እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ 2021 ጀርመንን የመጀመሪያዋ ሴት ቻንስለር ሆነው የነበሩት አንጌላ መርክል “ፍሪደም-ሜሟር 1954-2021” የሚል ግለ ታሪካቸውን በመፅሐፍ አሳትመዋል።
የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርክል በአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ብዙ ተወያይተዋል፣ ተከራክረዋል እንዲሁም ተጨቃጭቀዋል። በተገናኙ ቁጥር ውይይታቸው በውጥረት የተሞላ ነበር።
የጀርመኗ ጠንካራ ሴት በአውሮፓ ህብረት በግንባር ቀደምትንት ተፅዕኖ ያደረጉ መሪ ናቸው። አገራቸው ለአውሮፓ ህብረት ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የአንበሳውን ድርሻ እንዳላት ሁሉ እርሳቸው በህብረቱ ፖለቲካም ግንባር ቀደምት ተዋናይ ነበሩ።
በአሜሪካና በአውሮፓ ህብረት መካከል የነበረውን ግንኙነት፣ አንጌላ መርክል ገነን ብለው በሚታዩበት በህብረቱ በኩልና አንደ ጀርመን መሪነታቸው በሌላ በኩል ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት በትራንስ-አትላንቲክ ትብብር ዙሪያ ብዙ ተሻኩተዋል።
ትራምፕ “ቅድሜያ ለአሜሪካ” እና “አሜሪካን አንደገና ታልቅ እናደርጋለን” በሚለው መርሃቸው ምክንያት ከአውሮፓ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደቀድሞው ከትብብር ይልቅ ወደ ውጥረትና መጠራጠር አምርቶ ነበር።
ከአውሮፓ ህብረት፣ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከፓሪስ የዓየር ንብረት ስምምነት፣ ከኢራን የስድስዮሽ የኒኩሌር ስምምነት ወዘተ ጋር በተያያዘ ሰውዬው እንደቀደምት የአሜሪካ መሪዎች ቀላል ሆነው አልተገኙም።
ሰሞኑን የቀድሞዋ ቻንስለር አንጌላ መርክል እነዚህንና የጀርመን-አሜሪካ ግንኙነትን እንዲሁም የግል ትውስታዎቻቸውን በየሚዳስሰው መፅሃፋቸው ደጋግመው ካነሷቸው የአገራት መሪዎች መካከል የአሁኑ ተመራጭ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግንባር ቀደሙ ናቸው።
አንጌላ መርክል መፅሃፋቸው መታተሙን ተከትሎ ከተለያዩ ሚዲያዎች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል። ከጣሊያኑ ዕለታዊ ኮሪዬር ዴላ ሴራ ጋር በነበራቸው ቆይታ ታዲያ “ትራምፕ በኒውዮርክ የበዙ የጀርመን መኪኖች መኖር ይከነክነው ነበር” ብለዋል።
“ፕሬዝዳንት ሆኜ ከተመረጥሁ በጀርመን መኪኖች ላይ ከፍ ያለ ታሪፍ በመጣል ከማንሃታን ጎዳናዎች ላይ እንዲጠፉ አደርጋለሁ” ብሎኛል ሲሉ ሰውዬው ከቻይና ጋር እንዳደረገው ሁሉ ከጀርመን ብሎም ከአውሮፓያን አገራት ጋርም የንግድ ጦርነት ለመክፈት እንደሚፈልግ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ለ16 ዓመታት በቻንስለርነት ጀርመንን የመሩት ብረቷ አንጌላ፣ መርክል ትራምፕ ሁሉምን ነገር የሚያዬው ከሃብትና ንብረት ባለሃብትነት አንጻር እንጂ እንደ ፖለቲካ አይደለም ይላሉ። ለሱ ሁሉም አገሮች እርስ በርስ የሚፎካከሩ/የሚወዳደሩ እና የአንዱ አገር ስኬት ለሌላው አገር ውድቀት እንደሆነ ነው የሚመለከተው ሲሉ የሰውዬውን የተናጠል አመራር መርህ ያብራራሉ።
ሃብትን በትብበር በማልማት በጋራ መጠቀም አንደሚቻል አያምንም የሚሉት አንጌላ መርክል ከትራምፕ ጋር የማደርገው ውይይት ብዙ ጊዜ አሱ በስሜት እኔ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ነበር ይላሉ።
እ.ኤ.አ. በ2017 በዋይትሃውስ የነበራቸውን ስብበሰባ አስመልክተው በመፅሐፋቸው “ወደ አገሬ ስመለስ የደረስኩበት ድምዳሜ ከትራምፕ ጋር በትብብር መስራት እንደማቻል ነው” ሲሉ የሰውዬውን አስቸጋሪነት ይገልጻሉ።
በዛው ስብሰባቸው ትራምፕ አንድ ጥያቄ ጥይቋቸው አንደነበር ፅፈዋል። እሱም ስለ ቭላድሚር ፑቲን ያላቸውን አመለካከት። “በርግጠኝነት ስለ ሩሲያው ፕሬዝዳንት የተለዬ አድናቆት እንዳለው ተገንዝቤያለሁ” ሲሉ ትራምፕን ስለ ፑቲን ያለውን አመለካከት ጠቅሰዋል።
“በቀጣዮቹ ዓመታት ትራምፕ አምባገነንነትና ጨቋኝነት ባህርይ ያላቸው መሪዎች አንደሚስቡት ተገንዝቤያለሁ” ሲሉ የጻፉት መርከል በምስራቅ ጀርመን መወለዴና የኋላ ታሪኬ እንዲሁም ከፑቲን ጋር ስላለኝ ግንኙነትም ለማወቅ ትራምፕ ከፍተኛ ጉጉት እንደነበረው ፅፈዋል።
በአንድ ወቅት ከካቶሊኩ ጳጳስ ከፖፕ ፍራንሲስ ሰውዬውን አንዴት መያዝ አንደሚገባቸው ምክር ጠይቀው እንደነበርና “ግትር አትሁኚ፣ ግን ጠበቅ በይበት” እንዳሏቸው አስፍረዋል።
የትራምፕን ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት መመረጥን ተከትሎ አንጌላ መርክል መጭው ጊዜ ለአውሮፓ ቀላል እንደማይሆን ፍራታቸውን ገልጸዋል።
ዋልታ