… ያ ከእግር እራሱ ያፈራው ባቄላ እና አተር በጊዜ ካልተሠበሠበ የምድር ሲሳይ መኾኑ አይቀርም። የደረሰው ጤፍም እንዲሁ….
“ጤፉ የፍሬውን ዛላ መሸከም ተስኖት አንገቱን ደፍቷል” ከሰሞኑ መነሻየን ባሕር ዳር ከተማ አድርጌ በመርዓዊ በኩል ወደ ምሥራቅ ጎጃም አቅንቼ ነበር።
በጉዞየ ግራ ቀኙን ሳማትር ማሣ ላይ ያለው የበቆሎውን ይዞታ በአግራሞት በእጅ መዳፍ አፍ የሚያስከድን ኾኖ ታዝቤያለሁ።
በዚህም ተደምሜ ሳላበቃ ከጎኔ የመቀመጫ ወንበር ለተጋሩኝ ገራገር አርሶ አደር “የበቆሎው ቁመና ሲያምር?” አልኳቸው። እሳቸውም ፈገግ አሉና “ኧረ ገኝ” ወደ ማሣው ዘልቀህ ብትገባስ ታምር ነው የምታየው።
“እኔ በዕድሜየ እንደ ዘንድሮ ያለ ያማረ የሰብል ወቅት አላየሁም። በቆሎ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ጤፍ እና ዳጉሳ ፍሬውን ተሸክመውታል። ለመሠብሠብ ያብቃው ነው ያሉኝ።
“አንዱ የበቆሎ አገዳ እስከ ሦስት በቆሎ ‘አዝሏል’ ⎡ይዟል ለማለት ነው⎤። ሁለት በቆሎማ ተራ ነው” አይሉኝም መሰላችሁ።
መኪናው ጉዞውን ቀጥሏል። የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳን አልፈን ሜጫ ወረዳ መልከዓ ምድር እንደደረስን ከባድ የፍንዳታ ድምጽ ተሰማ። የተሳፈርንበት መለስተኛ የአውቶቡስ መኪናም ሚዛኑን ስቶ ተወዛወዘ። ተሳፋሪው መቀመጫው ላይ ክው ብሎ ቀረ።
“ለምን?” የምትሉ አይመስለኝም። ነገሩን “ሆድ ሲያውቅ…”ካላደረጋችሁት በስተቀር ባይ ነኝ።
ከነሐሴ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል በጸጥታ ችግር መታወክ ከጀመረ ሰንበትበት ብሎ የለ። በዚህም ምክንያት በምዕራብ አማራ የሚገኙ አውራ እና ገባር መንገዶች ሲዘጉ እና ሲከፈቱ ነው የቆዩት። በየቦታውም የተሽከርካሪ አስቁሞ እገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ የመርዶ ዜና በርክቶ ነው የከረመው። በመኾኑም የተሳፈርንበት ተሽከርካሪ የኋላ ቀኝ ጎማ ሲፈነዳ ያልደነገጠ ተሳፋሪ አልነበረም።
አሽከርካሪውም “ጎማ እስክንቀይር ድረስ ውረዱና ሩቅ ሳትሄዱ ተናፈሱ” የሚል ቀጭን መልዕክት ሲያስተላልፍ እፎይ አልን።
እኔም መኪና ውስጥ ሳየው የነበረውን የሰብል ቁመና ጠጋ ብየ እንድመለከት ዕድል ሰጠኝ።
ቀደም ሲል ወንበር የተጋሩኝ አርሶ አደር የነገሩኝን “ማየት ማመን ነው” እንዲሉ አንድ የበቆሎ አገዳ ከሦስት በላይ በቆሎ መያዙን በዐይኔ አይቼ አረጋገጥሁ። ድሮስ የአርሶ አደር ዓባይ መቼ ኑሮ ያውቅና!
