የአፋር ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች ለክልሉ ሰላም እና ልማት በጋራ ለመስራት ተስማሙ
የአፋር ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስረክበው ለክልሉ ሰላም እና ልማት በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
በአፋር ክልል አብአላ ከተማ ላይ በተካሄደው ስነ ስርአት ላይ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ አወል አርባ ትጥቃቸውን አስረክበዉ በሠላም ወደ ክልሉ ለመጡ ወጣቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን በመጠቆም ታጣቂዎቹ የሠላምን መንገድ መምረጣቸው ለክልሉ ሠላም መረጋገጥ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለሀገራዊ ሠላም እና አንድነት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በክልሉ ሠላም እና ልማት ላይ በንቃት መሣተፍ እንዲችሉ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ካሉ በኃላ የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ስምምነቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ጀማል ሻሌ በበኩላቸው የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ከዚህ ቀደምም በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችም ትጥቃቸውን አስረክበው ወደ ሠላማዊ መንገድ እንዲመጡ መደረጉን አውስተው በአፋር ክልልም ትጥቅ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ከአፋር ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች በተጨማሪ ራሱን የአፋር ነፃ አዉጪ ግንባር እያለ ከሚጠራዉ ታጣቂ ሀይል ጋርም በተሠራው ዉጤታማ ስራ ወደ ሠላማዊ መንገድ ማምጣት እንደተቻለ ገልፀዋል ።
ብርጋዲየር ጄኔራል ጀማል በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል በህገ ወጥ መንገድ ትጥቅ ይዞ የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ሃይል እንደሌለ አስታውቀው ከዚህ ለሀገር አንድነት እና ሠላም ከሚበጅ በጎ ተግባር ሌሎች ክልሎችም ትምህርት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ጋዶ ሐሞሎ ታጣቂዎቹን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ተከታታይ ውይይቶች ሲካሔዱ መቆየታቸውን ገልጸው የሀሳብ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ መፍታት እንደ ባህል መለመድ ያለበት አሰራር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ከግጭት እና ጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ የተናገሩት የአፋር ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች ሊቀመንበር ሀጂ ስዩም አወል ከአሁን በኋላ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አክብረን በሠላማዊ መንገድ ህዝባችንን ለማገልገል በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ካሉ በኋላ ለዚህ ታሪካዊ የሠላም ስምምነት መሳካት መከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት