጅ ኮታ እና ስርጭት ላይ ፍትሃዊ ስርዓት ለመፍጠር በትጋት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
“ከአቅርቦት እና ስርጭት ይልቅ ማስተዳደሩ ከባድ ነው። ነዳጅ እያላቸው ዘግተው የሚቀመጡ ማደያዎች በስፋት አሉ። የቅጣት መጠኑ ላይ ጠንካራ ስራ ይሰራል” ሲሉ በዘርፉ ያለውን ችግርና ስር የሰደደ የኮንትሮባንድ ችግር አሳይተዋል።
የተወካዮእች ምክር ቤት በማህበራዊ ገጹ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ሀብት ወጥቶበት ወደ ሀገር የሚገባውን የነዳጅ ምርት ለተገቢው አካል መድረሱን የሚያረጋግጥ አዋጅ እንዲሆን ከወዲሁ መስራት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መግለጹን አመልክቷል።
ቋሚ ኮሚቴ የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ከክልል ከመጡ የስራ ኃላፊዎችና በነዳጅ ምርት አቅርቦት ንግድ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱም፣ ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ 838/2006 ላይ የቁጥጥር ክፍተት ስለነበረበት የረቂቅ አዋጁ መውጣት ብክነትን እና አጠቃላይ በነዳጅ ዘርፉ ለይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አሻ ያህያ ጠቅሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አስቻለ አላምሬ በበኩላቸው፣ ነዳጅን ከአስመጭው እስከ ተጠቃሚው ድረስ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
የነዳጅ ግብይትን እና የነዳጅ ማደያዎችን ተደራሽነት ህጋዊነት ለማረጋገጥ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም የነዳጅ እና ኢነርጅ ባለስልጣን ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ፣ አሁናዊ የነዳጅ አቅርቦት ፣ ስርጭት እና አጠቃቀም ላይ ብክነት ስላለ እና ችግሩን ለመፍታት ረቂቁ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የዋጋ ማስተካከያ ይደረጋል በሚል እሳቤ ነዳጅ እያለ ነዳጅ የለም ብለው የሚዘጉ ማደያዎች መኖራቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ረቂቁ በአስመጭዎች፣ አከፋፋይ እና ማደያዎች ላይ ህጋዊ ስርዓት ለመዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የነዳጅ እና ኢነርጅ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሀርላ አብዱላሂ በበኩላቸው፣ እየተስፋፋ የመጣውን የኮንትሮባንድ ተጋላጭነት ለመቀነስ እና ነዳጅን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተው፣ በቋሚ ኮሚቴው ተነስተው መቀነስ እና መጨመር ያሉባቸውን አስተያየቶች በግብዓትነት እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡
በቴሌግራም ተከታተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk