በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ከምትሰራበት ቤት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እና ገንዘብ ሰርቃ የተሰወረች ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሏን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
ተጠርጣሪዋ ወንጀሉን የፈጸመችው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አያት ዞን 1 ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ነው።
ተጠርጣሪዋ በደላላ አማካኝነት በቤት ሰራተኝነት ከተቀጠረችበት መኖሪያ ቤት በሶስተኛ ቀን ቆይታዋ የግል ተበዳይ ወደ ስራ በሄዱበት ወቅት አጋጣሚውን በመጠቀም በቤቱ ውስጥ የተቀመጠውን የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ እንዲሁም የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጥ ሰርቃ ትሰወራለች።
ይህን ተከትሎም የግል ተበዳይ የተፈፀመባቸውን የወንጀል ድርጊት ለመሪ ሉቄ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ያመለክታሉ፡።
ተጠርጣሪዋ የወንጀል ድርጊቱን ከፈፀመች በኋላ የግል ተበዳይ ጋር ከመቀጠሯ በፊት በክፍለ ከተማው ወረዳ 14 አባዶ አካባቢ ለሦስት ወራት ተከራይታው በነበረ ኮንዶሚኒየም ቤት ትደበቃለች።
የፖሊስ አባላት ባደረጉት ክትትል ከሰረቀቻቸው የተለያዩ አልባሳት፣ የሴትና የወንድ ጫማዎች፣ 18 ሺህ የአሜሪካ ዶላርና የህንድ ሩፒ፣ የወርቅና ልዩ ልዩ ጌጣጌጥ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሏን ከክፍለ ከተማው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በተጨማሪም ተጠርጣሪዋ በሁለት የተለያዩ ስሞች የነዋሪነት መታወቂያ እንደተገኘባትም ተገልጿል።
ተጠርጣሪዋ በእጇ ላይ የተገኘውን የውጭ አገራት ገንዘብ ከየት ያመጣችው እንደሆነ ፖሊስ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ በተለይ ለEBC DOTSTREAM ገልፀዋል።
የቤት ሰራተኛዋ በተለያየ ወቅት በተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ወንጀል ስትፈፅም የቆየች እንደሆነች እና በእጇ ላይ የተያዙት የውጭ አገራት ገንዘብ እና ሌሎች ንብረቶችን ከየት የተገኙ እንደሆነ የሚደረገው የማጣራት ስራ የሚቀጥል መሆኑን ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ጠቁመዋል።

EBC DOTSTREAM