“ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት የተመለሱት ዶናልድ ትራምፕ እርሻ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩትን ሰነድ አልባ ካባረሩ ማን ድንችና ሽንኩርት ይልቅማል?” በሚል ሰፊና በአምክንዮ የተደገፈ መከራከሪያ የሚያቀርቡ እንደሚሉት ጉዳዩ የምርጫ ማሟሟቂያ ከመሆን እንደማይዘል ይገልጻሉ። እነዚሁ አካላት እንደሚሉት ግን ድንበር አካባቢ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚጀመር ግን ያምናሉ።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ” አገርህን እየተነጠቅህ ነው” የሚል ስሜት ዘርተው ለማሸነፊያ የተጠቀሙበት አንዱ የምርጫ ዘመቻ አጀንዳቸው የሆነውን ሰነድ አልባ ስደተኞችን የማባረር ዕቅድ እንደሚተገብሩ ማስታወቃቸው ከአስር ሺህ የሚልቁ ግብርና ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን በማን ይተካሉ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የላቸውም። ጉዳዩ ስራ ሲጀምሩ የሚታይ ቢሆንም ይተግበር ከተባለ ጉዳዩ ከአሜሪካ ገበሬዎች ዘንድም ተቃውሞ እንደሚያስነሳ ከወዲሁ የሚገልጹ አሉ።
በአሜሪካ ሰነድ አልባ የሚባሉና በተለያዩ ደረጃ የሚመደቡ ከአስራ አንድ እስከ ሃያ ሚሊዮን የሚዘልቁ የሌላ አገር ዜጎች እንደሚኖሩ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። እንዴት ባለ መንገድ እንደሚያስፈጽሙት ባይታወቅም ትራምፕ ከ11 ሚሊዮን እስከ 21 ሚሊዮን ሰዎችን ከአሜሪካ ሊያስወጡ እንደሚችሉ ውሳኔያቸውን ተለክትሎ ተነግሯል። ፒው ሪሰርች ሴንተር ‘ 2021 ላይ ይፋ ባደረገው ዳታ 10.5 ሚሊዮን ዶክመንት የሌላቸው ሰዎች አሜሪካ ውስጥ መኖራቸውን በራሱ ስሌት ገልጿል። ምንም ይሁን ምን እኒህ እርሻ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይባረሩ ከተባለ ማን ድንችና ሽንኩርት እየለቀመ ገበያውን ይሞላዋል? የሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን እየተነሳ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ከ’ታይም’ መጽሔት ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወደ ስልጣን ከመጡ እስከ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕገ ወጥ ያሏቸውን ስደተኞችን ከአገር ጠራርገው እንደሚያስወጡ ዝተው እንደነበር ይታወሳል።
ከመቼው ጊዜ በላይ በስደተኞች እየተጥለቀለቀች ባለችው አሜሪካ የሠነድ አልባ ስደተኞች ጉዳይ የምርጫ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ በዘለቀበት ምርጫ ትራምፕ ያሉትን ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን ከአሸናፊነታቸው አዋጅ በሁዋላም አጽንተዋል።
በአገራቸው የህግ ሥርዓት ላይ ጫና እያሳደሩ እንደሆነ የሚገልጿቸው ሰነድ አልባ ስደተኞች፣ ለወንጀል መበራከት ምክንያት መሆናቸውንም ነው ሲገልጹ የነበረው። እናም አሜሪካ ህግ የሚከበርባት አገር ትሆን ዘንድ ስደተኞቹን ወደ መጡበት አገር በጅምላ እንደሚመልሷቸው ሲያስታውቁ ድጋፍ የሰጡዋቸው ጥቂት አልነበሩም።
ከጾታ ጋር በተያያዘና በስደተኞች ጉዳይ በያዙት አቋም ምርጫ ላይ ድጋፍ ሊያጡ እንደሚችሉ ቢገለጽም ተፎካካሪያቸውን በሰፋ ልዩነት አሸንፈው ሲያበቁ ” ያልሞትኩት ለዚህ ነው ” በሚል ልዩ ቅባት ያላቸው አስመስለው ራሳቸውን በማሳየት ቃላቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ መነሳታቸውን ሲያስታውቁ በርካቶች ስጋት ገብቷቸዋል።
ትራምፕ ይህን ዕቅዳቸውን ለማስፈጸም የአገሪቱ ጦር አካል የሆነው ብሔራዊ ዘብን (ናሽናል ጋርድ) የማሰማራት ዕቅድ እንዳላቸው አስቀድመው ባስታወቁት መሰረት ይሁን በሌላ ነገሩ ተግባራዊ መሆኑ አይቀሬ ነው ተብሏል።
የትራምፕ ዘመቻ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት እንደገለፁት ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው ከሚወስዷቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች መካከል አንዱ ዶክመንት የሌላቸው / ሰነድ አልባ ስደተኞችን በብዛት ለማስወጣት የገቡትን ቃል መፈጸም እንደሆነ አስታውቀዋል።
ቃል አቀባዩ ትራምፕ በአሜሪካ ህዝብ ዘንድ አስደናማሚ የተባለ ድል ማስመዝገባቸውን አስታውሰው ” ይህ ድል ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ” ሲሉ ተናግረዋል። ይህም ሰነድ አልባ ስደተኞችን በብዛት / በገፍ ወደ መጡበት ሀገር መመለስ (ማስ ዲፖርቴሽን) እንደሆነ ጠቁመዋል።
አንዳንድ ሚዲያዎች ይህ ሰነድ አልባዎችን በብዛት ከአሜሪካ የማስወጣቱ /ማስ ዲፖርቴሽን/ ተግባር የትራምፕ የመጀመሪያው ቀን ስራ ይሆናል የሚል ዜና አስነብበዋል።
ሰነድ የሌላቸውን የሌላ አገር ዜጎች ” ከአሜሪካ ምድር ጓዛቸውን አስይዘን ወደ መጡበት እንልካቸዋለን ” ያሉት ትራምፕ፣ ቃል አቀባያቸው እንዳሉት ወደ ተግባር ከገቡ በስልጣን ዘመናቸው ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ከአሜሪካ ያወጣሉ። ጉዳዩን የሚከታተሉ ጎን ለጎን የሚያነሱት ይህን ለመፈጸም ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል የሚለውን ነው።
ምን ያህል በጀት ያስፈልጋቸው ይሆን ?
ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ሰዎችን ከአሜሪካ ለማስወጣት ምን ያህል በጀት ያስፈልጋቸው ይሆን ? ይህ ጥያቄና ስጋት ጎን ለጎን እየተነሳ ነው።
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልክ በፕሬዚዳንትነት ስራ ሲጀምሩ የመጀመሪያ ስራቸው ይሆናል የተባለው በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ የተባለ ዶክመንት የሌላቸው ሰዎችን ከሀገር ማስወጣት / የዲፖርቴሽን ስራ ነው። ይህ ግዙፍ የተባለ ዲፖርቴሽን በቢሊዮን ዶላሮችን ሊጠይቅ እንደሚችል ከሌሎች ወገኖች ቢነሳም፣ እሳቸው ግን ይህ የዲፖርቴሽን ጉዳይ ምንም የተለየ በጀት እንደማያስፈልገው እየገለጹ ነው። እንዲያውም ያሉት ” ዋጋ አትለጥፉበት” ነው።
በሳቸው የስልጣን ዘመን የአሜሪካ ድንበሮቿ እጅግ ጥብቅ እንደሚሆኑና ጥበቃው እንደሚጠናከር ትራምፕ አመልክተዋል።
በሀገሪቱ ሰዎች እየተገደሉ እና የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ ጌቶች ሀገሪቱን እያወደሙ የሚኖሩበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ትራምፕ ሲገልጹ ” እውነት ለመናገር ምንም ምርጫ የለንም ” ነው ያሉት።
” አሁን እነዚህ ሰዎች እዚህ አይቆዩም ፤ እንዲቆዩም አይደረግም ወደነዛ ሀገራት ይመለሳሉ ” ሲሉ የሚመለሱበትን አገር ስም ሳይጠሩ ተናግረዋል።
የበጀትም ይሁን የትግበራ ችግር እንደማይኖር ሲያስታውቁ ” በቀላል መመሪያ ነው የማስተዳድረው ” በማለት ነው። ” የገባሁትን ቃልኪዳን አክብራለሁ አስፈጽማለሁ ” ሲሉም በዚሁ አቋም ነው።
እሳቸው “ቀላል” ያሉትና በመመሪያ እንደሚፈጸም ያስታወቁት የዲፖርቴሽን ጉዳይ ቀላል እንዳልሆነ የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። እንቅጩን ምን ያህል ሰነድ አልባ ስደተኞች በአሜሪካ እንደሚኖሩ ባይታወቅም ከ11 ሚሊዮን እስከ 21 ሚሊዮን ሰዎችን ከአሜሪካ ለቀው እንደሚወጡ እየተነገረ ነው።
‘ ፒው ሪሰርች ሴንተር ‘ 2021 ላይ ይፋ ባደረገው ዳታ 10.5 ሚሊዮን ዶክመንት የሌላቸው ሰዎች አሜሪካ ውስጥ አሉ። ከአንዳንድ ትናንሽ አገራት ህዝብ ቁጥር በላይ ሰነድ አልባ ስደተኞችን የተሸከመችው አሜሪካ፣ በየአገሩ ለተፈጠረው ቀውስና ስደት ቀዳሚ ተጠያቂ ትደረጋለች። አሜሪካ ብቻ ሳትሆን የአውሮፓ ተስፋፊና ሃብት ማግበስበስ የለመዱ ለጥቅማቸው ሲሉ እርስ በርስ የማጫረስ መርህ እንደሚከተሉ ሰነድ የሚደግፈው መረጃና ማስረጃ አለ።
በርከት ያለ ጥሬ ሃብት፣ ማዕድንና የመሬት ስብ ያላቸው አገራትን ሆን ብሎ በማጫረስ፣ አማጺ በመፍጠር፣ ወዘተ ህዝብን ለስደት የሚዳርጉ አውራዎቹ አገራት ዓለም ላይ ለከፋው ዕልቂትና ስደት ተተያቂ መሆናቸውን በመግለጽ ቀደም ሲል ውስጥ ውስጡን የነበረ ተቃውሞ አሁን አሁን ገሃድ እየወጣ እንደሆነ አንዳንድ አገራት እያሳዩ ነው።