በየዓመቱ ከ70 ሺህ በላይ ወላድ እናቶችን ሕይወት ይቀጥፋል፤ ነገር ግን አሁንም ሳይንቲስቶችን ግራ እንዳጋባ ነው። ሰባት የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎችን ያሸነፈችው፣ 14 የዓለም ሻምፒዮና ወርቆችን የሰበሰበችው የአሊሰን ፌሊክስ እርግዝና እንደ ሩጫው ሁሉ ቀለል የሚላት መስሏት ነበር።
“በሕይወቴ በሙሉ አካሌ መሳሪያዬ በመሆኑ ስንከባከበው ነው የቆየሁት፤ አሳፍሮኝም አያውቅም” ትላለች ፌሊክስ። “ልምምድ አደርጋለሁ፤ ከዚያም የልምምዴን ውጤት ከአካሌ እጠብቃለሁ። ሁሌም ይሳካልኛል። ስለዚህም የወሊድ ጊዜዬ ተፈጥሯዊ እንደሚሆን ነበር የጠበቅኩት።”
ፌሊክስ ለ32 ሳምንታት የእርግዝና ክትትል ስታደርግ በከፍተኛ የደም ግፊት የተነሳ የአካል ጉዳት የሚያስከትለው አደገኛ የሆነ ፕሪ ኤክላምፕሺያ (ከእርግዝና ጋር የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት) እንደታየባት እና በፍጥነት ሆስፒታል ገብታ ክትትል ማድረግ እንዳለባት ተነገራት።
በሚቀጥለው ቀን ዶክተሮች በቀዶ ሕክምና ሴት ልጅ አዋለዷት።
ከዚያ በኋላም ልጇ ለአንድ ወር ያህል በጨቅላ ሕጻናት ማቆያ ውስጥ ሆና ክትትል ሲደረግላት ቆይታለች።
የሕክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለባት እስኪነግሯት ድረስ አልፎ አልፎ ከእግሯ ማበጥ በስተቀር ልጅም እናትም ደህና ይመስሉ ነበር።
“በዚያ ብዙም አልተደናገጥኩም ነበር። ነገር ግን ደም ግፊቴ እና የፕሮቲን መጠኔ እየወረደ እንደነበር ተረዳሁ። ያስፈራ ነበር” ብላለች።
በአሁኑ ወቅት ፌሊክስ ልጇ አምስት ዓመት የሞላት ሲሆን፣ እንደ እርሷ ተመሳሳይ የደም ግፊት ችግር የገጠማቸው እናቶች በሰላም ወልደው አቅፈው ለመሳም አለመታደላቸውን መስማቷ ዕድለኛ እንደሆነች እንዲሰማት አድርጓታል።

የወላድ እናቶች ገዳይ የሆነው ፕሪ ኤክላምፕሺያ
ከፍተኛ የደም ግፊት (ፕሪ ኤክላምፕሺያ) በእርግዝና ወቅት ወይም በወሊድ በኋላ የሚያጋጥም ከባድ የእናቶች የጤና እክል ነው።
ፕሪ ኤክላምፕሺያ በዓለም ላይ በየዓመቱ በከፍተኛ ደም ግፊት የተነሳ ከሚመጣ ስትሮክ የተነሳ ከ70 ሺህ በላይ ወላድ እናቶችን እንዲሁም ለ500 ሺህ ጽንሶች ሞት ምክንያት ነው።
ይህ ከፍተኛ የደም ግፊት በእርግዝና ወቅት ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቅያ ሊከሰት ይችላል።
በአንዳንድ እናቶች ላይ ከእርግዝናቸው 34ኛ ሳምንት በፊት ሲከሰት፣ ሌሎች ላይ ደግሞ ከዚያ በኋላ ያጋጥማል።
ፕሪኤክላምፕሺያ ከፍ ባለ የደም ግፊት እና እንደ ጉበት እና ኩላሊት ባሉ የአካል ክፍሎች ላይ ሊደርስ በሚችል ጉዳት የሚታወቅ ከባድ የእርግዝና ችግር ነው።
በህመሙ ላይ ምርመር የሚሠሩ ባለሙያዎች ለምን እንደሚከሰት የተወሰኑ ፍንጮችን መለየት ችለዋል።
ከፍተኛ የሆነ የደም መቆጣት ከማህጸን ጀምሮ በእናትየው እና በጽንሱ መካከል ያለውን ግንኙነት ይረብሸዋል።
በተናጠል ለማየት በማህጸን ውስጥ ለጽንሱ የሚያስፈልገውን ምግብ እና አየር የሚያቀብሉት የደም ሥሮችን መልካቸውን እንዲቀይሩ ያደርጋል።