ሰሜን ጎጃም ላይ በኩታ ገጠም የተዘራው በቆሎ እንደ ሀገሬ ወታደር በተጠንቀቅ የቆመ ይመስላል፤ በቁመት ተመሳሳይ ነው። ያለበት ይዞታም እንዲሁ። አንዱ የበቆሎ አገዳ በትንሹ ሁለት በቆሎ ይዟል። ዐይንዎን እስኪደክመዎት ቢመለከቱ የሚመልሰዎት ከአድማስ ባሻገር ነው።
በየማሣው ያለው በቆሎ መድረቅ በመጀመሩ በነፋስ ኃይል “ሿ..ሿ..ሿ…!”የሚል ድምጽ ያሰማል።
ይህን እስከ አድማስ ጥግ የቆመ የመሰለውን የበቆሎ ቁመና ያዬ ሰው “አርሶ አደሩ ብቻውን ሠብሥቦ ይጨርሰው ይኾን?” ማለቱ አይቀርም።
የመኪናችን የፈነዳው ጎማ ተቀይሮም ጉዟችንን ቀጠልን። “አየኽው አይደል አዝመራውን” አሉኝ እኒያ በባሕር ዳር ከተማ ታክመው ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ያሉት አርሶ አደር።
ከአይጠገብ ጨዋታቸው አስከትለውም “ሰብሉማ ወጥቶ ነበር፤ ግን ይህ… ያለ ጊዜው የመጣው ዝናብ ሊያበላሸው መኾኑ እንቅልፍ ነሳን እንጂ፤ ለአጨዳ የደረሰው በቆሎ ቶሎ ታጨዶ ካልተሠበሠበ ወይቦ ይበላሻል። ሳይሸለቀቅም ይበቅላል። ጤፉም ይበሰብሳል። በምስጥም ይበላል። ስለዚህ ተሻምተን መሠብሠብ አለብን። እንዲያ ሲኾን ነው ያየነውን ፍሬ የምንበላው” አሉኝ በትካዜ ድምጸት።
እኔም ለአርሶ አደሩ ከጎናቸው መኾናችንን በመንገር እያበረታተኋቸው ጉዛችንን ቀጥለናል።
በሰሜን ጎጃም ዞን እና አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በተመለከትነው የሰብል ቁመና እየተደመምን ምዕራብ ጎጃም ቀጣና ደረስን።
ኧረ እናንተዬ! ወዲህና ወዲያ የሚመለከቱት በኩታ ገጠም የተዘራ የጤፍ እና የበቆሎ ሰብል ነው። በተለይ ጤፉ የፍሬውን ዛላ መሸከም ተስኖት አንገቱን ደፍቷል።
በአንዳንድ ቦታም አርሶ አደሮች ተሽቀዳድመው ሰብላቸውን አጭደው ዝናብ በማያስገባ መልኩ ከምረዋል።
በሰብሉ ቁመና እየተደነቅን፣ አጨዳ ላይ ያሉትን አርሶ አደሮች እያየን “ጎበዞች!” ብለን አድንቀን ሳንጨርስ ከንፈር የሚያስመጥጥ ነገር ድንገት ገጠመን።
ፍንትው ብላ ወጥታ የነበረችው ፀሐይ ድንገት በደመና ተሸፈነች። አካባቢው ጠቋቆረ። ሁለመናችንን ቀዘቀዘን። የመሸም መሰለን። በቃ! መኪናችንም የበረዳት እስኪመስል ውስጧ ቀዘቀዘ።
ከመቅጽበት “አህያ የማይችለው ዶፍ ዝናብ” መውረድ ጀመረ። የመኪናው መስታዎት በጉም በመሸፈኑ ለማየት ተቸገርን። ብቻ እየተጓዝን ነው። ምዕራብ ጎጃም መዝነብ የጀመረ ምሥራቅ ጎጃምም ተጠናክሮ ጠበቀን። ትንሽ ቆይቶ ግን ዝናቡ አባራ።
በምሥራቅ ጎጃም እዚህም እዚያም ጤፍ ተከምሮ ይታያል። በሌላው ቀን ከደብረ ማርቆስ ወደ ባሕር ዳር ስመለስ በየማሳው አርሶ አደሮች በውስን አካባቢዎች በደቦ ሰብል ይሠበሥባሉ።
በብዛት ደግሞ አርሶ አደሮቹ በተናጠል ሰብሉን ይሠበሥባሉ። ወዲህ ደግሞ ዝናቡ ቀን እና ምሽት መዝነቡን ቀጥሏል።
እንዲህም አልሁ ለራሴ። ያ ከእግር እራሱ ያፈራው ባቄላ እና አተር በጊዜ ካልተሠበሠበ የምድር ሲሳይ መኾኑ አይቀርም። የደረሰው ጤፍም እንዲሁ።
ማሣ ላይ ዓይን ያጠገበው የሰብል ቁመናም ሳይባክን በአግባቡ መሠብሠብ አለበት። እኛ ኢትዮጵያውያን ጠላት ሲመጣ ፆታ እና ዕድሜ ሳይበግረን “ሆ!”ብለን በማበር ማሸነፋችንን ዓለም ያወቀው፤ ፀሐይ የሞቀው ነባራዊ ሐቅ ነው። እንደዚሁም ሁሉም ማኅበረሰብ በየአካባቢው በዘመቻ መልክ በመውጣት በሰብል ሥብሠባ ልንዘምት ይገባናል።
ዘንድሮ በየማሣው የሚታየው የሰብል ቁመና ማለፊያ ቢኾንም ወዲህ ደግሞ ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ የጥፋት በትሩን እያሳረፈበት ይገኛል። መፍትሔው ደግሞ ተፈጥሮ በጥፋቱ ሳይቀድመን እኛ አብረን ልንቀድመው ይገባናል። እንዲህ ስናደርግም ነው ያየነውን የማሣ ላይ ፍሬ የሚበላ ማድረግ የምንችለው።
እንደ መውጫ
በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ልብ ይሏል። 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርትም ይጠበቃል። ለስኬታማነቱ ደግሞ ሰብልን በደቦ ሠብሥቦ ከብክነት በጸዳ ሁኔታ ወደ ጎተራ ማስገባት ግድ ይላል ባይ ነኝ።