የ2017 የበጀት አመት ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የ582 ቢሊየን ብር የበጀት ጭማሪ በአብላጫ ድምጽ በ3 ተቃውሞ እና በአምስት ድምጸ ታቅቦ የበጀት ጭማሪው መፅደቁ ተገልጿል። ባለፈው 971 ቢሊዮኑ በጀት መጽደቁ ይታወሳል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዛሬው ዕለት በተካሄደው 6ተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ተኛ ዓመት 6ተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የሰራተኞችን ደሞዝ ጭማሪ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ተጨማሪ በጀቱ አልባዛም ወይ ? በገበያ ውስጥ የዋጋ ግሽበትን አያስከትምልም ወይ ? ከተጨማሪ በጀቱ 282 ቢሊየን ብር ከግብር የሚሰበሰብ ከሆነ በግብር ከፋዮች ላይ ጫና አያሳድርም ወይ ? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። በሚል ከምክር ቤቱ ጥያቄ ተነስቶ ነበር።
የገንዘብ ሚኒትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የቀረበው ተጨማሪ በጀት 120 ሚሊየን ህዝብ ላላትና በኢኮኖሚ በማደግ ላይ ላለች ሀገር ብዙ የሚባል አይደለም ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በጀቱ ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ከሚገኝ ገቢ የሚሸፈንና ዝቅተኛ ተከፋይ ለሆኑ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ለሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች የሚውል በመሆኑ በዋጋ ግሽበቱ ላይ ለውጥ እንደማያስከትልም አመልክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የጸደቀው አዲሱ የበጀት ጭማሪ ማጽደቅ የተፈለገው የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያ ተከትሎ እንደሆነ አስረድተዋል።
መንግስት በሰራተኞች ደሞዝ ላይ ያደረገው የደሞዝ ጭማሪ ቀድሞ ከነበረበት የደሞዝ መጠን ሶስት እጥፍ የጨመረ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ይህም ማለት ቀደም ሲል 1 ሺህ 500 ብር ይከፈለው የነበረ ሰራተኛ መንግስት ካደረገው የደሞዝ ጭማሪ በኋላ ወደ ከ4 ሺህ 500 እስከ 4 ሺህ 700 ብር ከፍ እንደሚል ገልጸዋል።
በተለይም የደሞዝ ጭማሪው ዝቅተኛ የወር ደሞዝ ባላቸው ሰራተኞች ላይ ሙሉ በሙሉ በሶስት እጥፍ መጨመሩን እና ከፍተኛ ደሞዝ ለሚከፈላቸው ሰራተኞች እንደየእርከናቸው የደሞዝ ጭማሪ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።