በእንግዴ ልጁ ውስጥ የሚያልፈው የደም ዝውውር ሲረበሽ የእናትየው አካል የደም ግፊቷን የምትቆጣጠርበትን መንገድ በማወክ ቀስ በቀስ ወደ ደም ግፊት እና ወደ ፕሪ ኤክላምፕሺያ ያመራል።
በዩናይትድ ኪንግደም ፕሪ ኤክላምፕሺያ ላይ የሚደረግ ጥናትን የሚመሩት እና በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢያን ዊልኪንሰን “አንዲት እናት ስታረግዝ ልቧ ለልጇ እና ለእንግዴ ልጁ ተጨማሪ ደም ይረጫል” ይላሉ ።
“በየደቂቃው ልቧ የሚረጨው ደም [ጤነኛ በሆነ እግዝና ወቅት] አንድ ከግማሽ ወይንም ሁለት እጥፍ ይሆናል።”
ወፍራም የሆኑ እና ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ እንዲሁም የተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅማቸው ችግር ያለበት (autoimmune disorder) እናቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።
ፕሮፌሰሩ ይህንን ይበሉ አንጂ አሁንም ቢሆን የተወሰኑ እናቶች ለምን ፕሪ ኤክላምፕሺያ እንደሚያጋጥማቸው፣ አንዳንዴም ያለምንም ቅድመ ምልክት ለዚህ ችግር እንደሚጋለጡ ሊታወቅ አልተቻለም።
በተለይ ደግሞ ጥቁር እናቶች በይበልጥ በአደገኛ ሁኔታ ለጉዳት የሚዳረጉ እና ለዚህ ዓይነት ችግር 60 በመቶ የተጋለጡ መሆናቸው ተደርሶበታል።
ይህ ግን ደካማ የሆነ የጤና ክብካቤ አገልግሎት እና የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ይታመናል።
በፌርፋክስ ቨርጂንያ የኤኖቫ ኩባንያ ዳይሬክተር የሆኑት ጋሪማ ሻርማ “የተወሰኑ የማኅበረሰብ አባላት በጤና አጠባበቃቸው እና በሚያገኙት አገልግሎት የተነሳ ከሌሎቹ ጋር የተስተካከለ ቅድመ መከላከል ሕክምና የማያገኙ ከሆነ እንዲሁም ቀድሞ ለመለየት የሚያስችል ምርመራ ካላደረጉ ይከሰታል” ብለዋል።
ሻርማ አክለውም ይህ ግን ፕሪ ኤክላምፕሺያ ለምን እንደሚከሰት ሊያስረዳ አይችልም ብለዋል።
ዶክተሮች የበሽታው መንስዔ ዕድሜ፣ የዘር ሁኔታ እንዲሁም የቀደመ የጤና ሁኔታ ለፕሪ ኤክላምፕሺያ ምክንያት መሆናቸውን ቢናገሩም የበሽታውን መነሻ ምክንያት በመገመት ረገድ ግን እጅጉን ርቀዋል።
አዲስ እና የተሻሻለ ምርመራ የሕክምናውን ዓለም ሲተዋወቅ ግን ሳይንቲስቶች ማን ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆነ እና ለምን እንደሚጋለጥ የበለጠ ይነግሩናል ይላሉ።

ፕሪ ኤክላምፕሺያን መገመት
ዶክተሮች እንደ ካንሰር ወይንም ሌሎች ጽኑ የጤና ችግሮችን ሲመረምሩ እክሉ ከገጠማቸው ሰዎች የውስጥ አካል ለተጨማሪ ምርመራ ናሙና (ባዩፕሲ) ይወስዳሉ።
ነፍሰጡር ሴቶች ማህጸን ውስጥ ግን ምን እየተከናወነ መሆኑን ለመረዳት እና ለማጥናት ቀላል አይደለም።
በሲድኒ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ላና ማክሌመንትስ “እንዲሁ ዝም ብለን በየጊዜው ከነፍሰጡር ሴት እንግዴ ልጅ ናሙና ልንወስድ አንችለም፤ ምክንያቱም ጽንሱ የመቋረጥ ዕድሉ ሰፊ ነው” ይላሉ።
ከዚያ ይልቅ ተመራማሪዎች ችግር መኖሩን ለማወቅ በደም ውስጥ ያሉ ያልተለመዱ ሞለኪውሎችን ደረጃ መመልከት ይኖርባቸዋል።
በተለይ በማህፀናቸው አካባቢ ከፍተኛ መቆጣት የሚገጥማቸው ሴቶች የእንግዴ ልጁ አንዳች ዓይነት ፕሮቲን በመልቀቅ ምላሽ ይሰጣል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ፕሮቲን በጽንሱ እና በእናትየው መካከል መቆጣት እንዲኖር በማድረግ አደገኛ የሆነ ተጽዕኖ ይፈጥራል።
በማሳቹሴቴስ የሕክምና ትምህርት ቤት ባዮሎጂስት የሆኑት ክሬግ ሜሎ “የፕሪ ኤክላምፕሺያ ህሙማን ከመደኛው የፕሮቲን መጠን በ100 እጥፍ ከፍ ያለ ይኖራቸዋል” ይላሉ።
“ስለዚህ በፕሪ ኤክላምፕሺያ ምክንያት የአካል ጉዳት ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ ለመመርመር ያስችላል።”
ባለፈው ዓመት ቴርሞ ፊሸር ሳይንትፊክ የተሰኘው ኩባንያ ፕሪ ኤክላምፕሺያን ለመመርመር የሚያስችል በአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን እውቅና የተሰጠው ቴክኖሎጂ አስተዋውቋል።
እንደዚህ ዓይነት የሕክምና ቴክኖሎጂዎች በፍጥነት መፈብረክ እንዲህ ዓይነት የጤና እክሎችን ለመመርመር ወይንም ለማከም ይረዳሉ።
በዚህ ህመም ደግሞ የሚፈጠረው የፕሮቲን መጠን ከሌላ ዝቅተኛ ከሆነ ፕሮቲን ጋር ለማነጻጸር፣ መደበኛ የሆነውን የእንግዴ ልጅ እድገትን ለመከታተል የሚደረገውን አስተዋጽኦ ያግዛል።
ይህ ታድያ አንዲት የደም ግፊት ታይቶባት አልጋ ያዘች ነፍሰጡር እናት በቀጣዩቹ ሁለት ሳምንታት ፕሪ ኤክላምፕሺያ ልታዳብር ትችላለች አትችልም የሚለውን ለመለየት ይረዳል።
የዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ ውጤታማነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 ከ18 የተለያዩ ሆስፒታሎች በተመረጡ 700 ነፍሰጡር እናቶች ላይ የደም ግፊት ሲታይባቸው ምልክቱ ከመባባሱ በፊት የተጠናከረ ክትትል እና እንክብካቤ ተደርጎ ውጤታማነቱ ተፈትሿል።
ይህ አዲሱ የምርመራ ቴክኒክ የእናቶችን ሕይወት እንደሚታደግ በሚነገርበት ወቅት በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነችው ሲንዲ አንደርሰን ለፕሪ ኤክላምፕሲያ ተጋላጭ የሆኑትን ቀድሞ ለመለየት የበለጠ የተሻሻለ የምርመራ በእርግዝናዎቹ መጀመሪያ ወራት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ትናገራለች።
የእንግዴ ልጁ ሙሉ በሙሉ ሳይጎለብት የፕሪ ኤክላምፕሺያ ምልክቶችን መለየት ከተቻለ ለመከላከል የሚኖረው ዕድል ሰፊ ይሆናል።
አንደርሰን “ ከዘጠኝ ሳምንት በኋላ እንግዴ ልጁ መልክ ይይዛል፤ ስለዚህ ምልክቶቹን ቀድሞ መለየት እንችላለን፤ በዚህም እናቶች ሕክምና ቀድመው እንዲጀምሩ በማድረግ ችግሩን መከላከል አልያም ማዳን ያስችለናል” ትላለች። ይህንን ለመመሞከር እና ውጤታማ ለመሆን የሳይንቲስቶች ቡድን በአዲስ ቴክኖሎጂ ላይ በጋራ በመሆን ምርምር እያካሄዱ ይገኛሉ።