በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን በፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ 461 ስር የተጠቀሱትን ካላሟላ በስተቀር ሊፈፀም አይችልም፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በግልግል ዳኝነት እና ዕርቅ አሰራር ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀፅ 53 ጭምር የተመለከቱ ናቸው፡፡ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህጉ በውጭ ሀገር ለተሰጠ ፍርድ አፈፃፀም የተደነገጉ ድንጋጌዎች ሁሉ በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን ላይም በተመሳሳይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
መግቢያ
የሰው ልጆች መስተጋብር በተለይ በአሁኑ የአለም ሁኔታ በሀገራት ድንበር የተገደበ አይደለም፡፡ በዚህ መስተጋብር መካከል ወደ ፍርድ ቤት ወይም ወደ ሌሎች አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች የሚሄዱ እና አፈፃፀማቸው በተለያዩ ሀገራት የሚሆኑ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ መሰል የውጭ ሀገር ፍርዶችን የማስፈፀም ጉዳይ የአለም አቀፍ የግለሰቦች ህግ (private international law) አካል ሲሆን ሀገራት የውጭ ሀገር ፍርድ ለማስፈፀም እንዲረዳቸው የህግ ማእቀፍ ያዘጋጃሉ፡፡ በተጨማሪም በርካታ ሀገራት ሁለት ውይም ከሁለት በላይ ባሉ ሀገራት በሚደረግ የአለም አቀፍ ስምምነት የውጭ ሀገር ፍርድን ያስፈፅማሉ፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ በውጭ ሀገር የተሰጡ ፍርዶች እና በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ በሀገራችን የሚኖረውን የአፈፃፀም ሥርአት እንመለከታለን፡፡
በውጭ ሀገር የተሠጡ ፍርዶች ምንነት
የውጭ ሀገር ፍርድ ማለት በውጭ ሀገር መንግስት ፍርድ ቤት የተሰጠ ፍርድ ማለት እንደሆነ እና የውጭ ሀገር ፍርድ ቤት ማለት ደግሞ ከኢትዮጵያ ግዛት ክልል ውጭ የሚገኝ በሀገሩ ህግ መሰረት የተቋቋመ የማናቸውም ሀገር ፍርድ ቤት እንደሆነ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ አንቀፅ 3 ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ በተጨማሪም የግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ዓ.ም አንቀፅ 2/8/ በውጭ ሀገር ለተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ ትርጉም የሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያ ባፀደቃቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት በውጭ ሀገር እንደተሰጠ የሚቆጠር የግልግል ውሳኔን ወይም የግልግል ዳኝነቱ መቀመጫ በውሳኔው ውስጥ ከኢትዮጵያ ግዛት ውጭ መሆኑ የተገለፀበት ውሳኔ እንደሆነ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡
በውጭ ሀገር የተሰጠ ፍርድ እንዲፈፀም የሚቀርብበት ሥርአት
በአለም አቀፍ ስምምነት በተለየ እንዲፈፀም የሚያደርግ ልዩ ህግ ከሌለ በስተቀር ከኢትዮጵያ ግዛት ውጭ የተሠጠ ፍርድ፣ ውሳኔ ወይም ብይን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀመው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህጉ መሰረት እንደሚሆን በሥነ ሥርአት ህጉ አንቀፅ 456 ተመልክቷል፡፡ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ አንቀጽ 456(2) መሰረት የውጭ ሀገር ፍርድ የሚፈፀመው እንዲፈፀም ማመልከቻ ከቀረበ ብቻ ነው፡፡ በፌ.ዴ.ራ.ል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ዓ.ም መሰረት የውጭ ሀገር ፍርድ ማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆኑ ማመልከቻው መቅረብ ያለበት ለዚሁ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ይህ ማመልከቻ ሲቀርብም
• የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ ትክክለኛነት የተረጋገጠበት የፍርድ ግልባጭ
• ፍርዱ በተሰጠበት ሀገር ፍርዱ የመጨረሻ እና መፈፀም የሚገባው መሆኑን የሚያረጋግጥ በፈረደው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይም ሬጅስትራል የተፈረመ የምስክር ፅሁፍ በአባሪነት አብሮ መቅረብ አለበት፡፡
የውጭ ሀገር የተሰጠ ፍርድ እንዲፈፀም ማመልከቻ የቀረበለት ፍርድ ቤት ባለእዳው ቀርቦ አስተያየቱን እንዲገልፅ መብት መስጠት ያለበት ሲሆን ለዚህም ቀነ ቀጠሮ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ጉዳይ ለማጣራት ተከራካሪ ወገኖችን አስቀርቦ ክርክራቸውን መስማት አስፈላጊ ነው ብሎ ካላመነ በስተቀር ውሳኔ የሚሰጠው በቀረበለት ማመልከቻ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የውጭ ሀገር ፍርድ የሚፈፅመው ፍርድ ቤት በማናቸውም ግዜ የሚያጠራጥር ሁኔታ ያጋጠመ እንደሆነ አጠራጣሪ የሆነው ጉዳይ እስኪጣራ ድረስ በአንቀፅ 459(3) መሰረት የውጭ ሀገር ፍርድ አፈፃፀም ውሳኔን ሊያግደው ይችላል፡፡
ፍርድ ቤቱ ማመልከቻውን ተቀብሎ ፍርዱን ለማስፈፀም ከወሰነ አፈፃፀሙ የሚመራው በኢትዮጵያ ውስጥ የተሰጠ ፍርድ በሚፈፀምበት ሥርአት እንደሚሆን በሥነ ሥርአት ህጉ አንቀፅ 460(3) ተመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ሲወስን ስለወጪ እና ኪሳራ አከፋፈል አብሮ መወሰን አለበት፡፡
በውጭ ሀገር የተሠጠ ፍርድ ወይም ብይን የማስፈፀም ቅድመ ሁኔታዎች
በውጪ ሀገር የተሰጠ ፍርድ ይፈፀም ዘንድ ሥነ ሥርአት ህጉ በአንቀፅ 458 ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎቹም መሟላት አለባቸው፡፡ ይኸውም
• እንዲፈፀም የተጠየቀውን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ የተሰጠን ፍርድ የሚፈፅም መሆኑ መረጋገጥ
• ፍርዱ የተሰጠው በህግ በተቋቋመ ፍርድ ቤት መሆን
• ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት የፍርድ ባለእዳው መቃወሚውን እና መከራከሪያውን ለማሰማት መብት ተሰጥቶት የነበረ መሆኑ መረጋገጥ
• የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ የመጨረሻ እና ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ መታወቅ
(የመጨረሻ ፍርድ የሚባለው በይግባኝ የሚታይበትን ሂደት በሙሉ የጨረሰ እና እንደገና የማይታይ ሲሆን ነው፡፡)
• የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ ለህዝብ ሞራል (public moral) እና ፀጥታ (public order) ተቃራኒ ያልሆነ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
የህዝብ ሞራል ሲባል የሚፈፀመው የውጭ ሀገር ፍርድ በሀገራችን ህብረተሰብ ዘንድ በጠቅላላው ተቀባይነት ያለው ወይም ለባህል ተቃራኒ ያልሆነ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ህግ ተቀባይነት ሌላቸው የኮንትራት(የውል ጋብቻ) ወይም ተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ በሌላ ሀገር ቢከናወን እና ከዚህ ጋር በተያያዘ በተነሳ ክርክር አፈፃፀሙ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣ ለህግ እና ለሞራል ተቃራኒ በመሆኑ ኢትዮጵያ ማመልከቻውን ተቀብላ አታስፈፅምም፡፡
እነዚህን በህጉ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች የማያሟላ የውጪ ሀገር ፍርድ በኢትዮጵያ ሊፈፀም አይችልም፡፡
በተመሳሳይ በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን በሀገራችን የሚፈፀመው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህጉ አንቀፅ 461 የተመለከቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟላ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም፡-
• በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ አንቀፅ 458(ሀ) መሰረት የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይኑ የተሰጠበት ሀገር በኢትዮጵያ የሚሰጥን ብይን የሚፈፀም የሆነ እንደሆነ
• ብይኑ የተሰጠው ተከራካሪዎቹ ወገኖች ለግልግል ወይም ለሽምግልና ዳኞች ጉባኤ ባቀረቡት ስምምነት መሰረት ወይም ብይን የተሰጠበት ሀገር ህግ በሚፈቅደው መሰረት የሆነ እንደሆነ
• ተከራካሪ ወገኖች የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኞችን ለመምረጥ የእኩልነት መብት ተሰጥቷቸው እንደሆነ ወይም በክርክር ላይ ማስረጃቸውን ለማቅረብ እና ክርክራቸውንም ቀርቦ ለመስማት የእኩልነት መብት አግኝተው እንደሆነ
• የግልግሉ ወይም የሽምግልናው ዳኝነት ጉባኤ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ተቋቁሞ ከሆነ
• ብይኑ የተሰጠበት ጉዳይ በኢትዮጵያም ህግ በግልግል ወይም በሽምግልና ዳኝነት ሊታይ የሚችል እንደሆነና የፍርዱም አፈፃፀም የህዝቡን ሞራል እና ፀጥታ የማይቃረን እንደሆነ
• የተሰጠው ብይን የኢትዮጵያ ህግ በሚያዘው እና በሚፈቅደው ሁኔታ ሊፈፀም የሚችል እንደሆነ ነው፡፡
በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን በፍትሐብሔር ህግ አንቀፅ 461 ስር የተጠቀሱትን ካላሟላ በስተቀር ሊፈፀም አይችልም፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በግልግል ዳኝነት እና ዕርቅ አሰራር ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀፅ 53 ጭምር የተመለከቱ ናቸው፡፡ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህጉ በውጭ ሀገር ለተሰጠ ፍርድ አፈፃፀም የተደነገጉ ድንጋጌዎች ሁሉ በውጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ብይን ላይም በተመሳሳይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በውጭ ሀገር የተሰጠን ፍርድ እና የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ውሳኔ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ለማስፈፀም በህጉ የተደነገጉት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡ በመሆኑም በውጪ ሀገር የተሰጠ ፍርድ ወይም የግልግል ወይም የሽምግልና ዳኝነት ውሳኔ ማስፈፀም የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በቅድሚያ ቅድመ ሁኔታዎቹ መሟላታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴርን