ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውና ሸኔ በቅርቡ በሚታወቅ ደረጃ ሁለት ቦታ መከፈሉ ይታወሳል። በገሃድ ሁለቱ ወገኖች ጃል መሮና ጃል ሰኚ ልዩነታቸውን ይፋ አውጥተው መናገራቸውን ተከትሎ የጃል ሰኚ ወገኖች ከመንግስት ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒከሽን ቢሮ ሃላፊ ሰሞኑን ንግግር እየተደረገ መሆኑን ተናገሩ።
ኦነግ ሸኔ በግልጽ ሁለት ቦታ ተከፍለ ይባል እንጂ ውስጡ አራት ቦታ መሰነጣጠቁን የሚገልጹ ህዝብ ለእነዚህ ሁሉ ቡድኖች እየገበረ፣ ቀለብ እየሰፈረ፣ ልጆቹ እየታገቱበት፣ መውጫና መግቢያው ተዘግቶበት እየተሰቃየ በመሆኑ ” ይብቃ” በሚል ህዝብ ድምጹን ከፍ አድርጎ እያሰማ ነው።
ሰሞኑን በሰላማዊ ስለፍ ህዝብ “የሰላም ያለህ” በሚል ቀንበር ተሸክሞ መንግስትንም ሆነ ተቀናቃኞች ወደ ሰላም እንዲመጡ ሲማጸን ታይቷል። ቀደም ሲል የተጀመሩና የተበላሹ የሰላም ደርድሮች እንዲቀጥሉ ህዝብ ጠይቋል። አባ ገዳዎች፣ አደ ስንቄዎችና የሚሰሙ የክልሉ ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ የማቀራረብ ስራ ሲሰሩ እንደነበር ይታወሳል።
የሰላም ማጣት በኦሮሚያ በተረጂነት የማይታወቁ አካባቢዎችን ሳይቀሩ የመንግስት እጅ ጠባቂ አድርጓቸዋል። መንግስት እርምጃ ለመውሰድ፣ ታጣቂዎቹ ግዛታቸውን ለማስፋት በሚያደርጉት ፍልሚያ የተጎዳው ህዝብ ” እንዴት ከዚህ ቀውስ ይወጣል” የሚለው ጥያቄ በበርከተበት ወቅት ነበር ጃል ሰኚ ” ስርዓት ተፍቷል። በግለሰብ አንመራም። ተጥያቂነት የሌለበት ትግል ህዝባችንን ዋጋ እያስከፍለ ነው” በማለት ጃል መሮን በይፋ አውግዘው የሰላም ወይይት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታወቁ።
ዛሬ የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላት ጋር እየተደረገ ባለው ውይይት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ እንደሆነ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል። ስምምነቱ በጃል ሰኚ ጋር ስለተጀመረውና ውጤት ስላስገኘው የሰላም ንግግር በይፋ ይናገር እንጂ፣ ሌሎች በሁለት አቅጣጫ ያሉ የሰራዊት አመራሮችም ጋር በተመሳሳይ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ሰምተናል። ንግግሩ ገና በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ዝርዝር ማቅረብ እንደማይችሉ የጠቆሙን እንዳሉት ከአሁን በሁዋላ ዛንዚባርና ታንዛንያ የሚወስድ ጉዳይ ሊኖር አይችልም።
የክልሉ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ለኦሮሞ ሕዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ ሲባል ልዩነትን ለማጥበብና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን በይፋ አውጇል። በውይይቱም በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ መሆኑንም መግለጫው አረጋግጧል።
ለውጡ ከመጣ ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ለተለያየ ችግር የሚጋለጠው የውስጥ አንድነት በማጣቱ መሆኑ ታምኖበት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህዝቡ አንድነት ያልተነሳበት መድረክ እንዳልነበረ በመግለጫው ተመልክቷል።
ሲደረግ የነበረው የሰላም ጥሪም ያለማቋረጥ እንደነበረ ገልጾ የኦሮሞ ህዝብ በተለያየ ጊዜ ያደረጋቸው ትግሎች ፍሬ ያላፈሩት በውስጥ አንድነት እጦት መሆኑን መግለጫው አክሎ አትቷል።
የለውጡ መምጣትም የኦሮሞን ህዝብ አንድነት የበለጠ እንደሚያጠናክር በማመን የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተሰራው ስራ ትልቅ እድል እንደነበረ ተመልክቷል።
በወቅቱ መልካም ጅማሮዎች እንደነበሩ ቢታወቅም ብዙም ሳይቆይ በመሳሳብና አንዱ ለሌላው እንቅፋት በመሆኑ ችግሩ ለስድስት ዓመታት እንደዘለቀም ተጠቅሷል፡፡
ህዝቡም ያልተገባ መሰዋእትነት እንዲከፍል መገደዱን ያተተው መግለጫው የስድስት ዓመታቱ የለውጥ ጉዞ በሰላማዊ ጉዞ የታጀበ ቢሆን ሮኖ ብዙ ርቀት መጓዝ ይቻል እንደነበረም አንስቷል።
ችግሩ እንዲቆምና በኦሮሞ መካከል አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ እንደ መንግስትም ሆነ እንደ ብልጽግና ፓርቲ የሰላም ጥሪ ያልቀረበበት ጊዜ እንደሌለም መግለጫው አስታውሷል።
ከሸኔ ጋር በሁለት ዙር የተደረገው የሰላም ውይይት ባይሳካም ተስፋ በመቁረጥ የሰላም መንገዱ እንዳልተዘጋና ይልቁንም በተከታታይ የሰላም ጥሪ ሲቀርብ እንደነበረ መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብም እንደ ባህሉና እንደ ወጉ እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን እነዚህ የሰላም ጥሪዎች ውጤት አላፈሩም ማለት አይቻልም ሲል መግለጫው አንስቷል።
በሺህ የሚቆጠሩ የሸኔ አባላት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ተመልሰዋል፤ የተሃድሶ ስልጠና ወስደውም ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ለብዙዎቹም የስራ እድል ተፈጥሯል ብሏል።
ሰሞኑን በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም በርካታ ወጣቶች የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ ወደ ሰላም እየተመለሱ መሆኑን ያብራራው መግላጫው ሰላምን ተጠምቶ የነበረው ህዝብም የክብር አቀባበል እያደረገ እንደሚገኝ አንስቷል።
አሁንም ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት የሚቻለው ከቡድኑ አመራር አባላት ጋር ስምምነትና መግባባት ሲፈጠር በመሆኑ ከቡድኑ አመራሮች ጋር ያልተቋረጠ ውይይት ሲደረግ መቆየቱም በመግለጫው መጠቀሱን መግለጫውን የጠቀሱ የመንግስት መገናኛዎች አመልክተዋል።
ውይይቱም በክልሉ ውስጥ እርቅና ሰላም ማውረድ ላይ አተኩሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን የሰላም መንገድ አዋጭ መሆኑን ከተቀበሉ አመራርና አባላት ጋር በተደረገው ውይይት መግባባት እየተፈጠረ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና ለሰላም የተከፈተው በርም ለሌሎችም ክፍት መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።